የቻይና ልዩ ልዑክ የሱዳን ጉብኝት | አፍሪቃ | DW | 29.02.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የቻይና ልዩ ልዑክ የሱዳን ጉብኝት

በዳርፉር ሁኔታዎች ሊሻሻሉ እንደሚችሉ በሱዳን አራተኛውን ጉብኝታቸው ያጠናቀቁት የቻይና ልዩ የሱዳን ልዑክ ሊዉ ግዢንግ አስታወቁ።

ቻይናዊ ሰላም አስከባሪ በዳርፉር

ቻይናዊ ሰላም አስከባሪ በዳርፉር

ዓለም አቀፉ ቅይጥ ሰላም አስከባሪ ጓድ በዚያ በሚሰማራበት ሂደት ላይ አሁን አንድም እንቅፋት እንዳልተደቀነ ነው ቻይናዊው ባለስልጣን ያመለከቱት። ይሁን እንጂ፡ ለዳርፉር ውዝግብ ፖለቲካዊው መፍትሄ ይገኝ ዘንድ ምዕራቡ ዓለምም ጥረቱን እንዲያጠናክር ሊዉ ግዢንግ ጠይቀዋል። የዳርፉር ዓማጽያን ከሱዳን መንግስት ጋር እንዲደራደሩ ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ ግፊት ሊያሳርፍባቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሊዉ ግዢንግ የተሳካ ነበር ባሉት የሶስት ቀኑ ጉብኝታቸው ብዙ ጠቃሚ መረጃ ማግኘታቸውን በመግለጽ፡ በዳርፉር የተሰማሩት አንድ መቶ አርባ የቻይና ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ስራ አድንቀዋል። በዳርፉር መሰማራት በያዘው ከተመድና ከአፍሪቃ ህብረት በተውጣጣው ቅይጡ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት ውስጥ ትልቅ ሚና መያዝ ያለባቸው አፍሪቃውያት ሀገሮች ታታሪነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
« ከትልቆቹ አፍሪቃውያት ሀገሮች መካከል እስካሁን ድረስ አንድዋም ወታደሮች የመላክ ግዴታዋን አላሟላችም፤ ምንም እንኳን ፍላጎቱ ቢኖራቸውም። ምናልባት በቴክኒካዊ ችግር፡ ወይም በጦር መሳሪያ እጥረት ሊሆን ይችላል። እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ችግራቸውን ስለተረዳው፡ ሀገራቱ ያለባቸውን ችግር እንዲያቃልሉ አሁን አብረን ለመርዳት ዝግጁ ሆኖዋል። »
በዳርፉር ይሰማራል ከሚባለው ሀያ ስድስት ሺህ ወታደሮች መካከል እስካሁን ጥቂት መቶዎች ብቻ ናቸው ዳርፉር የገቡት። ይሁን እንጂ፡ ሱዳን መንግስት ውዝግቡን ለማብቃት የሚያደርገውን ጥረቱን ሊው ግዢንግ በማሞገስ በሁለቱ ሀገሮቻቸው መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ጠቁመዋል። ባለፉት ጊዚያት ሁሉ በተመድ የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውስጥ በሱዳን አንጻር የቀረቡ ጥእእጥር ርምጃዎችን ቻይና ድምጽን በድምጽ በመሻር መብትዋ ተጠቅማ ውድቅ አድርጋቸዋለች። ቻይና በሱዳን ላይ ይጣል የሚባለውን ማዕቀብ ሀሳብ እንደማትደግፈው ሊዉ ግዢንግ አስታውቀዋል።
« እርግጥ፡ የሱዳን መንግስት ትብብሩን እንዲያሳድግ ማሳሰባችንን እንቀጥላለን። ይሁንና፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፡ በተለይም፡ በጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ያሉት ቋሚ መንበር ያላቸው ሀገሮች ከነርሱ የሚጠበቅባቸውን ማሟላት ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፡ ትልቁ ትኩረት ቅይጡ ሰላም አስከባሪ ጓድ በሚሰማራበት ድርጊት ላይ ብቻ መሆን የለበትም ማረፍ ያለበት፤ የፖለቲካው የመፍትሄ ሂደትም ትልቅ ሚና ሊሰጠው ይገባል። »
የፖለቲካ መፍትሄ ካልተገኘለት በስተቀር የሰላም አስከባሪው ጓድ አንድ ቀን ዳርፉርን ለቆ በሚወጣበት ጊዜ ውዝግቡ ሊቀጥል እንደሚችል ሊዉ ግዢንግ አስጠንቅቀዋል። በመሆኑም፡ ዓማጽያኑ ወደድርድሩ ጠረጴዛ እንዲመለሱ ጠይቀዋል። ምዕራቡ ዓለም በግዞት በሚገኙት የዳርፉር ዓማጽያን አማካይነት በዳርፉር በሚንቀሳቀሱት ዓማጽያን ላይ ግፊት እንዲያሳርፉም ቻይናዊው ልዩ የሱዳን ልዑክ ሀሳብ አቅርበዋል። ለምሳሌ በፓሪስ በግዞት የሚኖሩት ዋነኛው የዳርፉር ዓማጽያን መሪ፡ በዳርፉር ሲቭሉ ህዝብ እስካለቀ ድረስ ከሱዳን መንግስት ጋር መደራደር አስፈላጊ እንዳልሆነ አስታውቀዋል። በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ዘገባ መሰረት የሱዳን መንግስት ባለፈው የሳምንት መጨረሻ በምዕራብ ዳርፉር ባካሄደው ጥቃት ስድሳ ሺህ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ተዛማጅ ዘገባዎች