የቻይናና የምዕራቡ ዓለም የንግድ ውዝግብ | ኤኮኖሚ | DW | 01.09.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የቻይናና የምዕራቡ ዓለም የንግድ ውዝግብ

አስታራቂ መንገድ በማፈላለግ ችግሩን ለመፍታት የተያዘው ጥረት እስካሁን ዘላቂ ውጤት አላስከተለም፤ ቢሆንም ልዩነቱን ለማጥበብ የሚደረገው የሁለት ወገን ጥረት በጥቂቱም ቢሆን ተሥፋ ሰጭ አዝማሚያን መያዙም ሌላው ገጽታው ነው።

ዛሬ በዓለም ላይ በየገበያው፤ በየመደብሩ ተደርድሮ ከሚገኘው የጨርቃ-ጨርቅ ምርት አብዛኛው ከቻይና የመነጨ ነው። በሕዝባዊት ቻይና ይህን ገበያ በሰፊው መቆጣጠር መብቃት የተነሣ መፎካከር ተስኗቸው ከባድ የኤኮኖሚ ውድቀት ስጋት ላይ የወደቁት ታዳጊ አገሮች ብቻ አይደሉም። ቻይና ለዓለም ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች ርካሽ መሆናቸው መፎካከር ላቃተው ለምዕራቡ ዓለም አምራችም ብርቱ ፈተና ነው የሆነው።

ለዚህም ነበር አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ቤይጂንግ የምትሸጠውን ምርቷን መጠን እንድትገድብ በማስጠንቀቅ ለዓለም ንግድ ድርጅት አቤት እስከማለት የደረሱትና ገበዮቻቸውን ለመጠበቅ አንዳንድ ገቺ ዕርምጃዎችን መውሰድ የተገደዱት። የአውሮፓ ሕብረት ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የቻይናን ጨርቃ-ቀርቅ ምርቶች የሚገድብ ደምብ ሲያሰፍን አሜሪካም ጥቂት ቀደም ብላ ተመሳሳይ ዕርምጃ መውሰዷ ይታወሣል።

እርግጥ ምዕራባውያኑ መንግሥታት የአምራቾቻቸውን ጥቅም ለማስከበር የወሰዷቸው የመከላከል ዕምጃዎች ጊዜያዊ እንጂ በኮታው መወገድ የተፈጠረውን ነጻ ንግድ ለዘለቄታው ሊገድቡ የሚችሉ አይሆኑም። ስለዚህም የቀድሞው የኮታ ውል ባስቀመጠው በሶሥት ዓመታት የተወሰነ የመሸጋገሪያ ጊዜ ውስጥ ይዞታቸውን ከገበያው ሁኔታ ማጣጣማቸው ግድ ነው።

የአውሮፓ ሕብረትና ቻይና በጉዳዩ ዘላቂ ከሆነ ስምምነት ለመድረስ ባለፈው ሣምንት አራት ቀናት የፈጀ ድርድር አካሂደው ነበር። ሆኖም ድርድሩ ሁለቱን ወገኖች ጥቂት ቢያቀራርብም የተሟላ መፍትሄን ሳያስከትል ለጊዜውም ቢሆን መቋረጡ ግድ ሆኖበታል። የአውሮፓው ልዑካን መሪ የብራስልሱ የንግድ ኮሜሣር ፔተር ማንደልሶን እንዳመለከቱት ሕብረቱ ባሰፈነው የንግድ ገደብ የተነሣ በየጉምሩኩ ታግዶ የሚገኘው የቻይና የአልባሣት ምርት ወደየገበያው እንዲዘልቅ አንድ ጊዜያዊ አስታራቂ መፍትሄ ተገኝቷል።

እርግጥ ማንደልሶን ከቤይጂንግ ይዘው የመጡት ሃሣብ ለ 25ቱ የሕብረቱ ዓባል መንግሥታት ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘት የሚኖርበት ጉዳይ ነው። ታዲያ በወቅቱ በሚታየው መቀራረብ ራሳቸው አልባሣት አምራች የሆኑት ኢጣሊያንና ስፓኝን የመሳሰሉት የአውሮፓ ሕብረት ዓባል መንግሥታት መደሰታቸው ያጠራጥራል። ሕብረቱ በቻይና ምርቶች ላይ ገደብ እንዲጥል ዋነኛውን ግፊት ያደረጉትም እነዚሁ አገሮች ነበሩ።

በሌላ በኩል በዚህ በአውሮፓ የሚገኙ የጨርቃ-ጨርቅ ምርት ነጋዴዎችና ኢንዱስትሪዎች ደግሞ በገደቡ ሳቢያ በመግባት ላይ በሚገኘው በልግና በተቃረበው የክረምት ወራት መደብሮች ባዶ እንዳይሆኑ እያሰጋ ነው ሲሉ የሚያደርጉት ግፊት ቀላል አልሆነም። ፔተር ማንደልሶን አባባሉን እምብዛም ትክክል አድርገው አልተመለከቱትም። ነጋዴዎች ያለፈው ሐምሌ ወር ገደብ ሊጸና ዋዜማ የቻይናን ምርቶች በገፍ በማስገባት በፍጥነት ኮታው ጣራ ላይ እንዲደረስ አድርገዋል ሲሉ ነው አሁን ለተፈጠረው ሁኔታ ሃላፊነቱ የኮሚሢዮኑ ብቻ እንዳልሆነ የሚናገሩት።

ሆኖም ማንደልሶን ሃሣባቸው የዓባል ሃገራቱንና የጨርቃ-ጨርቅ ኢንዱስትሪውን ድጋፍ እንዲያገኝ ተሥፋ ከመጣል ሌላ በወቅቱ ብዙ ምርጫ የላቸውም። የመጪው 2006 ዓ.ም. ኮታ አሁን በየወደቡ በተያዘው የቻይና ምርት ላይ እንዲታሰብ ቤይጂንግን ለማስገደድም አይችሉም። ጥቅሟን ለማስከበር ጠንካራ አቋም ከምታራምደው ከቻይና ጋር መደራደር ቀላል ነገር አይደለም።

በአንጻሩ የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካ ኢንዱስትሪዎች አሁን ለተፈጠረው የገበዮቻቸው በቻይና ምርቶች መጥለቅለቅ የራሳቸውም ድርሻ እንዳለበት የግድ መቀበል ይኖርባቸዋል። በዘርፉ የተፈጥረውን ሂደት በሚገባ አጢነው ይዞታቸውን በጊዜው ከተጨባጩ ሁኔታ ለማጣጣም የረባ ወይም ቁርጠኛ ለውጥ አላደረጉም። ቻይና በበኩሏ የነጻውን ንግድ መሠረተ-ዓላማ በመከተል ነጻ ፉክክር ማድረግ ትችላለች። በተለይ የጨርቃ-ጨርቁ ኮታ ውል ካበቃ ወዲህ ይህን ዓላማ ያላንዳች ገደብ ለማራመድ የሚቀራት እስከ 2008 የሚዘልቀው የመሸጋገሪያው ሶሥት ዓመት ጊዜ ብቻ ነው የሚሆነው።

በዚሁ የጨርቃ-ጨርቅ ንግድ ጉዳይ ከቻይና ጋር ስትወዛገብ የቆየችው አሜሪካም በመጪው ሣምንት አጋማሽ ላይ ጉዳዩ በመሪዎች ደረጃ ከመነሣቱ በፊት የሃሣብ መቀራረብ እንዲገኝ ግፊት እያደረገች ነው። ዋሺንግተን የቻይናን ጨርቃ-ጨርቅና የአልባሣት ምርቶች ጎርፍ ለመግታት ጥብቅ ቁጥጥር ካሰፈነች ወዲህ ሁለቱ አገሮች ችግሩን ለመፍታት እስካሁን ሶሥት ዙር ንግግሮች አካሂደዋል።
በቅርቡ ሣን ፍራንሢስኮ ላይ ተገናኝተው ከስምምነት መድረስ ሳይችሉ የቀሩት የቻይናና የአሜሪካ ተደራዳሪዎች የጋራ መፍትሄ ለማግኘት ተሥፋ በመጣል ከትናንት በስቲያ አራተኛ ዙር ንግግር ጀምረዋል። ድርድሩ የሚካሄደው ሁለቱም ወገኖች ስምምነትን ለማስፈን ጠንካራ ግፊት አድሮባቸው በሚገኝበት ሁኔታ ነው።

የድርድሩ ፍሬ መስጠት በፊታችን ጳጉሜ 2 ቀን የሁለቱ መንግሥታት ፕሬዚደንቶች ለሚያካሂዱት ንግግር መልካም ሁኔታን እንደሚያመቻች ይጠበቃል። ፕሬዚደንት ሁ ጂንታዎና ጆርጅ ቡሽ የሚያካሂዱት ንግግር የሰሜን ኮሪያን የአቶም መርሃ-ግብር የመሳሰሉ ዓለምአቀፍ ጥያቄዎችን የሚጠቀልል ቢሆንም አሜሪካ ከቻይና ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ ያለባት ከፍተኛ የበጀት ኪሣራም አንዱና ዋናው ጉዳይ ነው።

አዝማሚያው ከሁለቱም ወገን ልዩነቱ እየጠበበ መምጣቱንና ውል የማስፈኑ ዕድል የተሻለ መሆኑን ነው የሚያመለክተው። እንዲያውም በዚህ በወቅቱ ዋሺንግተን ላይ በተያዘው አራተኛ ዙር ድርድር ውል መስፈን ይችል ይሆናል የሚል ተሥፋ አለ። ዋሺንግተን የምትደራደረው እስከ 2008 ማለት በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት ቻይና ወደ አሜሪካ ገበዮች የምታስገባውን ምርት የሚወስን አጠቃላይ ውል ዕውን ለማድረግ ነው።

ወደአገር ምርት የሚያስገቡ የአሜሪካ ነጋዴዎች በበኩላቸው የወቅቱ ገደብ ለዋጋ መናር መንስዔ በመሆን ተጠቃሚውን ጎድቷል ሲሉ የቻይናን ንግድ ቢያንስ በሃያና ሰላሣ በመቶ የሚያሳድግ ውል እንዲሰፍን ይጠይቃሉ። በሌላ በኩል የአሜሪካ ጨርቃ-ጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች የቻይናን ምርት የሚገድብ ይበልጥ የጠነከረ ውል መስፈን ይኖርበታል ባዮች ናቸው።

በአጠቃላይ የአሜሪካና የአውሮፓ አምራቾች የቻይና ኢንዱስትሪዎች በሚገለገሉበት ርካሽ የሥራ ጉልበት፣ መንግሥታዊ ድጎማና ምርቶችን የመኮረጅ ነጻነት ተገቢ ያልሆነ ተጠቃሚነት አላቸው ሲሉ ማንኛውም ውል ይህን ልዩነት ያጤነ እንዲሆን ነው የሚያሳስቡት። ግን ቤይጂንግ በቀላሉ የምትገፋ መሆኗ ሲበዛ ያጠራጥራል።

ሰሞኑን የነዳጅ ዘይት ዋጋ በበርሚል ከሰባ ዶላር በላይ መናሩ በአንድ በኩል በዚህ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸገው ዓለም ለአውቶሞቢል አሽከርካሪዎችና በክረምቱ ወራት ቤቶቻቸውን በዘይት ለሚያሞቁት ለብዙሃኑ ፈተና ሲሆን በሌላ በኩል አምራች ለሆኑ የአፍሪቃ አገሮች የኤኮኖሚ መድህን ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው።

አንዳንድ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት እነዚህ አምራች የሆኑት ጥቂት አገሮች በወቅቱ የዋጋ መናር የሚገኘውን ከፍተኛ ገቢ ተጠቅመው የኤኮኖሚ ይዞታቸውን አንድ ወጥ ባሕርይ በመቀየር ድህነትን ለመቀነስ ድርጅቱ ያወጣውን የሚሌኒዬም ዕቅድ ከግቡ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ያምናሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የኤኮኖሚና የማሕበራዊ ጉዳይ ዋና አማካሪ ቤሪይ ሄርማን ባለፈው ሰኞ እንዳሉት የነዳጅ ዘይት ዋጋ አሁን ባለበት ደረጃ ይህን ሁሉ ለማድረግ ግሩም አጋጣሚ ነው። በሄርማን አመለካከት በወቅቱ በሁኔታው ተጠቃሚ የሆኑት ናይጄሪያን፣ አንጎላንና ኤኩዋቶሪያን ጊኒን የመሳሰሉት አገሮች የነዳጅ ዘይት ዋጋ ውጣ-ውረድ የሚኖርበት መሆኑን ተገንዝበው የገንዘብ አጠቃቀም ስልታቸውን ማጣጣም ይኖርባቸዋል።

የኤኮኖሚው ጠቢብ በዚህ በኩል ናይጄሪያን አርአያ አድርጎ መውሰዱ እንደሚጠቅም ይናገራሉ። ናይጄሪያ ከገበያው ከምታገኘው ገቢ የተወሰነውን ለክፉ ጊዜ በማስቀመጥና ሁኔታውንም በመጠቀም በነዳጅ ዘይት ምርት ላይ ያለባትን ጥገኝነት ለማስወገድ ኤኮኖሚዋን ለማስፋፋት ዕድሉን ትጠቀምበታለች። በነዳጅ ዘይቱ ዋጋ መናር የተገኘውን ጥሩ አጋጣሚ በተቀናበረ ሁኔታ መጠቀም ያስፈልጋል ማለት ነው። ግን ይህ የሚሌኒየሙን ዕቅድ ገቢር ለማድረግ ብቻውን መብቃቱ የሚያጠራጥር ነው። ሰፊ የውጭ ዕርዳታ ወደፊትም ማስፈለጉ የማይቀር ነገር ነው።

ወደ አውሮፓ መለስ እንበልና የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከመጠን በላይ መናር መንግሥታቱን ለአንዳንድ ከዚህ ቀደም ላልተለመደ ዕርምጃ ማነሣሣት ይዟል። የቤልጂጉ የገንዘብ ሚኒስትር ዲዲዬር ሬይንደርስ ለምሳሌ በዓመቱ መጨረሻ እያንዳንዱን ቤተሰብ በ 75 ኤውሮ በመደጎም በነዳጅ ዘይቱ ዋጋ መናር የደረሰበትን ጉዳት ለማለዘብ ባለፈው ሰንበት ሃሣብ አቅርበው ነበር። ይህን ለቤልጂግ መንግሥት ሶሥት መቶ ሚሊዮን ኤውሮ የሚሆነውን ወጪ አንድ የአውሮፓ የኤኮኖሚ ጠቢብ በሰሜን ባሕር ላይ የሚጣል የአንዲት ጠብታን ያህል ነው ሲሉ ፍሬ እንደማይሰጥ አስገንዝበዋል። ሌላ የተሻለ መፍትሄ መፈለጉ ግድ ይሆናል ማለት ነው።