የቻይና የንግድ እንቅስቃሴ በአፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 01.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የቻይና የንግድ እንቅስቃሴ በአፍሪቃ

ቻይና በአፍሪቃ የምታደርገው እንቅስቃሴ መጠን እስካሁን ድረስ ይገመት ከነበረው በላይ መሆኑን አንድ ጥናት አሳየ። ጥናቱን ያካሄደው ማኪንዜ አፍሪቃ የተባለው አማካሪ ተቋም ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:03

«ከ10,000 የሚበልጡ የቻይና ተቋማት አፍሪቃ ውስጥ ይሰራሉ።»


ቻይና በአፍሪቃ የምታደርገው እንቅስቃሴ መጠን እስካሁን ድረስ ይገመት ከነበረው በላይ መሆኑን አንድ ጥናት አሳየ። ጥናቱን ያካሄደው ማኪንዜ አፍሪቃ የተባለው አማካሪ ተቋም ነው።  በቻይና እና በአፍሪቃ መካከል ያለውን የኤኮኖሚ ግንኙነት በተመለከተ በአህጉሩ ከሰሀራ በስተደቡብ የአፍሪቃ ሀገራት ውስጥ ካሉ  ከ100 የሚበልጡ አፍሪቃውያን ባለተቋማት፣ የመንግሥታት መሪዎች እና በአፍሪቃ ከሚገኙ ዪ,ቻይና ባለተቋም ስራ አስኪያጆች ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስን መሰረት አድርጎ  የተዘጋጀው ጥናት፣ ቻይና በአፍሪቃ የምታሰራው ወረትም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ በሶስት እጥፍ ከፍ እንደሚል ጠቁሟል።  በአፍሪቃ እና በቻይና መካከል ግንኙነቱ ባለፈው አሰርተ ዓመት በጉልህ አድጎ፣ የንግዱ ግንኙነትም በያመቱ በ20% እየጨመረ መምጣቱን የማኪንዜ አፍሪቃ ተቋም ሸሪክ ኦሚድ ካሲሪ ገልጸዋል።
« ከ10,000 የሚበልጡ የቻይና ተቋማት አፍሪቃ ውስጥ ይሰራሉ። ይህም እስካሁን ይገመት ከነበረው በአራት እጥፍ ከፍ ያለ ነው። ከነዚህ ተቋማትም መካከል 90% የግል ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ አንድ ሶስተኛው በማንዩፋክቸርኒንግ  ዘርፍ ነው የተሰማሩት።  »

Omid Kassiri ist Partner bei McKinsey & Company

ኦሚድ ካሲሬ


እነዚህ ተቋማት በተለያዩ ዘርፎች፣ ማለትም፣ በንግዱ፣ በኢንቬስትመንት፣ በመሰረተ ልማት ፣ በፊናንስ እና ማዕድን በማውጣቱ ዘርፎች  የሚሰሩ ከትንሽ እስከ ትልቅ የሚባሉ ናቸው። ለምጣኔ ሀብት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚዘግበው እና ከአፍሪክ አዚ መጽሄት ጋር የሚተባበረው   ጋዜጠኛው ፍሯንስዋ ሚሴ በማዕድን ማውጣቱ ዘርፍ ላይ  ቻይና እንዴት ምዕራባውያቱን ሀገራት እንደተካች ያስታውሳል።  
« ቻይና ለኮንጎ የመጀመሪያዋ ዕቃ አቅራቢ፣ የመጀመሪያዋ ውዒሎተ ንዋይ አፍሳሽ እና ማዕድንን በንግድ ወደ ሀገሯ የምታስገባ የመጀመሪያዋ ሀገር ናት።  ቻይናውያኑ ተቋማት በኮንጎ  ማዕድኖቹን መዳብ፣ ኮባልትን  በማውጣቱ ስራ ላይ ተሰማርተዋል። ቻይና በጊኒ ማዕድን ማውጣት ፕሮዤዎች ላይ የመሰማራት ፍላጎት አላት። በዚህ ዘርፍ  በመሰማራቱ ላይ አውሮጳውያንን ቀድማለች። የአሜሪካውያን እና የአውስትሬሊያ ተቋማትንም ተክታለች። ለምሳሌ። በዓለም ትልቅ ከሚባሉት ፕሮዤዎች መካከል አንዱ የሆነው በካታንጋ  ግዛት የሚገኘው የሺንኮሎብዌ ማዕድን ይጠቀሳል። እንደሚታወቀው ፣ በሂሮሺማ ፣ ጃፓን ከተማ የተጣለውን የአቶም ቦምብ ለመስራት ያስፈለገው ማዕድኑ ዩሬንየም የወጣው ከዚሁ ማዕድን ቦታ ነው። እና ቻይና ባለፈው ዓመት የዚሁ ማዕድን ዋነኛ ሸሪክ  ሆናለች። ይህ እንግዲህ ካሉት ብዙ ምሳሌዎች አንዱ ነው። »
በምዕራናዊ ኮንጎ በቻይናውያን የሚገነባው የኢንጋ ግድብ በሚያበቃበት ጊዜ 40,000 ሜጋ ዋት ኮሬንቲ እንደሚያመርት እና ግማሹን የአፍሪቃ የኮሬንቲ ፍላጎት ሊሸፍን እንደሚችል ይጠበቃል። 

Kongo Inga-Damm

የኢንጋ ግድብ


የማኪንዜ አፍሪቃ ተቋም ሸሪክ ኦሚድ ካሲሬ እንዳመለከቱት፣ በአፍሪቃ የቻይና እንቅስቃሴ መጉላቱ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው።
« የአፍሪቃን ልማት ለማሳደግ  ፣ የስራ ቦታ ፈጠራን፣ የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ዝውውርን ያበረታታል። በአሁኑ ጊዜ የንግዱ እንቅስቃሴ ወደ 180 ቢልዮን ዶላር ይደርሳል፣ በ2025 ወደ 440 ቢልዮን ከፍ ሊል እንደሚችል እናምናለን። »
በምዕራባውያት ሀገር  አንጻር ፔኪንግ በኤኮኖሚ፣ ንግድ እና ፊናንስ ዘርፍ  ግንኙነት በምትገናኛቸው አፍሪቃውያት ሀገራት ላይ፣ የሰብዓዊ መብት እንዲያከብሩም ሆነ ስርዓተ ዴሞክራሲ እንዲተክሉ አንዳችም  ቅድመ ግዴታ አታሳርፍም።  ይህ የቻይና አሰራር፣ ይላሉ  የፖለቲካ ተንታኙ ሴኔጋላዊው ሙሳ ዲያውን፣ ያን ያህል አያስጨንቅም።
« ባንዳንድ ቦታዎች/አካባቢዎች ላይ ቻይናውያን ቅድመ ግዴታ የሚያሳርፉት ፣ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ  አስፈላጊ ከሆነ ብቻ ነው የሚያደርጉት።  ተፃራሪ ውጤት የሚያስገኝ ለይስሙላ የሚደረግ ስርዓተ ዴሞክራሲ በመፍጠር ፈንታ የሕዝቦችን ኑሮ ማሻሻል የሚያስችሉ ተጨባጭ ርምጃዎች መውሰዱ ነው ዋነኛው ጉዳይ መሆን ያለበት።  ሁኔታዎችን ስንመለከት፣ በአፍሪቃ የዴሞክራሲ ሂደንትን ስንመረምር ቻይና በተቋሞችዋ አማካኝነት ፣ በምታደርገው ትብብር  ለአፍሪቃ ልማት ድርሻ  እያበረከተች ነው። »
 እንደ ኦሚድ ካሲሪ፣ ቻይና ትልቋ የኤኮኖሚ አጋሯ መሆንዋን የሚገነዘቡት  አፍሪቃ ሀገራት  ከቻይና ጋር ያለው ግንኙነት አስገኘው የሚባለውን አዎንታዊ ውጤት እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችላቸው እቅድ መንደፍ ያሻቸዋል።   
« ጥናቱ በተካሄደባቸው ስምንት ሀገራት መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው ከቻይና ጋር ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት የሚያግዝ የቻይና ስልት እያወጡ ያሉት። ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ሌላዋ ደቡብ አፍሪቃ ናት። ሌሎቹ ሀገራት ይህ ነው የሚባል ስልት አላወጡም፣ ግን ፣ ለምሳሌ ኢንዱስትሪያዊነትን ለማሳደግ  በመሰረተ ልማቱ ግንባታ ላይ ከቻይናውያን ጋር መስራት የሚችሉበት ስልት ማውጣት ይኖርባቸዋል። ይህ ከቻይናውያኑ ጋር በርዳታ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገርም ይረዳቸዋል።  »

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች