የቻይና ግዙፍ የዉኃ ግድብ ግንባታ | ኤኮኖሚ | DW | 05.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የቻይና ግዙፍ የዉኃ ግድብ ግንባታ

በቻይና የመጠጥ ዉኃ ምንጭ በደንብ በተመጣጠነ ሁኔታ ለኅብረተሰቡ አልተከፋፈለም። በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ከሚገኘዉ የመጠጥ ዉኃ አገልግሎት ይልቅ በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል በብዛት ተዳርሷል።

በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚታየዉን የዉኃ እጥረት በማሰብ 1000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘዉ ከያንግትስ ወንዝ በቅርብ ቀን ዉስጥ ዉኃ ተጠለፎ የሚተላለፍበት መስመር ዝርጋታ ተጠናቆአል። ይህ በዓለም እጅግ ግዙፍ እንደሆነ የተነገረለት የዉኃ ጠለፋ ፕሮጀክት ግዙፍ ግድብ፣ እጅግ ከፍተኛ ቱቦዎች እና ግዙፍ የዉኃ መምጠጫ ማሽኖችም አሉት። ወጭዉ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ የተነገረለት ይህ ግዙፍ ፕሮዤ ማኅበራዊና የአካባቢ ተፈጥሮን ሁኔታ ያላጤነ በመሆኑ አወዛጋቢ ሆንዋል። በግድቡ ግንባታ ምክንያትም በሽዎች የሚቆጠሩ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ቀያቸዉን እንዲለቁ ተገደዋል። ግድቡ እጅግ ግዙፍ ቢሆንም ለሰሜን ቻይና የዉኃ እጥረት መፍትሄ የማስገኘቱ ነገርም ዉሱን ነዉ እየተባለ ነዉ።
ኑያዙንግ አዉራጃ አጠገብ ዳሱን ገጠር የተገነባዉ ግዙፍ የዉኃ ማስተላለፍያ ግድብ አካባቢ አዛዉንት ገበሬዎች ቁጢጥ ብለዉ ከማሳ ላይ ቆስጣ ይቆርጣሉ። የራሳቸዉን መሬት በማጣታቸዉ የግብርና ተግባራቸዉን አቁመዉ ተቀጣሪ ሆነዋል። በእርሻ ቦታቸዉ ላይ መንግሥታቸዉ ከምንም በላይ የሚሊዮኖች መኖሪያ ወደሆነችዉ ቤጂንግ ዉኃ ለማድረስ ያለመዉን ግዙፉን የደቡብ- ሰሜን የዉኃ ግድብ ማስተላለፍያ ገንብቶበታል። የዳሱን ገጠር ነዋሪ የሆኑት አዛዉንቷ ሱይ እጅግ ተበሳጭተዋል፤
«ከዚህ ምንም ያገኘነዉ ጥቅም የለም። መሬታችን ተወሰደብን፤ ካሳ ተብሎ የተሰጠንም እጅግ ጥቂት ነዉ። በምን ልንኖር ነዉ? ከተገነባዉ ግድብ ዉኃን መጠቀም አይፈቀድልንም፤ የታቀደዉ ለፔኪንግ ነዉ። ስለዚህ የምንጠጣዉን ዉኃ ከጉድጓድ እየሳብን ነዉ የምጠቀመዉ» c


አዛዉንቷ ሱይ ያሰሙትን አይነት ቅሬታ የዉኃ ግድቡ በአለበት አካባቢ ሁሉ ይሰማል። የዉኃዉን በረከት ለሁሉም ለማዳረስ ተብሎ ከረዥም ርቀት ዉኃዉ ቢጠለፍም በአካባቢዉ የሚታየዉ የመጠጥ ዉኃ ስርጭት አሁንም ተመጣጣኝ አይደለም። በ20ኛዉ ክፍለ ዘመን የሕዝባዊት ቻይና የኮሚኒስት ፓርቲ መሪ የነበሩት ማኦ ሴቱንግ ከደቡብ ቻይና የዉኃ ጥማት ወደሚያጠቃዉና ወደ ደረቀዉ ሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ዉኃ ማስተላለፍያ መስመር ዘርግቶ የማረስረሱን ሃሳብ በአንድ ወቅት አልመዉት ነበር።
ይህን እዉን ለማድረግ ዉኃዉን የሚገፉ ማሽኖችን ተክሎ ማስተላለፍያ ባንቧዎችን ለመግጠም 12 ዓመታት ፈጅቶአል። በግንባታዉ ወቅትም 300,000 በላይ የአካባቢዉ ነዋሪ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎአል። የዚህ የዉኃ ፕሮዤ ጠቅላላ ወጭ 50 ቢሊዮን ይሮ እንደሆነም ይገመታል። የግድቡ ግንባታ ሥራ በአሁኑ ግዜ ቢጠናቀቅም፤ የዉኃ ማስተላለፍያዉ ግዙፍ ግድብ ጥቅምና ጉዳት አሁንም የመነጋገርያ ርዕስ ነዉ።
« የወጣዉን ወጭ ያየን እንደሆነ ለፔኪንግ የዉኃዉ ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የነዋሪዎች መፈናቀላቸዉ፤ ለዚሁ ግድብ የተገነባዉ ድልድይና የዉኃ መስመር ግንባት ሁሉ አለበት። ግዙፉ ፕሮዤ የሃገሪቱን ኤኮኖሚ ከፍ እንደሚያደርግ፤ ዉኃ የሚያገኙትም ከተሞች እንደሚጠቀሙ እሙን ነዉ። በሌላ በኩል በገጠር ነዋሪ የሆኑት ማኅበረሰቦች ከዉኃዉ የሚያገኙት ሲሶዉን ብቻ ነዉ»
ይላሉ « ንፁህ ዉኃ» የተሰኘዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ ጊዎ ዞንግ። በሄባይ የሚገኙ ገበሬዎች ደግሞ ምንም የሚያገኙት ነገር የላቸዉም። አዲሱ የዉኃ ማስተላለፍያ ቱቦ ሄባይ አዉራጃን የሚያልፈዉ እንደአዉራ ጎዳና በዘረጋ በሲሚንቶ የተለሰነ የዉኃ ማስተላለፍያ ተሸፍኖ ነዉ። 1400 ኪሎ ሜትር ርቀት ወደ ፔኪንግ የሚፈሰዉ የዉኃ ማስተላለፍያ መስመር ያለማቋረጥ አቅጣጫዉን ይዞ ሸለቆዉን አቋርጦ ይፈሳል።

China Überschwemmungen in Nordchina Flash-Galerie


ሄባይ የሚገኙ ገበሬዎች የእርሻ ቦታዎቻቸዉ ዉኃን ሲሻ በፔኪንግና አካባቢዋ ያለዉ የዉኃ እጥረት አንድ ሶስተኛዉ በዚህ በአዲሱ የዉኃ ማስተላለፍያ ፕሮዤ ተቀርፎአል። በቋፍ ለሚገኘዉ የቻይና የአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታ ግን ይህ ፕሮዤ አስተማማኝ ያልሆነና አደጋ ያለዉ ነዉ ሲሉ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ባለሞያዎች ይናገራሉ። በተቀላጠፈ አሰራር የዉኃ እጥረትን ለመግታትና የተጠቃሚን ፍላጎት ለሟሟላት በዚህ ፕሮዤ የተሰራዉ ሥራ እጅግ ጥቂት መሆኑም ተገልጾአል። ቻይና ዉስጥ በኢንዱስትሪ ጥቅም ላይ የሚዉለዉ የዉኃ መጠን ሌሎች በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሃገራት ከሚጠቀሙበት የዉኃ መጠን በአስር እጥፍ ይበልጣል። በዚህም ይላሉ ምሁራን ፔኪንግ ከዓመታት በኃላ ሌላ የዉኃ ምንጭን መፈለግ ይኖርባታል። ለዚህም ሌላ እቅድ ተይዟል ከቲቤት ተራራማ አካባቢዎች ወደፔኪንግ የዉኃ መስመር ለመዘርጋት። ይህም በግዙፍነቱ በዓለም ተወዳዳሪ የሌለዉ መሆኑ ከተገለጸዉ የዉኃ ማስተላለፍያ ግድብ የሚበልጥ እንደሚሆንም ተጠቅሶአል።
ሩት ኪርሽን / አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic