የቻይና አፍሪካ ትብብር ርዕይ 2035 ምን ይዞ መጣ?
ረቡዕ፣ ኅዳር 22 2014የቻይናው ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ዋንግ ይ ወደ አዲስ አበባ ከማቅናታቸው በፊት ትናንት ማክሰኞ በዳካር በሰጡት መግለጫ ቻይና እና አፍሪካ በግንኙነቶቻቸው ረገድ ጠቃሚ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም (FOCAC) ሲጠናቀቅ ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ ከሴኔጋሉ አቻቸው አይሳታ ታል ሳል ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ "ዓለም አቀፉ ነባራዊ ሁኔታ የቱንም ያክል ቢቀየር እና ቻይና እና አፍሪካ ምንም አይነት ፈተናዎች እና እንቅፋቶች ቢገጥሟቸው ሁለቱ ወገኖች ፖለቲካዊ መተማመን ለማጠናከር እና ተግባራዊ ትብብርን ጥልቅ ለማድረግ ቁርጠኛ ሆነው ለመዝለቅ መስማማታቸውን" ገልጸዋል።
ቻይና እና 53 የአፍሪካ አገራት የተሳተፉበት እና ከሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር አቅራቢያ በምትገኘው ዲያምኒያዲዮ የተካሔደው ይኸው ስብሰባ በርከት ባሉ ዘርፎች ላይ ያተኮረ ነበር። የቻይና አፍሪካ አማካሪ ተቋም መሥራች እና ዳይሬክተር አቶ አሌክሳንደር ደምሴ "ስምንተኛው ዙር ስብሰባ የቻይና እና የአፍሪካ አገሮች ግንኙነት እየበሰለ እየመጣ እንደሆነ የሚያሳይ" እንደሆነ ይናገራሉ። "ቻይና ከዚህ በፊት የ3 አመት ዕቅድ ብቻ ነበር ይዛ የምትንቀሳቀሰው። አሁን ግን የአስር አመት ዕቅድ ይዛ መጥታለች" የሚሉት አቶ አሌክሳንደር የሴኔጋሉ ስብሰባ "ስኬታማ ነበር" የሚል ዕምነት አድሮባቸዋል።
የቻይና አፍሪካ ትብብር ርዕይ 2035 ምን ይዞ መጣ?
የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም የምኒስትሮች ስብሰባ ባለፈው ሰኞ ሲጀመር ንግግር ያደረጉት የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ 65 አመታት ላስቆጠረው የቻይና እና የአፍሪካ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አዲስ መንገድ መቀየዱን ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዝደንቱ የሴኔጋሉ ስብሰባ ከመካሔዱ በፊት ሁለቱ ወገኖች ለግንኙነታቸው "የቻይና አፍሪካ ትብብር ርዕይ 2035" የተባለ ዕቅድ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። በዕቅዱ የመጀመሪያ ሶስት አመታት ቻይና በአፍሪካ ልታከናውን ያቀደቻቸውን ዘጠኝ ሥራዎች ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ በንግግራቸው ዘርዝረው አቅርበዋል። ፕሬዝደንቱ እንዳሉት ከዘጠኙ የትኩረት አቅጣጫዎች ቀዳሚው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ጉዳይን የተመለከተው የሕክምና እና የጤና መርሐ-ግብር ነው።
ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ "የአፍሪካ ኅብረት [በጎርጎሮሳዊው] 2022 ከአኅጉሩ ሕዝብ 60 በመቶውን ለመከተብ የያዘው ዕቅድ እንዲያሳካ ተጨማሪ አንድ ቢሊዮን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ለአፍሪካ እናቀርባለን። ከዚህ ውስጥ 600 ሚሊዮን ክትባት በነጻ፤ የተቀረው 400 ሚሊዮን ክትባት ደግሞ የቻይና ኢንርፕራይዞች ከሚመለከታቸው የአፍሪካ አገራት ጋር በጥምረት እንዲያመርቱ በማድረግ የሚቀርብ ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።
በመጀመሪያዎቹ ሶስት አመታት ተግባራዊ በሚሆነው በዚሁ ዕቅድ "የአፍሪካ አገሮች አስር የሕክምና እና የጤና አጠባበቅ ፕሮጀክቶችን እንዲያከናውኑ ቻይና ዕገዛ ታደርጋለች። ከዚህ በተጨማሪ 1,500 የሕክምና እና የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎችን ወደ አፍሪካ ትልካለች" በማለት አብራርተዋል።
ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ በንግግራቸው ይፋ ያደረጉት ሁለተኛ መርሐ-ግብር የድሕነት ቅነሳ እና የግብርና ልማት ነው። በዚህ መርሐ-ግብር ቻይና አስር የድሕነት ቅነሳ እና የግብርና ፕሮጀክቶች በአፍሪካ ለመከወን መዘጋጀቷን ሺ ዢንፒንግ ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ እንዳሉት አገራቸው 500 የግብርና ባለሙያዎችን ወደ አፍሪካ ትልካለች። ዕቅዱ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ማዕከላት፣ ማሰልጠኛዎች እና ሰርቶ ማሳያዎች መገንባትን ያካተተ ነው።
በንግድ ማስፋፊያ ረገድ በተወጠነው ዕቅድ የአፍሪካ የግብርና ውጤቶች ለቻይና ገበያ የሚቀርቡበትን መንገድ የሚያፋጥን እና የሚያቀላጥፍ ሥርዓት ለመዘርጋት የፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ መንግሥት አቅዷል። የአፍሪካን የወጪ ንግድ ለማገዝ ቻይና 10 ቢሊዮን ዶላር እንደምታቀርብ ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል። ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሺየቲቭ በተባለው የቻይና ዕቅድ ላይ በሚመረኮዘው መርሐ-ግብር አገራቸው የአፍሪካ አገሮችን እርስ በርስ የሚያገናኙ አስር የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች ለማከናወን እና ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ጽህፈት ቤት ጋር የኤኮኖሚ ትብብር የሚያበጅ የባለሙያዎች ቡድን ለማቋቋም ሺ ዢንፒንግ ቃል ገብተዋል።
አራተኛው ዕቅድ በሶስቱ አመታት የቻይና ኩባንያዎች ከ10 ቢሊዮን ዶላር በማያንስ መዋዕለ-ንዋይ በአፍሪካ እንዲሰማሩ ለማበረታታት እና የቻይና አፍሪካ የግል መዋዕለ ንዋይ መድረክ ለማቋቋም የተወጠነ ነው። ቻይና አስር የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ እና የሥራ ፈጠራ ፕሮጀክቶችን በአፍሪካ እንደምታከናውን የተናገሩት ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ የአኅጉሪቱን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለመደገፍ ለአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት 10 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንደምታቀርብ ቃል ገብተዋል። ቻይና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ካላት የመበደር አቅም አስር ቢሊዮን ዶላሩን ለአፍሪካ አገራት ለማስተላለፍ ዝግጁ መሆኗን ሺ ገልጸዋል።
የቻይና አፍሪካ አማካሪ ተቋም ዳይሬክተር አቶ አሌክሳንደር ደምሴ "የአፍሪካ አገሮች ራሳቸው የራሳቸውን ምርቶች ወደ ቻይና እንዲልኩ ይፈለጋል። [በጎርጎሮሳዊው] እስከ 2024 ዓ.ም. ድረስ እስከ 300 ቢሊዮን ዶላር የአፍሪካን ቁሳቁሶች ከአፍሪካ አገሮች ቻይና መሸመት ትፈልጋለች። ይኸ ትልቅ ዕድል እየፈጠረ ነው" ሲሉ ይናገራሉ። "እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች፤ ሌሎች ትልልቅ የግብርና አምራች አገሮች በዚህ በጣም ሊጠቀሙ ይችላሉ" ሲሉ አቶ አሌክሳንደር አብራርተዋል።
በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ተግባራዊ ከሚደረጉ የቻይና አፍሪካ ትብብር ርዕይ 2035 ውጥኖች መካከል ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ እንዳሉት በአፍሪካ አስር የዲጂታል ኤኮኖሚ ፕሮጀክቶች መገንባት፤ በሳተላይት እና በኤሌክትሮኒክ ግብይት ዘርፎች ትብብሮችን ማጠናከር ይገኙበታል።
ቻይና በሚቀጥሉት ሶስት አመታት አስር የአረንጓዴ ልማት እና የከባቢ አየር ጥበቃ ፕሮጀክቶች በአፍሪካ ለማከናወን፤ አስር ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እና ለማደስ፣ 10,000 የአፍሪካ ከፍተኛ ባለሙያዎችን በአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እና ስብሰባዎች ለመጋበዝ ፕሬዝዳንቱ ቃል ገብተዋል። የቻይና እና የአፍሪካን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ቃል የገቡት ፕሬዝደንቱ በአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ዘርፍ ጭምር ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል።
ቻይና እና የአፍሪካ አገሮች የዕዳ ጫና ሥጋት
ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ በስብሰባው ይፋ ያደረጓቸው ዘርፈ ብዙ ዕቅዶች የዓለምን ትኩረት የመሳባቸውን ያክል ቻይና ከአፍሪካ ባላት ግንኙነት ተጠቃሚው ማነው? የሚለው ሙግት ላለፉት ጥቂት አመታት በርትቶ ታይቷል። ቻይና ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በአፍሪካ ያከናወነችው መዋዕለ-ንዋይ እና ለአገራቱ የሰጠችውን ብድር ፍላጎቷን ለማስፈጸም ተጠቅማበታለች የሚል ክስ ይደመጣል። በጀርመን ላይፕዚግ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ኤኮኖሚ እና የአፍሪካ ጥናት ፕሮፌሰሩ ሔልሙት አሼ ግን "ይሁነኝ ተብሎ የታቀደ ፖሊሲ መሆኑን እጠራጠራለሁ። ቻይና የአፍሪካ አገሮች በዕዳ ወጥመድ ውስጥ ሲወድቁ የማየት ፍላጎት የላትም። ችግሩ የአፍሪካ አገሮች ከቻይና ከተበደሩት ግማሹ ድብቅ ዕዳ ነው። ድብቅ ዕዳ ማለት የአከፋፈል ውሉ እና ሒደቱ አይታወቅም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በአሜሪካው የጆን ኾፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የቻይና አፍሪካ ጥናት ተቋም ባለፈው መስከረም ይፋ ያደረገው አንድ ሰነድ ዛምቢያ ከቻይና መንግሥት እና የግል ተቋማት 6.6 ቢሊዮን ዶላር መበደሯን ይፋ አድርጓል። ይኸ የቀደመው የዛምቢያ መንግሥት ይፋ ካደረገው በእጥፍ ገደማ ከፍ ያለ ነው። እንዲህ አይነቱ የግልጽነት እጦት ቻይናን ለትችት እና ጥርጣሬ አጋልጧታል። የቻይና አፍሪካ አማካሪ ተቋም ዳይሬክተር አቶ አሌክሳንደር ደምሴ የአፍሪካ አገሮች ከሩቅ ምሥራቅ ወዳጃቸው ባላቸው ግንኙነት በቅጡ ለመጠቀም ብልኅ ሊሆኑ እንደሚገባ ያምናሉ።
"አንዳንድ አገሮች የተሻለ አቅም አላቸው። የተሻለ ግንዛቤም ይዘው እየመጡ ነው" የሚሉት አቶ አሌክሳንደር ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ እና ግብጽ ከወደ ቻይና የመጣውን ዕድል አጠቃቀም ካወቁበት ጎራ ይመድቧቸዋል። "ብዙ የአፍሪካ አገሮች የበለጠ ሥራ መሥራት አለባቸው። አንድ ስብሰባ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ሌት ተቀን መሥራት ግድ ይላል" ሲሉ አቶ አሌክሳንደር ያስረዳሉ።
የቻይና ዕዳ ከተጫናቸው የአፍሪካ አገሮች መካከል ከቤጂንግ በወሰደችው ብድር የባቡር መጓጓዣዎች፣ አውራ ጎዳናዎች፣ የስኳር ፋብሪካዎች እና የተለያዩ ማምረቻዎችን ጨምሮ ግዙፍ መሠረተ-ልማቶች ስትገነባ የቆየችው ኢትዮጵያ ትገኝበታለች። አገሪቱ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ ከቻይና የተበደረችውን ገንዘብ መክፈል ቸግሯታል። በአሜሪካው የጆን ኾፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የቻይና አፍሪካ ጥናት ተቋም ሰነድ እንደሚያሳየው ከጎርጎሮሳዊው 2000 እስከ 2018 ዓ.ም. ባሉት አመታት ቻይና ለአፍሪካ አገሮች ከሰጠችው 148 ቢሊዮን ዶላር ብድር 13.7 ቢሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ ከወደ ቻይና የተበደረችው የገንዘብ መጠን በቡድን 20 አገራት በኩል የጀመረችውን የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ሊያወሳስብ እንደሚችል ባለሙያዎች ሥጋት አላቸው።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ