የቻይና ልማት፤ የምዕራቡ ዓለም ስጋት | ኤኮኖሚ | DW | 07.04.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የቻይና ልማት፤ የምዕራቡ ዓለም ስጋት

የቻይና የግንቢያ ባንክ በሻንግሃይ

የቻይና የግንቢያ ባንክ በሻንግሃይ

ከሶሥት ሚሊያርድ በላይ ሕዝብ የሚገኝባት ግዙፍ አገር በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ዘርፎች በዓለም ላይ ዋነኛዋ አምራች፣ ገብዪ፣ ሻጭና ፈጂም ሆና ትገኛለች። ከአዳጊው እስከበለጸገው ዓለም በምድራችን ዙሪያ በሚገኙት ገበዮች ላይ የቻይናን ያህል የተለያየ ምርት የሚያራግፍ አንድም አገር አይገኝም። አሁን ከኤኮኖሚው ዕድገት ጋር እንዲያውም የውጭ ምርትን ወደ አገር በማስገባትም ቀደምት እየሆነች ነው። የቻይና አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ዕድገት ባለፉት ዓመታት በአማካይ በሥምንትና ዘጠኝ በመቶ መካከል የሚንሸራሸር ሆኖ ቆይቷል። በዚህና በመጪዎቹ ዓመታትም ብዙ ለውጥ የሚያመጣ አይመስልም።

መረጃዎች የሚጠቁሙት በያዝነው 2005 የመጀመሪያ ሩብ ፍጻሜ ዕድገቱ 8.8 በመቶ ሊጠጋ እንደሚችል ነው የሚገመተው። በኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ዕድገቱ በአንድና ሁለት በመቶ መካከል ተወስኖ የሚገኘው ምዕራቡ ዓለም ይህን ሊያስበው ቀርቶ ሊያልመው እንኳ አይችልም። ለሕዝባዊት ቻይና የተፋጠነ የልማት ዕርምጃ አንዱና ምናልባትም ዋና ሚስጥሩ በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት መንግሥታት ሲነጻጸር የሥራ ጉልበትም ሆነ ይሄው የሚጠይቀው ማሕበራዊ ወጪ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑና የምርታማነቱ ከፍተኛነት ነው።

ከሁለት አሠርተ-ዓመታት ወዲህ ከበለጸጉት መንግሥታት የዕድገት ደረጃ በመድረስ በኤኮኖሚ ልማትና በዘመናዊ ጦር በሚገባ የታጠቀች ሃያል አገር ለመሆን ቤይጂንግ በቁርጠኝነት የምታራምደው ፖሊሲ ማንም ሊገታው የሚችል አልሆነም። ምዕራባውያኑ መንግሥታትም ቻይናን ከተቀረው ታዳጊ ዓለም ለየት ባለ ዓይን በመመልከት ተስማምቶ መኖሩንና የወደፊቱ ሰፊ ገበያ ተጠቃሚ መሆኑን ነው የመረጡት። ዛሬ በቻይና የግንቢያም ሆነ የሌላ ሥራ ኮንትራት ለማግኘት ቤይጂንግ ውስጥ በታላቅ ጉጉት ተራ የሚጠብቁት ምዕራባውያን ኩባንያዎች ብዙዎች ናችው። የቤይጂንግ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ባይሻሻልም ምዕራቡ ዓለም ይህን በመሞገት ከጥቅሙ ለማስቀደም አልፈቀደም።
ሰሞኑን ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲይ ኢንተርናሺናል በዓመታዊ ዘገባው እንዳመለከተው በዓለም ላይ አብዛኛው የሞት ቅጣት ብያኔ ገቢር የሆነው በቻይና መሆኑም ይህን አይቀይረውም። ቻይና የውስጥ ጉዳዬ የምትለውን ይህንኑ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ለመናገር ያህል ያነሣ ምዕራባዊ መንግሥት በየጊዜው አይታጣ እንጂ እስካሁን ጉዳዩን ምክንያት አድርጎ ተገቢውን የፖለቲካና የኤኮኖሚ ግፊት ለማድረግ የደፈረ አንድም የለም። የኤኮኖሚ ቀውስ አዙሪት፣ የዕድገት ድቀትና የሥራ-አጥ ብዛት ወጥሮት በሚገኘው ባለኢንዱስትሪ ዓለም ከዋሺንግተን እስከ አውሮፓ የወደፊቷን ማራኪ ገበያ ቻይናን ማስቆጣቱ አልተፈለገም።

የአውሮፓው ሕብረት በወቅቱ በቻይና ላይ ጭኖ ያቆየውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ለማንሣት የሚያቅደውም በአመዛኙ በዚሁ የኤኮኖሚ ጥቅሙ በማየሉ የተነሣ ነው። ለቻይና የጦር መሣሪያ ማዕቀቡ በይፋ አነጋገር የፖለቲካ አድልዎ ሆኖ ነው የኖረው። ታዲያ ይህ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለግንኙነቱ መሰናክል መሆኑም አልቀረም። ለማንኛውም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊ-ሻዎሺንግ በቅርቡ አገራቸው ለሰላም ባለባት ሃላፊነት የተነሣ ከአውሮፓ ብዙ መሣሪያዎች አትፈልግም ይበሉ እንጂ ቤይጂንግ ጦሯን ዘመናዊ ለማድረግ መነሣቷን የሚጠራጠር የለም።

የቻይና ጦር ባለሥልጣናት ሰፊ የመሣሪያ ግዢ ዝርዝር አውጥተው ከተቀመጡ ቆይተዋል። ባንዳዎ-ሼንባዎ የተሰኘው የቻይና ጋዜጣ በቅርቡ እንደዘገበው ከሆነ ቤይጂንግ ለጦር መሣሪያ የውጭ ንግዷ ብዙም የፖለቲካ ቅድመ-ግዴታ ከማታስቀምጠው ከፈረንሣይ ሚራዥ የጦር አውሮፕላኖች፣ የባሕር ውስጥ መርከቦች (ኡ-ቦት) እና ወታደራዊ መረጃ አቀባይ አካላት (ሣቴላይቶች) መግዛት ትፈልጋለች። ሕጉ ከተወሳሰበባት ከጀርመንም ቢሆን የጦር መሣሪያ ግዢው ፍላጎት የጠነከረ ነው። የቻይናን መፍቀረ-ዴሞክራሲ ንቅናቄ በሃይል መቀጨት አስከትሎ የአውሮፓውያኑ ማዕቀብ ከ 16 ዓመታት በፊት ከሰፈነ ወዲህ በዚህ በጀርመን በገዢ እጥረት የተነሣ በጦር ታንኮች ሥራ ከተሰማራው ሙያተኛ ሁለት-ሶሥተኛው ሥራ-አጥ ለመሆን በቅቷል።

ቤይጂንግ አሁን የምታሰበው በሥራ-አጥ ብዛት ተወጥራ የምትገኘው ጀርመን የኤኮኖሚ ችግሯን ለመወጣት ስትል እንደገና የጦር መሣሪያ ልትሸጥላት ዝግጁ እንደምትሆን ነው። ለነገሩ የቤይጂንግ ግምት እምብዛም ከዕውነት የራቀ አይደለም። እርግጥ ማዕቀቡ እንዲነሣ ከፈረንሣዩ ፕሬዚደንት ከዣክ ሺራክ ጋር ሆነው በግንባር ቀደምነት ግፊት የሚያደርጉት የጀርመኑ መራሄ-መንግሥት ጌርሃርድ ሽሮደር በቅድሚያ ሃሣባቸውን በጥብቅ የሚቃወመውን ተቃዋሚ የፖለቲካ ሕብረት ማግባባት ግድ ይሆንባቸዋል።

ለነገሩ ብዙዎች የጦር መሣሪያ አቅርቦቱን የሚቃወሙት በቻይና የሰብዓዊ መብቱ ይዞታ የተነሣ ሣይሆን ይልቁንም ዘመናዊው መሣሪያ ጦርነት ሊፈነዳበት በሚችል የቀውስ አካባቢ ጥቅም ላይ የመዋሉ ሃሣብ እያስደነገጣቸው ነው። ቤይጂንግ ገና ከዛሬው በደቡብ-ምሥራቅ ጠረፏ ሰባት መቶ የመካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ሮኬቶች ተክላለች። እነዚህም በቀጥታ በታይዋን ላይ የተጠመዱ ሲሆን ቻይና ካስፈለጋት በደሴቲቱ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ከማካሄድ ለመቆጠብ ፈቃደኛ አይደለችም።
ይህ ሃቅ በአውሮፓ ችላ ተብሎ ኖሯል። ገና አሁን በቅርቡ ነው የቻይና ብሄራዊ ሕዝባዊ ሸንጎ የታይዋንን የመገንጠል ፍላጎት በሃይል ለመግታት የሚያስችል ሕግ ካጸደቀ ወዲህ እንደገና ማሳሰብ የጀመረው። የሆነው ሆኖ ጎልቶ ከሚታየው ተጨባጭ የኤኮኖሚ ጥቅም አንጻር ማዕቀቡ ጸንቶ መቀጠሉ ሲበዛ ያጠራጥራል።

ሕዝባዊት ቻይና ዛሬ ለምዕራቡ ዓለም በሁሉም አቅጣጫ በቀላሉ የምትታይ አልሆነችም። በወቅቱ የጨርቃ-ጨርቅ ምርቷ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትን ሃገራት ገበያ ማጥለቅለቁ ሌላው አከራካሪ ነገር ሆኖ ነው የሚገኘው። ከሰላሣ ዓመታት በፊት ጸንቶ የነበረው የጨርቃ-ጨርቅ ምርትን በኮታ የሚገድብ ውል የጊዜ ገደብ ባለፈው ጥር ወር ካበቃ ወዲህ ቻይና በአሜሪካና በአውሮፓ ገበዮች ሰፊ ምርት ማራገፍ ይዛለች። የቤይጂንግ የውጭ ንግድ በዚህ መስክ በተመሳሳይ ጊዜ ባለፈው ዓመት ከነበረው 28 በመቶ ከፍ ማለቱ ነው የሚነገረው።

ምዕራባውያኑ መንግሥታት ደግሞ የጨርቃ-ጨርቅ ኢንዱስትሪያቸው ቻይና በምታቀርበው ርካሽ ምርት የተነሣ ውድቀት እንዳይደርስበት መስጋታቸው አልቀረም። ለዚህም ነው ሰሞኑን ብራስልስና ዋሺንግተን የመከላከያ ዕርምጃ ለመውሰድ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙት። ሆኖም ይህም ዕርምጃቸው የዓለም ንግድ ድርጅት ደምብ በሚፈቅደው መሠረት ወደ ገበዮቻቸው የሚገባውን የቻይና ምርት ገደብ ከማድረግ አልፎ ጠንካራ የፖለቲካ ዕርምጃን እንደማያስከትል ግልጽ ነው። ሕዝባዊት ቻይና ዛሬ በዓለም ገበያ ላይ አልባሳትን በሰፊው የምትሸጠው ቀደምቷ አገር ናት። በኮታው ገደብ መነሣት ደግሞ ወደፊት ከሁሉም ይበልጥ ተጠቃሚ እንደምትሆን የብዙዎች ግምት ነው።

እርግጥ የሕዝባዊት ቻይና ግስጋሴ አስደናቂ ቢሆንም የተያዘው የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ከጅምሩ እንደታሰበው ያላንዳች እክል የሚራመድ አይደለም። የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል ምርት ግዙፍ ከሆነው የግንቢያ ፕሮዤ ጋር ተጣጥሞ ሊራመድ አለመቻሉ አንዱ ትልቅ ችግር ነው። በዚሁ የተነሣ ብዙዎች ፕሮዤዎች መቋረጥ ወይም መሸጋሸጋቸውና አጠቃላዩ ተግባር ጋብ እንዲል መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገቺ ዕርምጃዎች መውሰዱ ይታወቃል።

ሌላው ችግር በቻይና እየተለወጠ ከመጣው ሁኔታ አንጻር ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፈለሣ እያየለ መሄዱ ነው። እስከ 2020 ማለት በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ከ 300 ሚሊዮን የሚበልጡ ቻይናውያን ወደ ከተሞች በመጉረፍ የአገሪቱን ገጽታ በሰፊው እንደሚቀይሩ ነው የሚገመተው። እርግጥ በገጠሩ ሕዝብ ማነስ በዚያው የሥራ መስኮች እንደልብ መገኘታቸውና እያረጀ የሚሄደው የሕብረተሰብ ክፍል እንቅስቃሴ መቀነስም ከ 2020 በኋላ ፈለሣውን ጥቂት ገደብ ያደርገው ይሆናል።
ይህ የመንግሥት ግምት ነው። ሆኖም የኤኮኖሚ ዕድገትና የኢንዱስትሪው ልማት አንዴ ስለተንቀሳቀሰ ፈለሣው በቀላሉ ሊገታ መቻሉ ግን ሲበዛ ያጠራጥራል። ከጥቂት ጋብታ በኋላ እንደገና ከመቶ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ወደ ከተሞች መንቀሳቀሱ የማይቀር ነው የሚመስለው። የቻይና ጠበብት ይህ ሂደት ቀጣይ መሆኑንና በ 2040 ገደማ ዛሬ አርባ በመቶ የሚሆነው የከተማ ነዋሪ ድርሻ ሰባ በመቶ እንደሚደርስ ያምናሉ።

ውጤቱ ከተሞች የአካባቢ መንደሮችን እየዋጡና እየተስፋፉ መሄዳቸው፤ የጎስቋላ ቀበሌዎችም መብዛት ነው። የኢንዱስትሪው ልማት ቢስፋፋም ሠራተኛው ከሰው ብዛት የተነሣ ጉልበቱን በርካሽ መሸጥ ስለሚገደድ ብዙም ተጠቃሚ መሆኑን ለመናገር ያዳግታል። ታዲያ ቻይና ይህን ችግር እንዴት ነው የምትወጣው? ነገሩ በመሠረቱ ከዚህ ቀደም ያልታየ አዲስ ነገር አይደለም። የኢንዱስትሪው ዓለም ያለፈውና የሚያየው ጉዳይ ነው። ይሁንና በሕዝብ ብዛቷ ግዙፍ የሆነችው ቻይና በዚህ ተጨባጭ ሁኔታዋ የተነሣ ችግሩን በየዕድገቱ ደረጃ ለማረቅ መሞከር ብቻ ነው ምርጫዋ። ቅዠት ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም እንደሚባለው ቻይና ከምዕራቡ ዓለም ለመስተካከል የያዘችውን ውጥኗን ከግብ ሳታደርስ በዚህ እንደማትፋታ አንድና ሁለት የለውም።