የኃይለማርያም የስልጣን ዘመን ሲፈተሽ | ኢትዮጵያ | DW | 02.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኃይለማርያም የስልጣን ዘመን ሲፈተሽ

ኢትዮጵያን ለአምስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፈተና የተሞላበት የስልጣን ዘመን አሳልፈዋል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በድንገት በሞት ሲለዩ የተፈጠረውን ክፍተት የመሙላት፣ ሀገሪቱን የማረጋጋት እንዲሁም በእርሳቸው የስልጣን ዘመን ለፈነዳው ህዝባዊ ተቃውሞ መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:44

ፈተና የበዛበት የኃይለማርያም የስልጣን ዘመን  

ጥቁር በጥቁር ለብሰዋል፡፡ ፊታቸው በሀዘን ዳምኗል፡፡ የዚያን ዕለት፣ ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ንጋት የተሰማውን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት የፈጠረውን መደናገር ለማረጋጋት እየሞከሩ ነው፡፡ ቦታው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ የተቀመጡበት ወንበር ደግሞ አቶ መለስ ጋዜጠኞችን ጠርተው መግለጫ ሲሰጡ የሚጠቀሙበት፡፡ ፊት ለፊታቸው ለተደረደሩ ጋዜጠኞች አጠር አጠር ያለ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ በንግግራቸው መሃል የተጠቀሙበት “በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ መሪዎች” የሚለው አገላለጽ እርሳቸውን በቅጡ እንደሚገለጽ የተገነዘቡ ይመስላል፡፡ ለዚህም ይመስላል 22 ደቂቃ በፈጀው ቆይታቸው ከራሳቸው ይልቅ ሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ኢህአዴግን እና የፓርቲያቸውን ሌሎች አመራሮች ደግመው ደጋግመው ማንሳት የመረጡት፡፡ 

«አሁን በሥራ ላይ ያለው አመራር በተፈጠረው ሁኔታ ሳይታወክ በእልህ እና በቁጭት ውጤታማ የሆኑ ፖሊሲዎቻችንን እና ስትራቴጂዎቻችን ለማስፈጸም የትግል ወኔው ከመቼውም ጊዜ በላይ የጸና ነው፡፡ ውስጣዊ አንድነቱም በአስተማማኝ ደረጃ ያለ በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ ከእኛ የሚጠበቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁዎች ነን፡፡

ዛሬም እንደወትሮው ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ ትውልድ አመራር ለሀገራችን አመራር እና ትራንስፎርሜሽን መሳካት በሚያደርገው ጥረት እና አስተዋጽኦ ከጎናችን እንደሚሰለፍ እርግጠኞች ነን፡፡ ስለዚህም ከዚህ ቀጥሎ እነዚህን ፖሊሲዎች እና ስትራትጂዎች በማስፈጸም የተሳካ ውጤት ለማምጣት የምንረባረብ መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡ ስለዚህ እንደግለሰብ እኔ ብቻ ሳልሆን የአመራር ስርዓቱ በአጠቃላይ ነው፡፡ ሁላችንም እንደቡድን ይህንን ቃል ኪዳችን አድሰን፣ ይዘን ለመቀጠል የተግባባንበት ነው» ሲሉ አቶ ኃይለማርያም አካሄዳቸው ምን እንደሚመስል ጠቆም አድርገው ነበር፡፡

ያኔ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም በዚህ የመጀመሪያ ንግግራቸው ኢትዮጵያን በቡድን ለመምራት እንደተዘጋጁ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ኢህአዴግ የቡድን አመራር (collecetive leadership) ፍልስፍናን መከተል የጀመረው በእርሳቸው ጊዜ አይደለም፡፡ እስከ 1992 የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ፓርቲ ክፍፍል ድረስ ፓርቲው በዚህ መርህ ስር ነበር የቆየው፡፡ ከክፍፍሉ በኋላ ግን ህወሓትንም ሆነ ኢህአዴግን በሊቀመንበርነት ይመሩ የነበሩት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ያለተቀናቃኝ የበላይነቱን በመቆጣጠራቸው የቡድን አመራር ገሸሽ ተደርጓል፡፡ 

በአቶ መለስ ድንገተኛ ህልፈት ያንሰራራው የቡድን አመራር ሀገሪቱ ተጨማሪ ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንዲኖሯት እስከማድረግ ተጉዞ ነበር፡፡ ሆኖም የቡድን አመራሩም ሆነ አቶ ኃይለ ማርያም በመጀመሪያ ንግግራቸው ሊያስተማምኑ የሞከሩት “በጽኑ መሠረት ላይ ያለ” የአመራር ስርዓት በእውን ዘላቂ ሆኖ ሊታይ አልቻለም፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ የጋራ አመራር ሀሳብ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም ይላሉ፡፡  

«እንግዲህ የቡድን አመራር መልሶ ለመትከል ሙከራዎች አልነበሩም አይባልም ግን በአጠቃላይ ኢህአዴግ ውስጥ ራሱ፣ ኢህአዴግ ውስጥ ባሉ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የየራሳቸውን አቅም በማፈርጠም ደረጃ የተለያየ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ሁኔታ ስልነበረ፣ ያው ሽኩቻው ስለቀጠለ የጋራ አመራር በሰከነ ሁኔታ መሬት ላይ ተጠናክሮ እንዲወጣ አላደረገውም» ሲሉ ያስረዳሉ።

በኢህአዴግ ውስጥ ስምምነት መጥፋቱ የኃይለ ማርያም የስልጣን ዘመን «በድርድር እና በማስማማት» እንዲጠመድ እንዳደረገው በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እያጠኑ የሚገኙት አቶ ጎይቶም ገብረ ልዑል ያስረዳሉ፡፡ የአቶ ኃይለ ማርያምን የስልጣን ዘመን ለመመዘንም «ስልጣን የተረከቡበት ሁኔታን መመልከት ያስፈልጋል» ይላሉ፡፡ 

«የመለስ ህልፈት ሀገሪቷን ወዲያው ነው ወደ ሽግግር የመራት፡፡ ሽግግሩ ልክ አቶ ኃይለማርያም ስልጣን እንደያዙ ነው የጀመረው፡፡ ያ ሽግግር ደግሞ በአቶ መለስ ዘመን ኢህአዴግ በአንድ ሰው የሚመራ ድርጅት ነበር፡፡ ከእርሳቸው ህልፈት በኋላ ግን ድርጅቱ ያው ተከፋፋለ፡፡ የኢህአዴግ አባላት ወይም ፓርቲዎቹ በዓላማም፣ በስልጣን ክፍፍልም መስማማት አልቻሉም፡፡

በዋነኛነት ትኩረት የምሰጠው ምንድነው? ያ የአቶ ኃይለ ማርያም የስልጣን ዘመን በድርድር ነው ያለፈው፡፡ እና በዚያ ድርድር ላይ አንድ ጠንካራ እና ሀሳቡን አመለካከቱን በሌሎች ላይ መጫን አቅም ያለው እና ፍላጎት ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኖር ድርድሩ ጥሩ ላይሄድ ይችላል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ ለምን? እንደዚያ አይነት ሁኔታ ቢፈጠር ኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ ቡድን ጋር ወግኖ እንደድሮው በጉልበት እና በኃይል የተመሰረተ ስርዓት ሊፈጠር ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ይህን ማድረግ አለመቻላቸውም፣ አለመፈለጋቸውም በኢህአዴግ አባል መካከል ትክክለኛ ድርድር እና ሀሳቦችን የማቅረብ እና በፍቃድና በስምምነት የተመሰረተ ስርዓት ለመፍጠር ጥሩ ሁኔታ የፈጠረ ነው የሚመስለኝ» ይላሉ አቶ ጎይቶም፡፡ 

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኃይለ ማርያም ልክ እንደ አቶ መለስ «ጠንካራ መሪ ሆነው አለመውጣታቸው ብዙ ጊዜ ቢያስተቻቸውም በሌላ በኩል ያለውን ይህን ጥሩ ጎን ማስተዋል ያስፈልጋል» ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም በስልጣናቸው ዘመን በሙሉ በአቶ መለስ ጫማ ሲለኩ ነበር የቆዩት፡፡ ይህንንም እርሳቸውም ገና በጠዋቱ ተረድተዋል፡፡ በመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫቸውም በመተካካት መርህ ወደ ስልጣን የመጣው እርሳቸው ያሉበት «አዲሱ የአመራር ትውልድ» ሥራውን ሲያከናውን የነበረው በአቶ መለስ «ገሪነት» እንደሆነ ጠቁመው ህዝቡ ድጋፉን እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር፡፡  

«መቼም ቢሆን አንድ ሰው ሌላኛው ሰው እንዳለ ሊተካው እንደማይችል ሁልጊዜ የሚታወቅ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን የመሰሉ በታሪክ አጋጣሚ አንዴ ጊዜ የሚፈጠሩ መሪዎችን መሰል መሪ መተካት በጣም ከባድ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር እና ጥያቄ የለውም፡፡ ነገር ግን መድረኩ እና ወቅቱ ከሚጠይቀው የአመራር ሚና አንጻር አሁን ያለው ትውልድ ይሄን አመራር መጫወት ይችላል? አይችልም? የሚል ጥያቄ ነው መመለስ አለበት፡፡ ይሄን ለማድረግ የሚችል ብቃት አለው፡፡ ይሄን ለማድረግ የሚያስችል የውስጥ አንድነት አለው፡፡ ይሄንን ለማድረግ የሚያስችል የትግል ወኔ አለው፡፡ ስለዚህም አዲሱ አመራር በዚህ ላይ ተመስርቶ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠብቀውን የአመራር ሚና ሊጫወት ይችላል የሚል ሙሉ እምነት ነው ያለን» ብለው ነበር አቶ ኃይለማርያም ፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ከዚህ ንግግራቸው በኋላ በነበሩ ሁለት ዓመታትም «የመለስ ውርስ (ሌጋሲ)» አስፈጻሚ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲያስረዱ ቆይተዋል፡፡ በ2007 ዓ.ም የተደረገውን ምርጫ ተከተሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በድጋሚ ከተሾሙ በኋላ «ከመለስ ውርስ አቀንቃኝነት» የመላቀቅ አዝማሚያ ቢታይባቸውም በመንግሥታቸውም ሆነ በሊቀመንበርነት ሲመሩት በቆዩት ገዢው ፓርቲ «የተለየ ነገር ይዘው አልመጡም» በሚል ተተችተዋል፡፡ ፕሮፌሰር መድኃኔ ከእነዚህ ወገኖች ይመደባሉ፡፡ 

«እንግዲህ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የስልጣን ዘመን በአጠቃላይ አቶ መለስ የነበሩበትን የፖለቲካ እና የፖሊሲ አቅጣጫ ባመዛኙ ይዞ የተጓዘ፣ በሰፊው ወጣ ብሎ ሳይሆን በዚያው ማዕቀፍ ውስጥ የቀጠለ፣ በድርጅቱም በመንግስትም መዋቅር፣ በአጠቃላይ የሀገሪቱ  የፖለቲካ ኢኮኖሚም ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ያለመጣ ጉዞ ነው ማለት የሚቻለው፡፡ እየለወጡ መቀጠል (change and continuity) ሳይሆን በአብዛኛው ቀጣይ ነው የነበረው፡፡ ከዚህ አንጻር የእርሳቸው የስልጣን ዘመን ብዙም እመርታ ያልታየበት፣ የሀገሪቱን ችግሮች ከመፍታት አንጻርም፣ ኢህአዴግንም ወደ አንድ አቅጣጫ አምጥቶ ገዢውን ፓርቲ ለማጠናከር ብዙ መንገድ ያልተሄደበት ሁኔታ አድርጌ ነው የማየው፡፡ ያው ውጤቱም አሁን የምናየው የሀገሪቱን ሁኔታ ይመስላል ማለት ነው» ሲሉ የእርሳቸው አመራር ያመጣውን ዳፋ ያስረዳሉ።  

የአቶ መለስን ሀሳብ አፍላቂነት በማንጸሪያነት የሚያቀርቡ ወገኖች አቶ ኃይለ ማርያምን «በዚህ ረገድ ደካማ ናቸው» ይሏቸዋል፡፡ በሀገሪቱ በተደጋጋሚ ከተፈጠሩ ችግሮች ጋር በተያያዘ እንደመለስ «ጠንካራ እና የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ደካማ ሆነዋል» ሲሉም የሚነቅፏቸው አሉ፡፡ በ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግል ያልተሳተፉት ኃይለ ማርያም በቀድሞ ታጋዮች ቁጥጥር ስር ባለው የሀገሪቱ ጦር እና የደህንነት መስሪያ ቤት ላይ ያላቸው ስልጣንን እና ተሰሚነትም ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ብዙ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መድኃኔ ግን «አቶ መለስ እና አቶ ኃይለ ማርያም ወደ አመራር የመጡበት ሁኔታ ይለያያል» ባይ ናቸው፡፡ 

«አቶ መለስ ከታሪክም፣ ከድርጅቱ ይዘውት የመጡት አብላጫ የሆነ [ቦታ] አላቸው፡፡  በተለይ ከህወሓት ክፍፍል በኋላ ሀሳብ አመንጪም እርሳቸው ናቸው፤ ideologueም እርሳቸው ናቸው፤ /ነባቤ ቃል አፍላቂም/ therorticianም እርሳቸው ናቸው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ከትጥቅ ትግሉ ጋር በተያያዘ የነበራቸው የግል ግንኙነት በመንግስታዊ መዋቅርም ከፍተኛ ተጽዕኖ ነበራቸው፡፡ በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች የfellowshiop advantage ነበራቸው፡፡

አቶ ኃይለማርያም ሲመጡ ይሄ ሁሉ አልነበራቸውም፡፡ ራሳቸው ይዘውት የመጡት ሀሳብ ማመንጨት፣ አመራር መስጠት፣ ደጋፊ ማሰባሰብ፣ ስልጣናቸውን ማጠናከር እንደ አቶ መለስ አልቻሉም፤ አልነበራቸውም፡፡ የራሳቸው ጠንካራ የሆነ የስልጣን መደላድል (constituency) ፓርቲው ውስጥም አልነበራቸውም፡፡ የመንግስት መወቅር ውስጥም አልነበራቸውም፡፡  ምናልባት ከነበራቸው የኢህአዴግ ድርጅቶች ይሁንታ ነው፡፡ ይሄ የኢህአዴግ ድርጅቶች ይሁንታ ደግሞ በኢህዴግ ድርጅቶች ውስጥ በተፈጠረው ቀውስ የተነሳ ያው እየተሸረሸረ ሄደ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ በሌለበት ሁኔታ ሲከማች የቆየ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር አንዴ ሲፈነዳ እርሳቸው መልስ ለመስጠት በሌላቸው ቦታ  ያው አልቻሉም ማለት ነው፡፡ አልሞከሩም ሳይሆን አልቻሉም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ የኃይል ሚዛኑ እና የፖለቲካ ስልጣን ክፍፍሉ እና የፓርቲው ውስጥ ችግር እርሳቸውንም ያው ስልጣናቸውን አጠናክረው፣ ሁሉን አሰባስበው አንድ ዓይነት አመራር ለመስጠት ያስቸገራቸው ይመስለኛል» ሲሉ ፕሮፌሰር መድኃኔ ይተነትናሉ። 

በኢትዮጵያ ሦስት ዓመታት ገደማ ያስቆጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ የአቶ ኃይለ ማርያም ትልቁ የአመራር ፈተና ነበር፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞው በኦሮሚያ ክልል በኅዳር 2008 ዓ.ም ሲፈነዳ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመታቸው ከጸደቀ ገና አንድ ወር ብቻ ነበር ያስቆጠረው፡፡ በርካቶች አቶ ኃይለ ማርያም ተቃውሞውን እና እርሱን ተከትሎ የመጣውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ማከናወን የሚገባቸውን አላደረጉም ይላሉ፡፡ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ጎይቶም ግን ችግሩን ያልተፈታው በእርሳቸው «የግል አመራር ብቃት ማነስ አይደለም» ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ይልቁንም ለችግሩ መባባስ የገዢው ግንባር አራት አባል ፓርቲዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

«የእርሳቸው የአመራር ድክመት አይደለም፡፡ እርሳቸው የወረሱት ሁኔታ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ኢህአዴግ የተቀባይነት (legitimacy) ችግር ነበረው፡፡ የስልጣን ክፍፍል፣ የጥቅም ክፍፍል በአራቶቹ ቡድን መካከል እና ከዚያም አልፎ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ላላቸው የንግዱ ኅብረተሰብም፣ ሌሎች ሰዎችም የዚያ ስልጣን ክፍፍል በእነርሱ ላይም ይንጸባረቅ ነበር፡፡ እና የወረሱት ነገር ነው፡፡ ለዘመናት የነበረ ግን ታፍኖ የቆየ ችግር ነበር፡፡ እርሳቸውም ደግሞ ያንን ግዙፍ የሆነ ችግር በራሳቸው መፍታት አይችሉም ነበር፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፈ ነው፡፡ ይሄ አራቱም ደርጅቶች ተሰማምተው ሊፈቱት የሚችሉት ነገር ብቻ ነው፡፡ እና አሁንም የእርሳቸው ሚና ለችግሩም መንስኤ አልነበረም፣ ለመፍትሄውም መንስኤ ሊሆን አይችልም ብዬ ነው የማስበው» ሲሉ የፖለቲካ ተንታኙ ሀሳባቸውን ይጋራሉ።

አቶ ኃይለ ማርያም የሚመሩት ገዢው ፓርቲ አንዴ «ህዝባዊ ውይይት»፣ ሌላ ጊዜ «ጥልቅ ተሃድሶ» በሚል በኢትዮጵያ ላለው ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ ለመሻት ሲሞክር ቆይቷል፡፡ በዚህ ዓመት ታህሳስ ወር ለ17 ቀናት በስብሰባ ተጠምዶ የከረመው የኢህዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም «የማያዳግም እና መሠረታዊ መፍትሄዎችን» ይዞ እንደሚመጣ ቃል ገብቶም ነበር፡፡ ፓርቲው በስብሰባው ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ «በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የኢህአዴግ አመራር ድክመት የፈጠራቸው» መሆኑን አምኗል፡፡ 

ከህዝቡም፣ ከፓርቲያቸውም አመራራቸው ጥያቄ ውስጥ የገባው አቶ ኃይለ ማርያም በቀጣዩ የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ከስልጣናቸው ሳይሰናበቱ እንደማይቀር በሹክሹክታም፣ በግልጽም ሲወራ ሰንብቷል፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ፖለቲካዊ ትንታኔዎች በመስጠት የሚታወቁት ፈረንሳዊው ሬኔ ለፎ ባለፈው የካቲት አጋማሽ ባሳተሙት አንድ ጽሑፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም በግል  ለሚቀርቧቸው ስልጣናቸውን በኢህአዴግ ጉባኤ የማስረከብ ሀሳብ እንደነበራቸው መጠቆማቸውን አትተዋል፡፡ ሆኖም ነገሮች እንደተገመቱት አልቀጠሉም፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቲት ስምንት ቀን 2010 ዓ.ም ሳይጠበቅ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ይፋ አደረጉ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ስልጣን ለመልቀቅ የወሰኑት በሀገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋት እና የፖለቲካ ችግር ለማስወገድ ለሚወሰዱ ማሻሻያዎች «የመፍትሔው አካል ለመሆን» በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሬኔ ለፎ ግን የተለየ ሀሳብ አላቸው፡፡ «ኢትዮጵያ በአስርት ዓመታት ውስጥ አጋጥሟት የማታውቀውን ማዕበል ለማሻገር የመርከብ አዛዥነት ስልጣኑ የነበራቸው ኃይለ ማርያም ምናልባትም መርከቧ ብትገለበጥ ለሚፈጠረው ሁነት ተጠያቂ ላለመሆን በመሻት ነው» ሲሉ ጽፈዋል፡፡ «የእርሳቸው ስልጣን መልቀቅ የገዢው ፓርቲን ማምለጫ አሳጥቶት ከማዕበሉ የሚወጣበትን መፍትሔ እንዲሻ ለማድረግ ተስፋ አድርገውም ይሆናል» ሲሉ ሌላኛውን ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ፈረንሳዊው የፖለቲካ ተንታኝ በዚሁ ጽሑፋቸው የገዢው ግንባር አባል ፓርቲዎችን «የተለያዩ፣ የተከፋፈሉ እና ለመታዘዝ አሻፈረኝ» ያሉ ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ተንታኞችም አቶ ኃይለ ማርያም ለአመራራቸው ስኬት የተማመኑበት የፓርቲያቸው «የውስጥ አንድነት» መጥፋቱ ለስልጣናቸው ዋነኛ ተግዳሮት እንደነበር ይስማማሉ፡፡ ፕሮፌሰር መድኃኔ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መልቀቅ «የብዙ ነገር ድምር ውጤት ነው» ይላሉ፡፡  

«በአንድ በኩል ኢህአዴግ ውስጥ ያለ ችግር አለ፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ዝግ እየሆነ ሌሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በታደከሙበት ሁኔታ የህዝቡን ስሜት እና ፍላጎት ለማንጸባረቅ የኢህአዴግ ድርጅቶች ናቸው እንግዲህ ወኪል (agent) የሆኑት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ የኢህአዴግ ድርጅቶች ካላቸው ሽኩቻ በተጨማሪ የህዝቡን ፍላጎት፣ የህዝቡንም ስሜት በሌላ መልኩ ሊገለጽ ስለማይችል በኢህአዴግ ድርጅቶች በኩል መገለጽ በመጀመሩ ሽኩቻውንም ያው አባባሰው ማለት ነው፡፡ የእርሳቸውንም ስልጣን ጥያቄ ውስጥ አስገባው፡፡ በዚህ በተዳከመ ሁኔታ ያው ለመልቀቅ ወሰኑ ማለት ነው» መድኃኔ ፡፡

«አቶ ኃይለ ማርያም የነበሩባቸው ችግሮች ዛሬ ስልጣኑን ከእርሳቸው ወደ ተረከቡት ዶ/ር አብይ አህመድ መንከባለሉ ካልቀረ በኢትዮጵያ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ወይ?» የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መድኃኔ ሁለቱን መሪዎች በማነጻጸር ምላሽ ይሰጣሉ፡፡  

«የአቶ ኃይለ ማርያም የስልጣን መሠረት (powerbase) እና አሁን የተመረጠው መሪ ከስፋቱም ከጥልቀቱም አንጻር የተለያየ ነው፡፡ እርሳቸው በነበረው እየተዳከመ፣ እየተከፋፈለ፣ የኃይል ሚዛኑ እየተበወዘ በመጣው ድርጅት በዚያ ላይ ደግሞ የራሳቸው ጠንካራ የሆነ የስልጣን መሰረት ሳይዙ ነው ባዶ ቦታ ውስጥ የገቡት፡፡ አሁን የሚመጣው በኢህአዴግ ሽኩቻ ውስጥ ወደፊት ተስፈንጥሮ የመጣ፣ በኢህአዴግ ውስጥም ቢሆን ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥም ቢሆን ጠንካራ የሆነ ቡድን እና መሠረት ያለው ኃይል ነው፡፡ ስለዚህ ስፋቱም ጥልቀቱም ይለያያል፡፡ ይሄ ከመንግሥት መዋቅር ጋር እንዴት ይተያያል? እንዴት ይደራደራል? እንዴት ራሱን፣ ሀሳቦቹን፣ የፖለቲካ ስልጣኑን ወደ መንግሥት መዋቅሮች እያዛመተ በሀገሪቱ መረጋጋት እና የሽግግር ለውጥ ያመጣል? የሚለው እንግዲህ የሚታየው ነው የሚሆነው» ሲሉ ፕሮፌሰር መድኃኔ ያጠቃልላሉ።

ተስፋለም ወልደየስ 

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic