የኅዋ ምርምር እንዲበጅ ለምድር፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 12.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የኅዋ ምርምር እንዲበጅ ለምድር፣

የአውሮፓ የኅዋ ምርምር ድርጅት (ESA) የተቋቋመበትን 10 ኛ ዓመት ከሰሞኑ በተለያዩ መርኀ ግብሮች አስቦታል ። የወደፊት ተግባራቱንም ለማከናወን ከጀርመን የከባቢ አየርና የኅዋ አሰሳ ወይም ምርምር መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር አያሌ መርኀ

ግብሮችን ተልመዋል።ጋሊሌዮ ከተሰኘው የአውሮፓውያን የአቅጣጫ መምሪያ ሳቴላይት ሌላ በዛ ያሉ የመገናኛ ሳቴላይቶችን የማምጠቁ ተግባር የተለመደ የስራ ክንዋኔ ሆኗል።

ለሥነ ፈለክ ተመራማሪዎችም ሆነ ፤ በአጠቃላይ ለሳይንስ ጠበብቱ አጓጊ ሆኖ የተገኘው፤ ኅዋን ዘልቀው የሚያስሱት ሰው ሠራሽ ሳቴላይቶች ተግባርና ፕላኔታችንን የሚቆጣጠሩ ሳቴላይቶች ምርምር ነው። በመሆኑም ፣  የጀርመን የኅዋ ምርምር  ማዕከልና የአውሮፓው የኅዋ ምርምር ድርጅት በመተባበር፤   ስለ ኅዋ  በሰፊው ለማወቅ፤ እንዲሁም ስለፕላኔታችን ጠለቅ ያለ ዕውቀት ለማካበት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

ስለሆነም የአውሮፓው የኅዋ ምርምር ድርጅት፣ ዘንድሮ  በተለይ ካለፈው ጥር ወር አንስቶ ሰፋ ያሉ አቅዶችን የዘረጋ ሲሆን፤ ከሚያመጥቃቸው ሳቴላይቶች መካከል በምድራችን  ላይ   በተለይ  በአትክልቶችም ሆነ አጽድ የሚታየውን ለውጥ የሚከታተሉና  በምድራችን ፤ ከፀሐይና ከሌሎችም ከዋክብት የሚፈነጥቀውን እጅግ አደገኛ ጨረር  የሚከላከለውን የምድርን ዋልታ  መግነጢሳዊ ጋሻ እንቅሥቃሴ ለውጥ  የሚከታተሉ ይገኙበታል።

በቅርቡ የተካሄዴ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ መግነጢሳዊው የሰሜን ዋልታ ጣቢያ ከ 500 መቶ ዓመታት ወዲህ  ባልተጠበቀ ፍጥነት ከሰሜን ጫፍ ወደ  ምሥራቅ በማጋደል ላይ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የአቅጣጫ አመላካች መሣሪያዎች (ኮምፓሶች)አቅጣጫ ከመልክዓ ምድራዊው ጣቢያ በእጅጉ በመራቅ እየተለወጠ ነው።

ይኸው  ከኅዋ ወደ ምድራችን የሚፈነጥቅን  አደገኛ ጨረር በሚያስደንቅ ሁኔታ  ጋሻ ሆኖ የሚመክተው መግነጢሳዊ ጣቢያ ተግባሩን የሚያከናውነው በትኅተ ምድር 2,500 ሜትር ጥልቀት ላይ  የምድራችን ብረትነት ያለው  ፈሳሽ ክፍል  እንደውቅያኖስ  በሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ነው። የምድራችን የተጠቀሰው ውስጣዊ አካል ፤ የሙቀቱ መጠን፤ ከ 20 ዓመት በፊት በቤተ ሙከራ የተካሄደ የምርምር ውጤት ከገለጠው በላይ እጅግ የጋለ መሆኑም ዘንድሮ ሊታወቅ ችሏል። እ ጎ አ በ 1993 ዓ ም፤ ጀርመናውያን ተመራማሪዎች፤ካስታወቁት የሙቀት መጠን፣ ያሁኑ፣ በ 1000 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ልቆ መገኘቱ ነው የተነገረው። የአውሮፓ የጨረር የምርምር ድርጅት  እንዳለው ከምድራችን የውስጥ አካል ማዕከል አቅራቢያ ፤ የሙቀቱ መጠን፤ 6,000 ዲግሩሪ ሴንትግሬድ ነው።

በከርሠ -ምድር ፤ የመሬት ብረትነት ያለው ፈሳሽ ክፍል ፣ ዑደቱ ከቀሪው የምድራችን ክፍል ዘገምተኛ ሲሆን፤ በዚህ ባልተመጣጠነ እንቅሥቃሴ ሳቢያ በሚመነጨው  የኤሌክትሪክ  ፍሰትም ነው መግነጢሳዊው ጣቢያ የሚፈጠረው።  እንደ ወንዝ የሚንቀሳቀሰው የኤልክትሪክ ፍሰት፣ መደበኛ አይደለም ይለዋወጣል። የቅርብ ጊዜ ምርምር እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ የምድር ዋልታ ተዘዋዋሪ እየሆነ ነው። ከአያሌ ምዕተ -ዓመታት የተደላደለ ይዞታ ወዲህ ፤ በአሁኑ ጊዜ፤ በያመቱ 55 ኪሎሜትር  ከካናዳ ወደ ሩሲያ በመሸጋሸግ ላይ ነው። በዚህ ፍጥነት  መንቀሳቀሱ ከቀጠለ፤ በ 50 ዓመታት ውስጥ፤  የሰሜን ምድር ዋልታ ፣ መልክዓ- ምድራዊው ሳይሆን ፣ መግነጢሳዊው ዋልታ፣ የሚገኘው በሳይቤሪያ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ጠበብት እንደሚሉት ከሆነ፤ የሰሜኑ መግነጢሳዊ ዋልታ፣ ደቡባዊ መግነጢሳዊ ዋልታ በመሆን ቦታ የመለዋወጥ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ልውውጥ፤ ከ 780,000 ዓመታት በፊት  አጋጥሞ እንደነበረ ነው የሚነገረው።  በምድራችን የአፍርና ቋጥኝ ታሪክ በአንድ ሚሊዮን  ዓመት ውስጥ 5 ጊዜ ያህል የተጠቀሰው ዓይነት ልውውጥ ካጋጠመ በኋላ፣ 50 ሚሊዮን ዓመታት  ገደማ ተመሳሳይ ሁኔታ  እንዳልተከሠተ ነው የተገለጠው።

ታዲያ በእንዲህ ዓይነቱ ለውጥ፣ መግነጢሳዊው የምድር ዛቢያ ጫፍ ጣቢያ፣ ኃይሉ በጣም ከተዳከመ፤ ምድራችን ፤ ከፀሐይ የሚመጣውን አደገኛ  የጨረር ማዕበል መከላከል ያቅታትና ፤ እንዲሁ በነባቤ-ቃል እንደሚነገረው እንስሳትና እጽዋት ሊረግፉ ይችላሉ።

ሰውም  ከእንስሳት  የተለየ ዕጣ ሊያጋጥመው አይችልም ። በኅዋ የተኮለኮሉ የመገናኛ ሳቴላይቶች ተግባር ይሠነካከላል፣ የናይትሮጂን ኦክሳይድ ጋዝ መጠን  ከፍ ይላል፤ በምድር ገጽ ላይ አደገኛ ጨረር ሳንክ ይፈጥራል። አቅጣጫ አመላካቹ መሣሪያ (ኮምፓስ )ከጥቅም ውጭ ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ በእርግጥ  ሊያጋጥም የሚችልበትን የጊዜ ቀመር የሚያውቅ አንድም የሥነ ፍጥረት ተመራማሪ አይገኝም።    

ዘንድሮ ፣ ካለፈው ሳምንት  አንስቶ 10ኛ ዓመቱን በማሰብ ላይ የሚገኘው የአውሮፓው የኅዋ ምርምር ድርጅት፤ ግንቦት 29,2005 ፣ «አውቶሜትድ ትርንስፈር ቢዬክል» በሚባለው የጭነት መንኮራኩር አማካኝነት፤ ከዚህ ቀደም በክብደቱ መጠን ወደር ያልተገኘለት 4,8 ቶን ነዳጅ ፤ የተለያየ የምግብ ዓይነት ፣ ውሃ ፣  ልብስ፤ የምርምር መሳሪያዎችንም  ጨምሮ ፤ በአጠቃላይ 6,6 ቶን የሚመዝን ስንቅ  ለዓለም አቀፉ የጠፈር  ምርምር ጣቢያ ጭኖ  እንዲያደርስ ፤ ከኮሩ ፈረንሳይ ጋያና ፤ በአርያነ -5 ሮኬት  በተሣካ ሁኔታ ወደ ኅዋ እንዲመጥቅ አድርጓል ።

በሰዓት 28,000 ኪሎሜትር ያህል የሚከንፈው መንኮራኩር ፣   ከ 3  ቀን በኋላ ፣ ከዓለም አቀፉ የኅዋ የምርምር ጣቢያ ጋር በመገጣጠም ጭነቱን ያራግፋል። ብብሬመን የሚገኘው የአውሮፓው የኅዋ ምርምር ኩባንያ -አስትሪዬም እንዳስታወቀው፤ በአሪያነ 5 ሮኬት መንኮራኩር በተሣካ ሁኔታ ሲመጥቅ የሰሞኑ 55ኛ ው መሆኑ ነው። ይኸው ATV-4 በሚል የአንግሊዝኛ ምኅጻር የሚታወቀው መንኮራኩር በመጪው ጥቅምት ወር 6 ቶን ቁሻሻ ጭኖ በመመለስ፤ በሰላማዊው ውቅያኖስ ተቃጥሎ ተልእኮው ያከትማል። 

(ይቀጥላል)

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic