የቻይና ኤኮኖሚና መንግሥታዊው ሥልጣን | ኤኮኖሚ | DW | 01.10.2003
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የቻይና ኤኮኖሚና መንግሥታዊው ሥልጣን

ሕዝባዊት ቻይና ውስጥ ብዙ ሰዎች ከቀድሞው ይልቅ ዛሬ የተሻለ ኑሮ ነው የሚመሩት። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቻይናውያን ናቸው የራሳቸውን ቤት ለመግዛት፣ የራሳቸውን መኪና ለመንዳት ወይም የጉብኝት ጉዞ ለማድረግ የበቁት። በሌላው በኩል ደግሞ፣ ሕዝባዊት ቻይና ልክ እንደተለመደው ፍትሐዊ መንግሥት ከምትሆንበት መንገድ አሁንም እንደራቀች ነው የምትገኘው። በዚህ አኳኋን እንግዲህ፣ “ሶሻሊስታዊ የገበያ ኤኮኖሚ” የሚሰኘው የሀገሪቱ ምጣኔ

��ብታዊ ይዘት ምን የሚመስል ይሆናል? መልሱ በማኦና በካፒታሊዝም/ማለት በከበርቲአዊው ሥርዓት መካከል ይታያል።


ቻይና ውስጥ ዛሬም ቢሆን የታላቁ ሊቀመንበር/ማለት የማኦ ትዜዶንግ ገጽ የማይታይበት አንዳች የባንክ ኖት ወይም የወረቀት ገንዘብ የለም። ማኦ ትዜዶንግ ከሞቱ ከ፳፯ ዓመታትም በኋላ ሌላው ቢቀር በሕዝቡ የገንዘብ ኮሮጆ ውስጥ እንደጎሉ ናቸው። የወረቀቱ ገንዘብ የታተመው በማኦ የሕይወት ዘመን ሳይሆን፣ ከአራት ዓመታት በፊት ሕዝባዊት ቻይና ፶ኛ የምሥረታ ዓመቷን ባከበረችበት ወቅት ነበር። ግን ሁኔታው ምፀት ነው ለማለት ያስደፍራል፥ ይኸውም፣ የኤኮኖሚ ሥርዓቱን ለውጥ ያመጡት የማኦ ተከታይ ዴንግ ቻዎፒንግ እንጂ፣ ራሳቸው ማኦ አለመሆናቸው ነው። የለውጥ አራማጁ ዴንግ ቻዎፒንግ መፈክር፥ “ሐብታም መሆን አያሳፍርም” የሚል ነበር።

ታላቁ ሊቀመንበር--ማኦ ትዜዶንግ በቻይና ታሪክ ውስጥ እስካሁኑ ዘመን ድረስ ገና እልባት ላልተደረገላቸው ለብዙ አሰቃቂ ምዕራፎች በቀጥታ ተጠያቂ ናቸው። ሆኖም፣ ማኦ ትዜዶንግ በሀገሪቱ ታሪክ አጻጻፍና በቻይናውያኑ ልብ ውስጥ አሁንም ጥብቁን ቦታ እንደያዙ ናቸው። ገሃዳዊው ዕለታዊ ኑሮ ብቻ ከማኦ ርእዮታዊ ድርሳን ጋር እምብዛም የሚያገናኘው ነገር የለም።

ሕዝባዊት ቻይና ከ፳፭ ዓመታት በፊት ጀምራ ነው የገበያውን ኤኮኖሚ ስትሞካክረው የቆየችው። የሀገሪቱ ኮሙኒስት አመራር ኤኮኖሚውን ለቀቅ ለማድረግ በጀመረው ርምጃ ሥር ለግለሰቡ ከምንጊዜውም የበለጠ ነፃነትን ነበር የፈቀደው። ሕዝቡ ይህንኑ የነፃነት ፉካ አሁን እየተጠቀመበት ነው። ሰብዓዊውን ክብር የሚገፈው ባሕላዊው ዐብዮት አሁን ለብዙች እጅግ መራራ ትውስሕት ነው። ዛሬ ሕዝባዊት ቻይና ውስጥ የራሱን ኑሮ በራሱ ውሳኔ ለመምራት የሚሻው ግለሰብእ ዕድሉን በግል ኩባንያ ምሥረታ ለማቃናት ነው የሚጣጣረው። በዚህ ረገድ አንድ ምሳሌ የሚሆነን፥ ሸንዠን በተባለው ልዩ የኤኮኖሚ ቀጣና ዕድሉን በመጋብርት ፋብሪካና በሕንፃ ቆሳቁስ ለመደገፍ የተነሳሳ እንድ ጠና ያለ ጎልማሳ ነው፥

ሰውየው ራሱ እንደሚለው፣ የግሉን ታታሪነት አንድ አሮጌ ትራክተር በመግዛት ይጀምራል። ትራክተሩን ለእርሻ ሳይሆን ለሕንፃ ዕቃዎች ማጓጓዣ ይጠቀምበታል--አሸዋ፣ ድንጋይ.....ወዘተ። በባልተቤቱ አጋዥነት ድንጋዩን ከወንዞች ዳርቻ እየሰበሰበ ትራክተሩ ላይ በመጫን ለሕንፃው ሥራ እያቀበለ ጥሪት መቋጠር ጀመረ--ይህም ወደ ከፍተኛ ደረጃ አሸጋግሮት ዛሬ በ፸ ሚሊዮን ኦይሮ የሚገመት ኩባንያ ባለቤት አድርጎታል።

ይኸው ተጣጣሪ ግለሰብእ ከኮሙኒስቱ ፓርቲ አንዳች ርዳታ ባያገኝም፣ የፓርቲው አባል ለመሆን ይፈልጋል፣ ባለፈው ኅዳር የተካሄደው የፓርቲ ጉባኤ የወሰደው የርእዮት ማረሚያ ርምጃ ይህንኑ ፍላጎቱን እንዲያሟላ ያስችለዋል። በዚህ አኳኋን የኮሙኒስቱ ፓርቲ አባል የሆነው ባለኩባንያና ባለሚሊዮን ጌታ ካፒታሊስት ወይም ከበርቲ እንዲባል አይፈልግም። በእርሱ አስተያየት መሠረት፣ እንደ ቀድሞ ከበርቲዎች ትልቅ ባለርስት አለመሆኑ እና ማንንም አለመበዝበዙ ነው ካፒታሊስት የማ’ያደርገው። “ርግጥ እኔ ሐብታም ሰው ነኝ፣ ግን በቀን ከ፲፮ እስክ ፲፯ ሰዓታት ነው ስግር የምውለው፣ ከሠራተኞቼ ይበልጥ ነው የምግረው፣ ከውጭ ሲመለከቱኝ የግል ባለኩባንያ እመስላለሁ፣ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በሀገራችን የኤኮኖሚ ግንባታ ነው ተሳትፎ የማደርገው” ይላል የቻይናው ባለኩባንያ።

ማኦ ትዜዶንግ በ፲፱፻፵፩ የሕዝባዊት ቻይናን ኅልውና ባወጁበት ወቅት መላው ካፒታሊስቶች/ማለት ሐብታሞች እንዲወረሱ ነበር ያደረገው። ትልልቆቹ የመሬት ሐብታሞች ለክትትል ተዳርገው ራሳቸውን እስከመግደል እንዲደርሱ ነበር የተገፋፉት። እነርሱ ዛሬ ቢሆን ኖሮ እንደገና ሐብት ለመሰብሰብ በበቁም ነበር። የቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ ዛሬ የሚጣጣረው የፖለቲካ ኅልውናውን ለመጠበቅ ነው፤ የመንግሥት ገዥ ፓርቲ እንደሆነ ለመቆየት ከፈለገ፣ መሠረቱን ማስፋትና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን መላውን ስብስቦች ማስተሳሰር አለበት። ለጊዜው ግን አሁን ቻይና ውስጥ በኤኮኖሚውና በፖለቲካው ገሃድ መካከል ያለው ክፍተት ከምንጊዜውም ይበልጥ የገዘፈ ሆኖ ነው የሚታየው።

አስቀድመን የጠቀስነው ባለኩባንያና ሌሎችም የግል ተጣጣሪዎች፥ ኮሙኒስቱ ፓርቲ ቻይናን ጠንካራና ሐብታም ሀገር ለማድረግ እንደሚበቃ ያምኑበታል። እንዲያውም፣ በብዙዎቹ ቻይናውያን አመለካከት፣ ዛሬ ኤኮኖሚው እንጂ ፖለቲካው አይደለም ክብደት ያለው። ይፋው የመንግሥት አቋም ግን ተገላቢጦሹን ነው የሚዘበዝበው። የሆነ ሆኖ፣ ብዙ ቻይናውያን ከምንጊዜውም ይልቅ ዛሬ በይበልጥ የተሻሻለውን ኑሮ ነው የሚመሩት። የሕዝቡ የኑሮ ደረጃ ከፍ እያለ ከመሄዱ የተነሳ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ቻይናውያን የራሳቸውን መኖሪያቤት ለመግዛት፣ የራሳቸውን አውቶሞቢል ለማሽከርከር ወይም ወደ መዝናኛ ማዕከላት ለመጓዝ የበቁ ሆነው ነው የሚታዩት። ነፃ ሐሳብን፣ ነፃ አስተያየትን በይፋ መለፈፍ በእርግጥ የሚፈቀድ አይሆንም፣ ግን አንድ ሰው የሚያስበውን ነገር ሌላው ቢቀር በቤተሰቡ ዙሪያ ሊናገረው ይችላል።

ዛሬ ቻይና ውስጥ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ነፃነት ቢኖርም ቅሉ፣ መገናኛ-ብዙሃን አሁንም በቁጥጥር እንደተወጠሩ ናቸው፣ የመንግሥት ደኅንነት ወኪሎች የፖለቲካ አፈንጋጮችንና ሌላ ሀሳብ ተከታዮችን አቆብቁበው ይጠባበቃሉ፣ ክርስቲያናት ክትትል ይደረግባቸዋል፣ የሃራጥቃው ቡድን ፋሉን-ጎንግ አባላት ለቁምስቅል ይዳረጋሉ፣ በየወሩ ከመቶ የሚበልጡ ሰዎች ይረሸናሉ፣ ቻይና አሁንም ቢሆን ከፍትሓዊው ሥርዓተ-መንግሥት አለቅጥ እንደራቀች ነው የምትገኘው። ነፍሰጡሮች በስምንተኛውም ወራቸው እርግዝናውን እንዲያስወርዱ ይገደዳሉ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም ለአንድ ግዙፍ የውሃ ግድብ ፕሮዤ ቦታ እየለቀቁ በማይፈልጉት ቦታ መልሰው እንዲሠፍሩ ይደረጋሉ። ፖለቲካዊው የአብሮ ውሳኔ መብት ወይም ነፃው ምርጫ አሁንም ቢሆን ነውር እንደሆነ ነው የሚገኘው። ግን በዚሁ የመብት ጉድለት አንፃር የተቃውሞ ድምጽ ለማሰማት የሚደፍሩት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።

ነገሩ ምፀት ሆኖ ታዲያ፣ ዛሬ ቻይናን የሚጎበኝ ሰው በዚያችው ሀገር ውስጥ “ምንድን ነውኮሙኒዝም የሚባለው” ብሎ በአንክሮ እስከመጠየቅ ይደርስ ይሆናል---እንደ ነፃው የገበያ ኤኮኖሚ የአክሲዮን ገበያዎች አሉ፣ የግል መደብሮችና ምግብቤቶች በያለበት ይታያሉ፣ ግን አንዳች የተቃና የማሕበራዊ ኑሮ አውታር የለም። የትምህርት ገበታ፣ ወይም የጤንነትና የጡረታ አበል ዋስትና በነፃ አይገኝም። በዚህ ፈንታ የማኅበራዊው ኑሮ ዋስትና ከዛሬ ወደ ነገ የግል ጉዳይ እንዲሆን ነው የሚተወው።

የለውጥ አራማጁ ዴንግ ቻዎፒንግ መፈክር “ሐብታም መሆን አያሳፍርም” የሚል ነበር፤ የዛሬው አመራር ደግሞ “ለራሱ ኑሮ ሊጨነቅ የማይችል፣ ጥፋተኛው ራሱ ነው” የሚለው አነጋገር የሚጎላበት ይሆናል። ስለዚህ እንግዲህ፣ ዛሬ ብዙ ቻይናውያን ወደ ኋላ መለስ ብለው ማኦ ትዜዶንግንና አንድ መደብአልባ ኅብረተሰብእ ለመፍጠር የነበራቸውን ሕልም በናፍቆት ቢያስታውሱ የሚያስገርም አይሆንም።