የቻይና እና የአፍሪቃ የትብብር ጉባዔ በጆሀንስበርግ | አፍሪቃ | DW | 05.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የቻይና እና የአፍሪቃ የትብብር ጉባዔ በጆሀንስበርግ

በደቡብ አፍሪቃ የጆሀንስበርግ ከተማ የተካሄደው የሁለት ቀናት የቻይና አፍሪቃ ትብብር ጉባዔ ዛሬ ተጠናቀቀ። በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች የተካፈሉበት እና በአፍሪቃ ምድር የተካሄደው የመጀመሪያው ጉባዔው በተለይ ያጎላው አፍሪቃ እና ቻይና ባንድነት ያድጋሉ፣ ብሎም፣ ለጋራ ልማት ሁለቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲ የሚለውን ሀሳብ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:43
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:43 ደቂቃ

የትብብር ጉባዔ በጆሀንስበርግ

የውይይቱን መድረክ ከደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ጎን በተባባሪ ሊቀ መንበርነት የመሩት የሚፈልጉት የቻይና ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግ ከአፍሪቃ ጋር በእኩልነት የተመሰረተ ግንኙነት መፍጠር የሚያስችል ያሉትን ባለ አስር ነጥብ የልማት እቅድ አቅርበዋል። ጉባዔው ይህንኑ የጆሀንስበርግ መግለጫ የሚሰኘውን የድርጊት መርሀግብርን አፀድቋል። ይህንንም እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ሃገራቸው በአፍሪቃ ልማትን ለማራመድ በሶስት ዓመት ውስጥ 60 ቢልዮን ዶላር እንደምትሰጥ ቻይናዊው ፕሬዚደንት አስታውቀዋል። « በመካከላችን በቅርብ ተባብረን በከፍተኛ ደረጃ የምናደርገውን ልውውጥ፣ የአስተዳደር ተሞክሮዎችን የማካፈሉን አሰራር ማጠናከር ፣ እንዲሁም፣ አሳሳቢ በምንላቸው ጉዳዮች ላይ ተግባብቶ እና ተደጋግፎ መስራት ይገባናል። » እንደ ዢ ጂንፒንግ አስተያየት ያልተሟላ መሰረተ ልማት፣ የሰለጠነ የሰራተኛ ኃይል እና የገንዘብ እጥረት የአፍሪቃን ልማት ወደኋላ እየጎተተው ነው።

ከገንዘቡ መካከል አምስቱ ቢልዮን በርዳታ የሚሰጥ ይሆናል። ባለአስር ነጥቡ እቅድ የኢንዱስትሪ ፕሮዤዎችን፣ ኢንቬስትመንትን፣ ስልጠናዎችን እና የግብርናውን ዘርፍ ዘመናይ ማድረግን ያጠቃልላል። ቻይና የአፍሪቃን ልማት ሂደት ለማፋጠን በባቡር ሀዲድ፣ በመንገድ፣ በአየር ማረፊያ፣ በወደቦች ግንባታ፣ በኮሬንቲ እና የስልክ መስመሮችን በማስፋፋቱ ዘርፎችላይ ወረቷን እንደምታሰራ ነው በጉባዔው የተገለጸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው አዳጋቹ የኤኮኖሚ ቀውስ የአፍሪቃን የንግድ እንቅስቃሴ እና ወደአህጉሩ ሊገባ በሚችለው ወረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ መሆኑን የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ዙማ ገአስታውቀዋል። ይሁንና፣ 1,1 ቢልዮን ሕዝብ ያላት እና ትልቅ ገበያ ልትሆን የምትችለው አፍሪቃ እነዚህን ችግሮች በሕዝቧ ኃይል ልትወጣ እንደምትችል ተሳፋቸውን ገልጸዋል።

የውይይቱ መድረክ ቻይና እና የአፍሪቃ ሃገራት ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ ቆርጠው መነሳታቸውን ያሳየ መሆኑን በጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የዴሞክራሲ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ጌድዮን ቺታንጋ ገልጸዋል። ብዙዎቹ አፍሪቃውያት ሃገራት በቅኝ አገዛዝ ስር በነበሩበት ጊዜ ከቻይና ድጋፍ ያገኙበትን ዘመን ያስታውሳሉ። « እነዚህን ግንኙነት መልሶ ለማደስ እና 54 ቱን የአፍሪቃ ሃገራት እና በተለይም ቻይናን ተጠቃሚ ወደሚያደርግ ይፋ ተጨባጭ ዲፕሎማቲክ ፣ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ግንኙነት ለመቀየር መግባባቱ እና ፍላጎቱ አለ። »

ይሁንና፣ የቻይና ዓላማ በአፍሪቃውያን ዘንድ አዎንታዊ እና አሉታዊ አስተያየት ነው ያስከተለው። አፍሪቃውያን መሪዎች ከቻይና ጋር የሚያደርጉዋቸው ውሎች ላይ ያረፉትን ቅድመ ግዴታዎች በጥንቃቄ ሊመለከቱዋቸው እንደሚገባ አንዷ የዚምባብዌ ተወላጅ አስጠንቅቀዋል።« ገንዘብ በርዳታ ሰጥተናል ወይም ገንዘባችንን በሃገራችሁ አሰርተናል፣ ባለ ወረቶቹም እኛ በመሆናችን የምንላችሁን ስሙ ዓይነት አሰራር የታከለበት አሳሳቢ ሁኔታ ይታያል። »

አንዱ ደቡብ አፍሪቃዊ ግን ቀደም ሲል አስተያያት ባቀረቡት ተናጋሪ አንፃር ቻይና አፍሪቃን ከድህነት ለማላቀቅ ቀና ጥረቶችን አነቃቅታለች ባይ ነው።« የራሳችንን ጥቅም ማስጠበቅ ቅኝ አገዛዝ ማለት አይደለም። ሌሎች ይህ የቅኝ አገዛዝ ዓይነት ነው ብለው ሊያስቡ ይችሉ ይሆናል። ግን፣ ቻይናውያኑ ምን ይዘው ነው የሚመጡት የሚለው የራሳችን ጥያቄ ካልሆነ በስተቀር።ከማንም ግዴታ አላረፈብንም። »

ቻይና የአፍሪቃ ትልቋ የንግድ አጋር ስትሆን፣ በአፍሪቃ አህጉር እና በቻይን መካከል የተደረገው የንግድ ግንኙነት በጎርጎሪዮሳዊው 2014 ዓም የንግዱ መጠን 220 ቢልዮን ዶላር ነበር። የቻይና የአፍሪቃ ፖሊሲ በአህጉሩ እጅግ ብዙ ወረት በማሰራት በተለይ በልማቱ ዘርፍ ውስጥ ሰፊ የኤኮኖሚ ጥቅም ማግኘት የተሰኘ መሆኑን በደቡብ አፍሪቃ የስቴልንቦሽ ዩኒቨርሲቲ፣ የቻይና ጥናት ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሮስ አንተኒ ለዶይቸ ቬለ አስረድተዋል።

« ቻይና በአፍሪቃ፣ ከዚያም አልፎ በአዳጊው ዓለም ውስጥ የረጅም ጊዜ ፍላጎት ያላት ይመስለኛል። የሃገሪቱ መንግሥት እና ቻይናውያን ተቋማት በአፍሪቃ የተፈጥሮ ሀብትን በማውጣቱ እና የመሰረተ ልማትን በማስፋፋት ስራላይ አትኩረዋል። በዚህ የዓለም ክፍል ውስጥ የኤኮኖሚ ጥቅም የማግኘቱ እድል ከፍ ያለ ሆኖ ታየዋለች። በተለይ፣ የሃገሯ ኤኮኖሚ እንቅስቃሴ እየቀዘቀዘ በመሄዱ፣ በመሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ ተሰማርተው የነበሩት ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ ውጭ ሃገራት ማዞር ተገደዋል። ይህ በርግጥ አንዱ ኤኮኖሚያዊ ምክንያት ሲሆን፣ የአህጉሩ ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብትም ሌላው ምክንያት ነው። »

ከጎርጎሪዮሳዊው 2009 ዓም ወዲህ ቻይና ትልቋ የአፍሪቃ የንግድ ተጓዳኝ ስትሆን ፣ በኤኮኖሚው ላይ ያሰረፈችውን ተፅዕኖ ወደ ፖለቲካውም ልታስፋፋው ትችል ይሆን በሚል አንተኒ ሮስ ተጠይቀው ሲመልሱ፣« በሆነ መንገድ ማስፋፋት ከጀመረች ቆይታለች። በአንድ አካባቢ፣ በተለይ ብዙ ውዝግብ በሚታይበት አፍሪቃን በመሰለ አካባቢ ብዙ ወረት እስካፈሰሰች እና ብዙ የሰው ኃይል እስካሰማራች ድረስ ፣ ጥቅሟን፣ ሊነሳ ከሚችል ማንኛውም ዓይነት አደጋ መጠበቅን አስፈላጊ አድርጋ ታየዋለች። ይህም በአንድ ሃገር ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የተሰኘውን ፖሊሲዋን መከተሉን፣ በተለይ ሃገሪቱ በዓለም አቀፉ ገበያ ውስጥ መግባት ከጀመረች ወዲህ ይበልጥ አዳጋች አድርጎባታል። »#

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic