የቻይና ኤኮኖሚና ዘላቂ ዕጣው | ኤኮኖሚ | DW | 07.03.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የቻይና ኤኮኖሚና ዘላቂ ዕጣው

ቻይና ባለፉት ዓመታት ታላቋ የውጭ ንግድ አራማጅና ዋነኛዋ የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት መናኮራኩር ሆኗ መቆየቷ የሚታወቅ ነገር ነው። ይሁን እንጂ የዕድገት ዘይቤዋ ለወደፊት ዕርምጃዋ የሚበጅ ዘላቂነት ያለው መሆኑን አሁን የዓለም ባንክ ጠበብት፤

ቻይና ባለፉት ዓመታት ታላቋ የውጭ ንግድ አራማጅና ዋነኛዋ የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት መናኮራኩር ሆኗ መቆየቷ የሚታወቅ ነገር ነው። ይሁን እንጂ የዕድገት ዘይቤዋ ለወደፊት ዕርምጃዋ የሚበጅ ዘላቂነት ያለው መሆኑን አሁን የዓለም ባንክ ጠበብት፤ አጠያያቂ አድርገዋል። ለመሆኑ የቻይና ኤኮኖሚ በሃያ ዓመታት ውስጥ ምን ዓይነት ገጽታ ሊኖረው ይችላል? ግዙፏ የሩቅ ምሥራቅ እሢያ አገር ምን ፈተናስ ተደቅኖባት ነው የምትገኘው? የዓለም ባንክ በቻይና መንግሥት ጥያቄ መሠረት በአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ጥናት ካካሄደ በኋላ ባለፈው ሣምንት መጀመሪያ «ቻያና በ 2030» በሚል ርዕስ ያጠናቀረውን ዘገባ ይፋ አድርጎ ነበር።

ጥናቱ የቻይናን ኤኮኖሚ የወደፊት ሂደት ሲዳስስ የአማካይ ጊዜ ሃሣብ የሚሰነዝርና የዕድገት ፈለግንም የሚያሳይ ነው። የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ የጥናቱ ዓላማ ቻይና ወደ በለጸገ ሕብረተሰብ ሽግግር እንድታደርግ ማገዝ መሆኑን ነው ወጤቱን ባቀረቡበት ወቅት የተናገሩት።

ጥናቱ በአጠቃላይ በርከት ባሉ አወዛጋቢ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ነው። ለምሳሌ የዓለም ባንክ እንደሚለው የአገሪቱ መንግሥታዊ ኩባንያዎች የነጻ ገበያ ኤኮኖሚን መርህ ተከትለው መሥራት ይኖርባቸዋል። የቻይና መንግሥታዊ ፋብሪካዎች ለሞኖፖል ያመቸ ሁኔታቸውን በመጠቀም ተፎካካሪዎችን ያላግባብ ከገበያ ያርቃሉ ሲሉ በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚተቹት ኩባንያዎች ዛሬ ብዙዎች ናቸው።

ይህ በአገር ውስጥ የግል ንብረት ሆነው የተቋቋሙ ኩባንያዎችንም አዘውትሮ ከዕድገት ችግር ላይ ሲጥል ይታያል። ዘገባው የሚያስጠነቅቀው የኤኮኖሚ ዕድገት እየቀነሰ መሄድ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል ነው። ይሁንና የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ ሁኔታውን ያን ያህል አስደንጋጭ አድርገው አልተመለከቱትም።

«እኔ የማምነው ቻይና ለዘብ ያለ አስተራረፍ ታደርጋለች በዬ ነው። የኤኮኖሚ ቀውስ ግን በወቅቱ አይታየኝም»

ይህን አመለካከት ኮሎኝ ከተማ ውስጥ ተቀማጭ የሆነው የጀርመንና የቻይና የኤኮኖሚ ትብብር ማሕበር ስራ አስኪያጅ ራይነር ጌህነንን የመሳሰሉ በዙዎችም ይጋሩታል። የሆነው ሆኖ ለዓመታት ተለምዶ የቆየው ዓመታዊ ክአሥር በመቶ በላይ የኤኮኖሚ ዕድገት ዘላቂነት በአገሪቱም በጥርጣሬ ዓይን መታየቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው የሚገኘው። በቤይጂንግ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሁ-ሢንግዱ ለምሳሌ ችግሩ ቻይናን በአምሥት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚሰማት ያምናሉ።

እርግጥ ዛሬ የቻይና የኤኮኖሚ ይዞታ መረጃዎችን ላይ ላዩን ከተመለከቱ ብዙም ለስጋት መንስዔ የሚሆን አይደለም። የዕድገት አሃዞቹ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገውን ዓለም እንዲያውም የሚያስቀኑ ናቸው። የቻይና ብሄራዊ ኤኮኖሚ ባለፈው ዓመት እንኳ 9,2 ከመቶ ዕድገት ታይቶበታል። በሌላ በኩል ግን ፕሮፌሰር ሁ ስውር ችግሮችን በመጠቆም እንደሚናገሩት ዕድገቱ በአሃዝ እንደሚታየው የጎላ አይደለም።

አምራቹ ኢንዱስትሪ ከመጠን በላይ የጉልበት መትረፍረፍ ሲኖረው አስፈላጊ ያልሆኑ ግንቢያዎችና ለፖለቲካ ዝና ተብለው የሚራምዱ ፕሮዤዎች መኖራቸውንም ምሁሩ ያናገራሉ። በተለይም ብዙ ሚሊያርድ ገንዘብ የሚፈስባቸው የመጨረሻዎቹ የፖለቲካ ፕሮዤዎች ደግሞ ዕውነተኛው አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት እንዲጋነን የሚያደርጉ ናቸው።

የቻይና መለያ ዛሬም እንዳለፉት ሃያ ዓመታት ሁሉ ግንቢያ ነው። በአገሪቱ ዙሪያ አዳዲስ ክተሞችና ፋብሪካዎች ያለማቋረጥ ያታነጻሉ። ይሁንና የአገሪቱ ኤኮኖሚ እጅጉን በውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ ነው። የዓለም ባንክ በበኩሉ አገሪቱ የግሉን ዘረፍ እንድታስፋፋ፣ ገበዮቿን ይበልጥ እንድትከፍትና የፊናንስ ፖሊሲዋንም ከምዕራቡ ዓለም እንድታጣጥም ያሳስባል። የቻይና የፊናንስ ሚኒስትር ክሢ ሱረን እንደሚሉት አገሪቱ ለውጡን የምታራምድ ሲሆን በተለይም የውስጥ ፍጆትን ለማዳበር እንደምትፈልግ ነው አጉልተው የሚናገሩት።

«በአገራችን በያዝነውን መዋቅራዊ ለውጥ ወደፊት ለመግፋት እንፈልጋለን። የዚህ መዋቅራዊ ለውጣችን ስልታዊ ግብ የሚሆነውም የአገር ውስጡን የፍጆት አቅም የማስፋፋቱ ጉዳይ ነው»

«ቻይና 2030» የሚለው ጥናት በዓለም ባንክ እንዲካሄድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ-ኬኪያንግ ተግባሩን ለዓለም ባንክ ያስተላለፉት የፊናንሱ ተቋም ሃላፊ ሮበርት ዞሊክ በ 2010 ቤይጂንግን በጎበኙበት ወቅት ነበር። በነገራችን ላይ ሊ በቤይጂንግ መንግሥት ውስጥ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ጉዳይ ሃላፊ ሲሆኑ በመጪው 2013 የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ከፍተኛ ዕድል የሚሰጣቸው ባለሥልጣንም ናቸው። እንግዲህ በቻይና የወደፊት የኤኮኖሚ ዕርምጃ ላይ ዓቢይ ሚና ሊኖራቸው ይችላል።

ትልቅ ትኩረታቸውና የዓለም ባንክ ጥናትም ዋና ዒላማ መንግሥታዊው ኩባንያዎች ናቸው። ቻይና ውስጥ እነዚህ የሁሉ ነገረ ተቆጣጣሪዎች ናቸው። ኤነርጂና ጥሬ ሃብትን፤ እንዲሁም ቴሌኮሙኒኬሺንና አጠቃላዩን መዋቅራዊ ዘርፍ በሙሉ ይቆጣጠራሉ። መንግሥታዊው ኩባንያዎች በአገሪቱ ማሕብራዊ ሕይወት ውስጥ የበላይ ሲሆኑ የሚተዳደሩትም በአብዛኛው በታላላቅ የፓርቲ ባለሥልጣናት የቤተሰብ ዓባላት ነው።

ከመንግሥት ባንኮች በትንሽ ወለድ ብድር ማግኘት፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ዋጋን መስቀልና የአክሢዮኖች ዋጋ ከመጠን በላይ ወደላይ እንዲተኮስ ማድረግ በነዚሁ ዘንድ ያለ ነው። የዓለም ባንክ ይህ አጉል የኤኮኖሚ አሰራር እንዲወገድ መንግሥታዊ ኩባንያዎች በውጭ ገለልተኛ ንብረት አስተዳዳሪዎች ቁጥጥር ይደረግባቸው ዘንድ የመጀመሪያ ዕርምጃ ብሎ ሃሣብ አቅርቧል። የቁጥጥሩ ዓላማም ኩባንያዎቹ የገበያ ኤኮኖሚ ደምቦችን ተከትለውና በፖለቲካም ነጻ ሆነው ምስራታቸውን ማረጋገጥ ነው።

ቻይና የተወሰኑ የንግድ ዘርፎችን በመሸጥም የግል ተፎካካሪዎችን ለማጠናክር አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባታል። ሮበርት ዞሊክ እንደሚያሳስቡት ቻይና በመንግሥት ይዞታ ስር ያሉ ኩባንያዎቿን ሚና ቀነስ አድርጋ መገደቧ፣ ሞኖፖልን ማፍረሷና የንብረት ግንኙነትን በማስፋት በግል ባለሃባቶች ላይ የተደቀነውን መሰናክል ማስወገዷ ለዚሁ ወሣኝ ነው። እርግጥ ይህ በቀላሉ የሚሆን አይደለም።

Wen Jiabao, Eröfnung des Chinesischen Volkskongresses in Peking

ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂባኦ

በመንግሥታዊው ዘርፍ ላይ ያተኮረው ለውጥ የዓለም ባንክ ባቀረበው ሃሣብ መሠረት የሚካሄድ ከሆነ የብዙዎችን የፓርቲ ካድሬዎች ጸጋ ፈተና ላይ የሚጥልና ከባድ ፈተናን የሚያሰከትል ነው። ኤኮኖሚው እርግጥ በይፋ የጋራ የአገር መሆኑ ቢነገርም ሃቁ የኮሙኒስቱ ፓርቲ ዓባላት በአገሪቱ ሃብት ለዓመታት በግል ሲካብቱ መኖራቸው ነው። የዓለም ባንክ ዘገባ «ቻያና 2030» ሌላው ቀርቶ በማዕከላዊው መንግሥት ውስጥ እንኳ በከፍተኛ ደረጃ አውዛጋቢ መሆኑ አልቀረም።

የአሜሪካው ጋዜጣ Wall Street Journal እንደዘገበው ከሆነ የቻይና መንግሥታዊ ኩባንያዎች ባለሥልጣን ተቋም ገና ዘገባው ከመውጣቱ በፊት አዘጋጆቹን በመንቀፍ የሚከተል ማንኛውንም የለውጥ ዕርምጃ በአጭሩ እንደሚቀጭ ነበር ያስገነዘበው። ይህ በሌላ በኩል ቻይና ውስጥ የሚኖረው ጋዜጠኛና ደራሲ ፍራንክ ሲረን እንደሚለው በጉዳዩ ውስጣዊ የፖለቲካ ቅራኔና የሥልጣን ትግል መኖሩንም የሚያመለክት ነው።

የቻይናን የወደፊት ዕድገት በተመለከተ እንግዲህ ሁለት የተለያዩ አስተሳሰቦች መኖራቸው የተሰወረ ነገር አይደለም። በውቅቱ በይፋ ውይይት ሲካሄድባቸው እየታየ ነው። ይሁንና የዓለም ባንክ ጥናት በቻይና የአንድ ፓርቱ ስርዓት ውስጥ የተለያየ አመለካከት ከያዙት ሃይላት አሰላለፍ አንጻር ተጽዕኖው ምን ያህል እንደሚሆን መተንበዩ የሚያዳግት ነው። የአገሪቱ የወደፊት የኤኮኖሚ ዕድገት ዕጣ ቁልፉ በማዕከላዊው መንግሥት ዕጅ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

ያም ሆነ ይህ የቻይና ኤኮኖሚ ጥገና ከሚጠይቅበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በመጪዎቹ ዓመታት የሕዝቡን የገንዘብ አቅምና ምርታማነትን አጣምሮ በማሳደጉ አቅጣጫ ማምራቱ አገሪቱን በረጅም ጊዜ ከቀውስ ለመሰወር ከተፈለገ አማራጭ የሚኖረው አይመስልም። የገቢ አለመጣጣምን ለማቃለልና ቀጣይነት የሚኖረው የውስጥ ፍጆታን ለማስፈን አዳዲስ ፖሊሲዎች ገሃድ መሆን አለባቸው። ቻይና በውጭ ንግዷላይ ጥገኛ ሆና መቀጠሉን ከመረጠች ይሄው በውስጥ ማሕበራዊ ውጥረትን በውጭም ከባድ ችግርን ሊያስከትል ይችላል።

እርግጥ የቻይና መሪዎችም ይህን ጠንቅቀው ነው የሚያውቁት። የአገሪቱ ወቅታዊ የዕድገት ሞዴል ፍቱን ሆኖ ሊቀጥል የሚችል አይደለም። የቻይና ኤኮኖሚ ባለፉት ስላሣ ዓመታት ውስጥ በአማካይ አሥር ከመቶ ዕድገት ሲያደርግ አገሪቱ በዚሁ ከ 500 ሚሊዮን የሚበልጥ የአገሪቱን ሕዝብ ከድህነት ማውጣቱ ተሳክቶላታል። ሆኖም የዓለም ባንክ የሚገምተው የቻይና ኤኮኖሚ በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት 8,5 በመቶ በማደግ ከ 2026 በኋላ ወደ አምሥት ከመቶ እንደሚያቆለቁል ነው።

Solarenergie in China

የቻይና የፀሐይ ኃይል ማመንጫ

እርግጥ የቻይና ኤኮኖሚ በተባለው መጠን ቢያቆለቁልም በሌላ በኩል አገሪቱ በኤኮኖሚ ታላቅነት በ 2030 ላይ አሜሪካን በአንደኝነት እንደምትተካ የሚጠራጠር የለም። ሆኖም ግን ቤይጂንግ ማሕበራዊ ቀውስን ከወዲሁ ለመቋቋም ለውጦችን በጊዜው ማድረግ ይኖርባታል። ቀደም ሲል ከተጠቀሰው የግል ኤኮኖሚ ዘርፍ መስፋፋት አስፈላጊነት ሌላ ተሃድሶ በማድረግ የተፈጥሮ እንክብካቤ ዕርምጃዎችን መውሰዱ፣ የሕዝብን ማሕበራዊ ዋስትና ማረጋገጡና የገበሬዎችን መብት መጠበቁ ወዘተ- አስፈላጊ ነው። ለውጡ ቻይናን የተረጋጋች፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል የሰፈነባት የሚያደርግና በውጭ ንግድ ላይ ያለባትን ጥገኝነትም የሚቀንስ ነው የሚሆነው።

በሌላ በኩል የቻይና የውጭ ንግድ በማደግ ቢቀጥል በዓለም ገበያ ላይ ውጥረትን ሊያስከትል የሚችል ነው። እርግጥ ሮበርት ዞሊክ እንዳስረዱት ቤይጂንግ በዓለም ባንክና በታወቂ የቻይና የልማት ተመራማሪዎች በተዘጋጀው ዘገባ ይዘት ላይ እንዳለ አትስማማም። ዞሊክ የባንኩ ዘገባ ከተጨባጩ ሁኔታ የተጣጣ መሆኑን ሲጠቅሱ የለውጥ መሰናክሎችን ለይቶ ለማውጣትና ተሃድሶን ለማቃለል ጥረት መደረጉንም አመልክተዋል። በመሠረቱ የዓለም ባንክ ዘገባ አቀባበል ያለፈውን ሕዳር የዓለምአቀፉን ምንዛሪ ተቋም ዘገባ ያህል ነው። የምንዛሪው ተቋም በጊዜው ቤይጂንግ ለመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች፣ የንግድ ባንኮችና ማዕከላዊ ባንኳ የበለጠ መብት ለመሰጠት የፊናንስ ገበዮችን ነጻ እንድትለቅ ነበር የጠየቀው።

ቤይጂንግ በበኩሏ ሃሣቡን በከፊል ተጨባጩን ሃቅ የሚያንጸባርቅ አይደለም በማለት መቃውሟ ይታውሳል። ቤይጂንግ አሁንም የዓለም ባንክን የመፍትሄ ሃሣቦች በሙሉ ገቢር ታደርጋለች በሎ መጠበቁ አዳጋች ነው። በተለይም የመንግሥት ይዞታዎችን ወደ ግል ዕጅ በማሻገሩ ረገድ! የእስካሁኑ ልምድ የሚያሳየው ቻይና ከፖለቲካና ከማሕበራዊ ስሌት አንጻር አመቺ የሆነውንና ለኤኮኖሚ ደግሞ ይበጃል የምትለውን መርጣ እንደምትወስድ ነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 07.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14FzR
 • ቀን 07.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14FzR