የቻድ ፕሬዚደንት እና የገጠማቸው ተቃውሞ | አፍሪቃ | DW | 27.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የቻድ ፕሬዚደንት እና የገጠማቸው ተቃውሞ

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የቻድ ዜጎች የሀገሪቱ መንግሥት የሚከተለውን የጭቆና አገዛዝ በመቃወም ሰሞኑን አደባባይ መውጣቱ ይታወሳል። የሙያ ማህበራት እና በርካታ የሲቭል ማህበረሰብ ቡድኖች ባለፈው ረቡዕ በጠሩት ጠቅላላ የስራ ማቆም አድማ የመዲናይቱ ንጃሜና እንቅስቃሴ ከሞላ ጎደል ተስተጓጉሎ ውሎዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:40
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:40 ደቂቃ

ቻድ

በመዲናይቱ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ተቃውሞውን ያሰማው ሕዝብ የፊታችን ሚያዝያ በሚደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ ለአምስተኛ ጊዜ መወዳደር የሚፈልጉት ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ጠይቋል። ዴቢ የፕሬዚደንቱን የስልጣን ዘመን በሁለት በሚገድበው የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ ያስደረጉት ገና እጎአ በ2004 ዓም ነበር።

በፕሬዚደንት ዴቢ ላይ ግፊት ለማሳረፍ የተደረገው ተቃውሞ እንዳሰቡት መካሄዱን «በቃ» የሚል መፈከሪያ የያዘው የቻድ ተቃዋሚ ቡድን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሊግ ጭምር የሚጠቃለልበት የሲቭል ማህበረሰብ ቡድን እና የቻድ የሙያ ማህበራት ህብረት ቃል አቀባይ ማሃማት ኑር ኢቤዱ ገልጸዋል።

« የተቃውሞውን ጥሪ ሰምቶ አደባባይ የወጣው ሕዝብ ከጠበቅነው በላይ ነበር። በሁለተኛዋ ትልቋ የቻድ ከተማ ሙንዱ ለምሳሌ « ከተማዋን በድን እናድርጋት » የሚል መፈክር የያዘውን የስራ ማቆም አድማ ጥሪ ሕዝቡ መቶ ከመቶ በመከተሉ አንድም እንቅስቃሴ አልነበረም። የፀጥታ ኃይላት ተቃዋሚዎች በስራ ማቆሙ አድማ እንዳይሳተፉ ለማከላከል የሚያደርጉት ወከባ እና የማስፈራራት ዛቻ ተግባር ከከተሞች ይበልጥ በገጠሩ ቢብስም፣ በደቡቡ፣ ምሥራቅ እና ማዕከላይ ቻድ የሕዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር። »

ኑር ኢቤድ እንዳስረዱት፣ የተቃውሞው መሳካት ሕዝቡ ምን ያህል በዴቢ አገዛዝ መሰላቸቱን እና ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን የመወዳደር እቅዳቸውን ለማከላከል፣ እንዲሁም፣ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለማስከበር ቆርጦ መነሳቱን አሳይቶዋል። በሀገሪቱ ካለፈው ሳምንት ወዲህ ተቃውሞ ከቀጠለ በኋላ፣ ወታደሮች ባለፈው ሰኞ ቁጣቸው ገንፍሎ አደባባይ የወጡትን ተቃውሞ ሰልፈኞችን ለመበተን ያደረጉት ሙከራ ሳይሰራ ሲቀር በከፈቱት ተኩስ አንድ የ17 ዓመት ተማሪ መግደላቸው እና አምስት ማቁሰላቸው ተሰምቶዋል። ይህንኑ ተቃውሞ የቀሰቀሰው አንዲት ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ በተወዳዳሪነት ይቀርባሉ የተባሉ የተቃዋሚው ቡድን አባል ልጅ የሆነች አንዲት የ16 ዓመት ተማሪ ከጥቂት ቀናት በፊት በብዙ ወንዶች የተደፈረችበት እኩይ ተግባር ነበር። ወንጀሉን ከፈፀሙት መካከል የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ልጅ እና ሶስት የከፍተኛ ጀነራሎች ልጆችም ይገኙባቸዋል። ድርጊቱን የሚያሳይ በእጅ ስልክ የተቀረፀ ስዕል በኢንተርኔት በወጣበት ጊዜ ነበር በመላይቱ ቻድ ተማሪዎች አደባባይ የወጡት። ወንጀሉን ፈፀሙ የተባሉት ግለሰቦች በቁጥጥር እንደዋሉ እና ዓቃቤ ሕግም ክስ እንደሚመሰርት ቢሰማም፣ እንደ ማህማት ኑር ኢቤዱ ገለጻ፣ የቻድ ሕዝብ ቁጣ ገና አልበረደም።

በቻድ መንግሥት ቃል አቀባይ ሙስጠፋ አሊ አሊፌይ በሰጡት መግለጫ፣ መንግሥት ቀደም ሲል ያሳለፈውን ተቃውሞ ሰልፍ ማድረግን መከልከሉን በማስታወስ፣ ተቃውሞውን እና የስራ ማቆሙን አድማ ሕገ ወጥ ብለውታል።

« ከተማዋን በድን እናድርጋት » የሚል መፈክር የያዘውን የስራ ማቆም አድማ መጥራት ትክክለኛ አይደለም፣ ምክንያቱም ፣ በሀገሪቱ መንግሥት እይታ መሰረት፣ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር እና ሕገ ወጥ ርምጃ ነው። የሲቭሉ ማህበረሰብ ሚና ውይይትን ማበረታት እና ተራርቀው የሚገኙ የተቀናቃኞቹን አቋሞች ማቀራረብ ነው። ሕዝብን ለዓመፅ መቀስቀስ የለበትም።» ዴቢ ስልጣን ከያዙበት ከ1990 ወዲህ በሀገሪቱ የዘፈቀደ እስራት፣ የቁም ስቅል፣ በተቃዋሚዎች ላይ ዛቻ እና ወከባ ቀጥሎዋል፣ መሰረታዊ ነፃነቶች ተነፍገዋል። ስር የሰደደ ሙስና፣ የተበላሸ አስተዳደር እና ድህነት ተስፋፍቶዋል።

የአፍሪቃ ህብረት ባለፈው ጥር ባካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢን በዙር የሚደርሰውን የህብረቱን ሊቀ መንበርነት ስልጣን በሰጠበት ጊዜ ግራ የተጋቡት የመብት ተሟጋቾች ርምጃውን ተስፋ አስቆራጭ ማለታቸው አይዘነጋም።
የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፣ የቻድ ፕሬዚደንት ለአምስተኛ ጊዜ ለመወዳደር የያዙትን እቅድ ፣ በተወሰኑ ሀገራት ላይ መሪዎች እንደሚያደርገው፣ በግልጽ በመቃወም አስተያየት ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቅም። ምክንያቱም፣ በናይጀሪያ በሚንቀሳቀሰው እና በጎረቤቶችዋ ሀገራትም ጭምር ጥቃት በሚጥለው አሸባሪ ቡድን ቦኮ ሀራም አንፃር ለሚካሂደው ትግል ፕሬዚደንት ዴቢን አጋር አድርጎ ይዞዋል። እንዲያውም፣ ዴቢ የአፍሪቃ ህብረትን የሊቀመንበርነት ስልጣን የተረከቡበትን ርምጃ ምክንያት በማድረግ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በጻፉት መልዕክታቸው፣ « ይህንኑ ስልጣን የተረከቡበት ጊዜ አዳጋች ነው። አህጉሮቻችን ሽብርተኝነትን የመታገል፣ በስደት እና ሕገ ወጥ ፍልሰት መንስዔዎች ሰበብ የሚፈጠሩ ቀውሶችን እና ውዝግቦችን የማስወገድ ዓቢይ ስራ ይጠብቃቸዋል። » ባሉበት አነጋገራቸው የዴቢን አጋርነት አረጋግጠዋል።

ዩኤስ አሜሪካ እና ፈረንሳይ ደግሞ ከዚህ ራቅ ብለው በመሄድ አክራሪነትን በመታገሉ ረገድ ቻድ ቀዳሚውን ስፍራ መያዟን ገልጸዋል። ዩኤስ አሜሪካ በዚህ ሳምንት ከዚችው የማዕከላይ አፍሪቃ ሀገር ጋር የሶስት ሳምንት ዓለም አቀፍ የጦር ልምምድ እንደምትጀምር ዜና ምንጮች አመልክተዋል።

ያም ቢሆን ግን፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እምብዛም ተቃውሞ የማይካሄድባት በነበረችው ቻድ ሁኔታዎች እየተለወጡ መምጣታቸውን የቻድ ሕዝብ ሰሞኑን በብዛት በመውጣት በፕሬዚደንቱ አለመደሰቱን በግልጽ ያሳየበት ርምጃው ምስክር መሆኑን ከጥቂት ጊዜ በፊት ቻድን ጎብኝተው የተመለሱት « ብሮት ፊውር ዲ ቬልት» የተባለው የጀርመናውያኑ ግብረ ሰናይ ድርጅት ባልደረባ ሀይደ ቬጋት አስታውቀዋል። ቬጋት ከቻድ የመብት ተሟጋቹ ሊጋ ባልደረቦች ጋር ባካሄዱት ውይይት በመንግሥት አንፃር ተቃውሞ ያሰሙት ጥቂቶች ብቻ እንደነበሩ ነው የሰሙት።

« አሁን የሚደርሱኝ መልዕክቶች ግን ተስፋ የሰነቁ ናቸው፣ ሕዝቡም ለውጥ ለማስገኘት የሚችልበትን ርምጃ ለማንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። » ይሁንና፣ የሀገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ ትልቁ ኃላፊነቱ መሆኑን በየጊዜው የሚገልጸው የቻድ መንግሥት የመብት ተሟጋቾች እና ሕዝቡ ለሚያሰሙት ቅሬታ ደንታ መስጠቱ አጠያያቂ ነው። ሆኖም፣ የሚያዝያው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በትክክል ከተካሄደ ለውጥ ሊገን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኙ አህማት ማሀማት ሀሰን፣ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

«በቃ» የሚለው መፈክር የቻድን ሕዝብ ቅሬታ በግልጽ ያሳያል። እና ምርጫው ግልጽ የሚሆን ከሆነ፣ መራጩ ህዝብ በዴቢ አንፃር ድምፁን መስጠቱ አይቀርም። »

ቢርጊት ሞርገንራት/አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic