አዲስ አበባ- አዲስ ሹም ሽር
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እስካሁን የሠላም ሚንስትር የነበሩትን ብናልፍ አንዷለምን ሽረዉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሐን ባለሥልጣን የበላይ ኃላፊ የነበሩትን መሐመድ ኢድሪስን በሠላም ሚንስትርነት ሾመዋል።የኢትዮጵያ መንግሥት መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት አቶ መሐመድ ኢድሪስ መሐመድ የሠላም ሚንስትርነቱን ሥልጣን የተሾሙት ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ሕዳር 18፣2017 ነዉ።አቶ መሐመድ ኢድሪስ ከመጋቢት 2013 ጀምሮ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሐን ባለሥልጣን የበላይ ኃላፊ (ዋና ዳይሬክተር) በመሆን ሲያገለግሉ ነበር። ከጥቅምት 2013 ጀምሮ የሠላም ሚንስትርነቱን ሥልጣን ይዘዉ የነበሩት አቶ ብናልፍ እንዷለም አዲስ የተሾሙበት ኃላፊነት ሥለመኖር አለመኖሩ የተባለ ነገር የለም።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ ከመጋቢት 2010 ወዲሕ በተደጋጋሚ የሚንስትሮችና የከፍተኛ ባለሥልጣን ሹም ሽር ያደርጋሉ።ተደጋጋሚዉ ሹም ሽር የኢትዮጵያ መንግሥት ሥራና አስደዳርን ለማሻሻል ይረዳ ይሆን? ተወያዩበት።
አሶሳ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የአገዳ ምርት በእሳት ታቃጠለ
የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የአገዳ ምርት በእሳት መቃጠሉን ነዋሪዎችና የፋብሪካው ሠራኞች አስታወቁ። በምዕራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሱሉላ ፍንጫ ወረዳ የሚገኘው የፍንጫ ስኳር ፍብሪካ የአገዳ ምርት ትናንት መቃጠሉን የፋብሪካዉ ሠራተኞችና ነዋሪዎች አስታወቁ።
የፋብሪካዉ ሠራተኞች እንዳሉት ትናንት ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ የተነሳዉ እሳት በአምስት ማሳዎች ላይ የነበረዉን የሸንኮራ አገዳ አቃጥሎታል።የፍንጫ ስኳር ፍብሪካ በሚሊዩን ኩንታል የሚቆጠር ስኳር ያመርት ነበር።ከ2015 ዓ.ም ወዲህ በተለያየ ጊዜ በደረሰበት ጥቃት ምርቱ መቀነሱን ሰራተኞቹ ተናግረዋል፡፡ የትናንትናው ቃጠሉ በማን እንደተለኮሰ ባይታወቅም ከዚህ ቀደም በፋብሪካው ይዞታ ውስጥ በህግ ወጥ መንገድ የሚያርሱ ግለሰቦች ያመረቱትን ምርት የአካባቢው የወረዳ አስተዳደር መውረስ መጀመሩን ተከትሎ በቂም በቀል ያደረጉት ሳይሆን እንዳልቀረ ዶቼቬለ ካነጋገርናቸው ሰራተኞች አንዱ ጠቁመዋል፡፡
"ትናንት አገዳ ተቃጥሎብን ነበር፡፡ አንድ ዶዘርም ተቃጥሏል፡፡ ከቀኑ 8፡00 እስከ ምሽቱ 1፡30 የእሳቱን እያጠፋን ነበር፡፡ ብዙ ሄክታር የሚሆን አገዳ የተቃጠለ ሲሆን መንደር 2 የተባለ ቦታ ብቻ ከ50 አስከ 60 ሄክታር ይሆናል የተቃጠለው፡፡ ሰክሽን ‹ዲ እና ኢ‹ የሚባሉ ቦታዎች አሉ እዛም ተቃጥሏል፡፡"
የአሶሳዉ ወኪላችን ነጋሳ ደሳለኝ በጉዳዩ ላይ ከፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ እና ከሱሉላ ፍንጫ ወረዳ አስተዳደር መረጃ ለማግኘት ቢሞክርም አልተሳካም፡፡ የፍንጫ ስኳር ፍብሪካ በግንቦት 2015 ዓ.ም በደረሰበት ጥቃት በቢሊዩን ብር የሚገመት ውድመት ደርሶበት እንደነበር ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
አምስተርዳም ኔዘርላንድ ለእሥራኤል የጀት መለዋወጫዎች እንዳትሸጥ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም የጣለው እግድ እንዲፀና ተጠየቀ
የኔዘርላንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መንግሥት ለእስራኤል የF«35»ተዋጊ ጀቶች መለዋወጫዎች እንዳይሸጥ የጣለውን እግድ እንዲያጸና ተጠየቀ። እግዱ እንዲጸና አቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ምክር ለግሷል። ባለፈው የካቲት የሄጉ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ መንግሥት የመለዋወጫዎቹን ሽያጭ እንዲያቆም ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። ትእዛዙ የተላለፈው በጋዛው ጦርነት ወቅት መለዋወጫዎቹ ዓለም አቀፍ ሕግን ለመጣስ ጥቅም ላይ ይውላሉ በሚል ስጋት መነሻነት ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ ንብረት የሆኑ የF-35 መለዋወጫዎች መጋዘኖች ከሚገኝባቸው ሀገራት አንዷ ከሆነችው ከኔዘርላንድስ ከጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 2023 ዓ.ም. አንስቶ መለዋወጫዎቹ እሥራኤልን ጨምሮ ለሌሎች ሀገራትም ይከፋፈላሉ። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በይግባኙ ላይ ቀን ሳይቆርጥ በቅርቡ ብይን እንደሚሰጥ አስታውቋል። የቻሪቲ ኦክስፋም የኔዘርላንድ ቅርንጫፍን ጨምሮ በመንግሥት ላይ ክስ የመሰረቱት የሰብዓዊ መብቶች ቡድኖች ለፍርድ ቤቱ ምክር በመሰጠቱ ተደስተዋል።
ጋዛ በዳቦ መሸጫ ቤት በተፈጠረ ግፍያ ሦስት ሰዎች ሞቱ
በምግብ ቀውስ ውስጥ በሚገኘው በጋዛ ሰርጥ በአንድ ዳቦ ቤት ውስጥ በተፈጠረ ግፍያ ሁለት ህጻናትና አንዲት ሴት መሞታቸውን የህክምና ባለሥልጣናት ተናገሩ። ማዕከላዊ ጋዛ ዴር አል ባላህ ውስጥ ወደሚገኘው አልአክሳ የሰማዕታት ሆስፒታል የተወሰዱት ህጻናቱና የ50 ዓመቷ ሴት የሞቱት ታፍነው መሆኑን አንድ ሐኪም አረጋግጠዋል። ባለፉት አስራ አራት ወራት እሥራኤል ወደ ጋዛ እንዲገባ የምትፈቅደው ምግብ መጠን እያሽቆለቆለ ሄዷል።የእስራኤል ይፋ መረጃዎችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ባለሥልጣናት ፣የሰብዓዊ እርዳታ ጥገኛ በሆነው የጋዛ ህዝብ ላይ ረሀብና ተስፋ መቁረጥ እያየለ መምጣቱን ይናገራሉ። ጋዛ የሚገኙ አንዳንድ ዳቦ ቤቶች ባለፈው ሳምንት የዱቄት እጥረት ከገጠማቸው በኋላ ለተወሰኑ ቀናት ተዘግተው ነበር። ዳቦ ቤቶቹ ከተከፈቱ በኋላ ደግሞ ዳቦ ለመግዛት የመጡ በርካታ ሰዎች ሲጋፉና ሲጮሁ ታይተዋል። ጋዛ ሰርጥ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ፍልስጤማውያን የዳቦ ቤቶችና በነጻ ምግብ የሚያድሉ ድርጅቶች እጅ ጠባቂ ናቸው። አብዛኛዎቹ በቀን አንዴ ብቻ ነው ምግብ የሚያገኙት ።
ቤይሩት ከተኩስ ቀቁሙ በኋላ ሊባኖስ የተመለሱ በርካቶች ቤቶቻቸው ፈርሰዋል
በእሥራኤልና በፈፈጣ ተዋጊው ቡድን ሄዝቦላ መካከል በዚህ ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያን ወደየመንደሮቻቸው እየተመለሱ ነው። ይሁንና ብዙዎቹ ባለፉት ሁለት ወራት በእሥራኤል የአየር ድብደባ መኖሪያ ቤቶቻቸው ፈርሰዋል። እሥራኤል ፣በምሥራቅና ደቡባዊ ሊባኖስ እንዲሁም ከቤይሩት በስተደቡብ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ባካሄደችው የአየር ድብደባ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል። የተኩስ አቁም ስምምነቱ በአካባቢው የሀማስ እሥራኤል ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የመጀመሪያው ዋነኛ የለውጥ ምልክት ነው። ይሁንና ስምምነቱ ለጋዛው ጦርነት ያመጣው መፍትሄ የለም። በእስራኤል በጀርመን በዩናይትድ ስቴትስና በብሪታያንያ እንዲሁም በሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት በአሸባሪነት የተፈረጀው ሀማስ መስከረም 26 2015 ዓም በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ በተነሳው እስካሁን በቀጠለው የእሥራኤል ሀማስ ጦርነት የጋዛ የጤና ሚኒስቴር እንደሚለው ከ44 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል ከ104 ሺህ በላይ ደግሞ ቆስለዋል።በዚሁ ጊዜም እሥራኤል የጋዛን አብዛኛውን ክፍል አውድማለች። ከዚያ የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥርም ወደ 2.3 ሚሊዮን ይጠጋል።
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ