የቻንስለር አንጌላ ሜርከል የአፍሪቃ ጉብኝት፤አፍሪቃዉያን ስደተኞች በየመን | አፍሪቃ | DW | 04.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የቻንስለር አንጌላ ሜርከል የአፍሪቃ ጉብኝት፤አፍሪቃዉያን ስደተኞች በየመን

የጀርመኗ  ቻንስለር  አንጀላ  ሜርከል ያለፈዉ ረቡዕ ነበር ቡድን 5 በመባል የሚታወቁትን የሳህል ሀገራት ጉብኝት የጀመሩት።ቡድን 5 ቡርኪናፋሶን፣ማሊን፣ኒጀርን፣ ሞሪታንያና ቻድን የመሳሰሉ የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራትን የሚያጠቃልል ሲሆን ቻንስለሯ በዕነዚህ ሀገራት የ3 ቀናት ጉብኝት አድርገዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:01

የሜርከል የሞዕራብ አፍሪቃ ጙብኝት፤

የጉብኝታቸዉ ዓላማም ለዕነዚህ ሀገራት ፖለቲካዊ ድጋፍ ማሳየት ነዉ። ሀገራቱ በሽብርተኝነት ጫና ዉስጥ የሚገኙ በመሆናቸዉም የቻንስለሯ የሳህል ሀገራት ጉዞ በቀጠናዉ ሰላምና መረጋጋት ስለሚመጣበት ዘዴ ለመምከር ጭምር ነዉ።  ለ2 ዓመት በሚዘልቅ የፀረ-ሽብር ተልዕኮ ላይ በጋራ እየሰሩ ለሚገኙት የቡድን 5 የሳህል አካባቢ ሀገራት ቻንስለሯ ድጋፋቸዉን ማጠናከርም ይፈልጋሉ።
ቻንስለር አንጌላ ሜርከል ያለፈዉ ረቡዕ ጉብኝታቸዉን የጀመሩት በቡርኪናፋሶ ዋና ከተማ ዋጋ ድጉ የ5ቱን የሳህል አካባቢ ሀገራት መሪዎች በማነጋገር ነበር።በዉይይቱም   ሽብርተኝነትና የስደተኞች ጉዳይ ዋና መነጋገሪያ ነበር።
ቡድን 5 የሚባሉት የማሊ፣የኒዠር፣የቡርኪና ፋሶ፣የቻድና የሞሪታንያ መንግስታት አሸባሪዎችን  የሚወጋ 5ሺህ ወታደሮች የያዘ የጋራ ጦር አደራጅተዋል።ጦሩ «አሸባሪዎች» በሚላቸዉ ኃይላት ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ቢሰነዝርም በተለይ ማሊንና ቡርኪናፋሶን በየጊዜዉ ከሚፈፀምባቸዉ ጥቃት ማዳን አልቻለም።
ሀገራቱ ሽብርተኝነትን ለመቆጣጠር በተናጠልም ጥረት ያደርጋሉ ያም ሆኖ ግን  የሚፈለገዉን ያህል ዉጤት ግን እስካሁን ማምጣት አልመቻላቸዉ ነዉ የሚነገረዉ። ቻንስለሯ ወደ ቦታዉ ከማምራታቸዉ ከ3 ቀናት በፊት እንኳ ሰሜናዊ ቡርኪናፋሶ በሚገኝ አንድ የኢባንጀሊካን ቤተክርስቲያን የ6 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ የሽብር ጥቃት መፈፀሙ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነዉ።
ለዚህም ይመስላል ሜርከል ከቡርኪናፋሶዉ ዉይይት በኋላ በአሸባሪዎች ላይ ፈጣንና የተባበረ ርምጃ መወሰድ አለበት ያሉት።ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም የአካባቢዉን መንግስታት መደገፍ ይኖርበታል ይላሉ ሜርከል።


«አሸባሪዎች የሚያደርሱት ጥቃት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ከሚደርሱት ጥቃት መረዳት ይቻላል።ፕሬዝዳንቶቹ በትክክል እንዳስታወቁት አሸባሪዎችን መዋጋት ዓለም አቀፋዊ ተግባር ነዉ።ለዚህም ነዉ ለቡድን 5 የሳህል ሀገራት ተልዕኮ  የተባባሩት መንግስታት ድርጅት እዉቅናና ድጋፍ መስጠት እንዳለበት የምመኔዉና የምገነዘበዉ።»
ቀጠናዉ ከሽብርተኝነትን ጥቃት ነፃ ለማድረግ የተቋቋመዉ የ5ቱ ሀገራት የጋራ ጦር ዉጤታማ አለመሆን ከገንዘብ ድጋፍ ጋር የተያያዘ ነዉ የሚሉ አሉ።የቡድን 5 ሀገራት የጋራ ጦር ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የ400 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ  የሚያስፈልገዉ ሲሆን ከዚህ ዉስጥም ከአዉሮፓ 100 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠበቅ ነበር። ያም ሆኖ ግን ለጦሩ ዘመቻ የአዉሮጳ ሕብረት እስካሁን የሰጠዉ ድጋፍ አነስተኛ  መሆኑ ነዉ የሚነገረዉ። እናም ሜርከል ሀላፊነቱ ለሳህል አካባቢ ሀገራት ብቻ መተዉ የለበትም ይላሉ።
«ሀላፊነቱ የዕነዚህ አምስት ሀገሮች ብቻ አይደለም የአዉሮፓ ጭምር እንጅ።ምክንያቱም ችግሩን ማንኛዉንም ዋጋ ከፍለን ማስወገድ እንፈልጋለን።ይህም በሊቢያና በሌሎች አካባቢዎች ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማምጣት ግልፅ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ይህ በተደጋጋሚ የሚያስጨንቀን በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነዉ።ምክንያቱም ቦታዉ አዲስ የሽብር ስጋት መፈልፈያ  ይሆናል የሚል ስጋት አለን።»
እንደ ቻንስለር አንጌላ ሜርከል ከሁሉም በላይ የአዉሮፓዉያን ምላሽ  ፈጣን መሆን ይኖርበታል ።
«እኛ አዉሮፓዉያን የበለጠ ምላሽ መስጠት አለብን ። በፍጥነት ማከናዎንም አለብን።አንዳንድ ነገሮች ላይ እንቅስቃሴ አለ።ነገር ግን አንዳንድ ነገሮችን ተጨባጭ ለማድረግ  አሁንም ድረስ ትግል አለ።ለዚህም ነዉ ፤ሁኔታዎች በፍጥነት ሲፈፀሙና  በፍጥነት ሲተገበሩ ማየት አጥብቄ የፈለኩት። ምክንያቱም መታመን እንፈልጋለን ፈተናዎቹም ብዙ ናቸዉ። »
በቡርኪናፋሶ ከፕሬዝዳንት ሮክ ማርክ ካቦሬ ጋራም ድህነት የወለደዉ የፀጥታ ስጋት በሀገሪቱ እየተባባሰ ስለመምጣቱ በተናጠል ዉይይት አድርገዋል። ቡርኪናፋሶ የበለፀጉት  የቡድን 20 ሀገራት «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ» በሚል ማዕቀፍ በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት  ድጋፍ ከሚደረግላቸዉ የአፍሪቃ ሀገራት አንዷ በመሆኗ ፤በሀገሪቱ ለመዋዕለ ንዋይ ፍሰት የሚመች ሁኔታ ለመፍጠርና የሀገሪቱን የፖሊስ ሰራዊት ለማጠናከርም 10 ሚሊዮን ዮሮ ድጋፍ እንደሚያገኙ ለፕሬዝዳንቱ ቃል ተገብቶላቸዋል።
ሜርክል ከቡርኪናፋሶ በቀጥታ ያመሩት ወደ ማሊ ነበር። በማሊ ጉብኝታቸዉ  ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሀገሪቱ  የሠፈሩ የጀርመን ወታደሮችን ጎብኝተዋል።ጀርመን በሰሜናዊ ማሊ 850 ወታደሮች አሏት።


ሞራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር  ኒጀር  የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርከል የመጨረሻዉ የጉብኝት ቦታ ነበር።በዚያም ከኒጀር ፕሬዝዳንት ማህሙዱ አይሶፉ ጋር በመዲናዋ ኒያሚ የመክረሩ ሲሆን  የጎረቤት ሊቢያ ቀዉስ እንዲሁም ናይጄሪያ የሚገኔዉ ቦኩሃራም የተባለዉ የሽብር ቡድን በኒጀር አለመረጋጋትን እየፈጠረ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል። ሀገሪቱን በማረጋጋቱ  ስራም  ሀገራቸዉ ጀርመን ፕሬዝዳንቱን ለመርዳት ዝግጁ መሆኗን ቻንስለሯ ቃል ገብተዋል። በሌላ በኩል ኒጀር በአመት 150 ሺህ የሚደርሱ ወደ አዉሮፓ ለመሻገር የሚፈልጉ  ስደተኞች የሚተላለፉባት ሀገር በመሆኗ የስደተኞች ጉዳይ ሌላዉ የመነጋገሪያ አጀንዳ ነበር።በዉይይቱም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር በሊቢያ መዉጫ ያጡ ስደተኞችን ተገን ወደ ሚያገኙበት ሀገር እስኪሄዱ ድረስ  በኒጀር እንዲሰፍሩ ለማድረግ የተነደፈዉን መርሃ -ግብር ለማገዝ ፤እንዲሁም  ወታደራዊና ሌሎች ጤናንና ትምህርትን የመሳሰሉ የሀገሪቱን ማህበራዊ ተቋማት ለመደገፍ ስለሚቻልልበት ሁኔታ መሪዎቹ መክረዋል። ሁለት ሶስተኛዉ የሀገሪቱ ክፍል በማይምነት ለሚኖርባት ኒጀር ለዉሃ ጉድጓዶችና ለትምህርት ቤቶች ግንባታ የሚዉል 10 ሚሊዮን ዩሮ ለመደገፍም ጀርመን ቃል ገብታለች።
አዉሮፓም ይሁን ጀርመን የቀጠናዉን  ሀገራት የመደገፍ  የተለዬ ፍላጎት አላቸዉ ።ምክንያቱም ስደተኞችን ወደ አዉሮፓ የሚገፋ የድህነት፤የሽብር ጥቃትና ሌሎች የፀጥታ ችግሮች በነዚህ ሀገራት ከፍተኛ ነዉና።

አሪቃዉያኑ ስደተኞች በየመን፤
የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ ሳዉዲ ዓረቢያ ለመሻገር በጦርነት ወደ በምትታመሰዉ የመን የሚገቡ የምስራቅ አፍሪቃ ስደተኞች በርካቶች ናቸዉ። እነዚህ ስደተኞች አደገኛዉን የባህርና የየብስ ጎዞ ጨርሰዉ ወደ የመን ሲገቡ የሚያጋጥማቸዉ ችግር ያልጠበቁት ነዉ።በመሆኑም ስደተኞቹ ለረሀብ ፣ለበሽታ ፣ለእንግልትና ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ።ዓለም ዓቀፉ የስደት ድርጅት ሰሞኑን እንዳስታቀዉ በኤደን ከተማ የዕግር ኳስ ስታዲየም ከተጠለሉ ስደተኞች ዉስጥ፤ በቅርቡ 8 ሰዎች በኮሌራ በሽታ ህይወታቸዉ አልፏል።እንደ ድርጅቱ የስደተኞች ሁኔታ በአካባቢዉ አስከፊ በመሆኑ ቋሚ መፍትሄ ያስፈልገዋል።
"በስታዲየሙ ውስጥ ያለው የሰብአዊ ሁኔታ በጣም አስከፊ ነው,።በመሆኑም  ከተባበሩት  መንግስታት ድርጅትና፣መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከሌሎች ተባባሪዎች ጋር አስፈላጊ የሆኑትን  መሠረታዊ  ፍላጎቶችን ለማሟላት  እየሰራን ነው።ግን ይህ ቋሚ መፍትሄ አይደለም።በቀጣይ ምንም ቢፈጠር  እነዚህ ስደተኞች ወደ የትኛዉም ቦታ ቢጓዙ ክብርን በጠበቀና ሰብዓዊ መንገድ መከናወን አለበት።"
የተባበሩት  መንግስታት  ድርጅት በአካባቢዉ ስደተኞችን ለመርዳት ጊዜያዊ  የህክምና ማእከሎችን  አቋቁሞ ህጻናትን ጨምሮ 200 ያህል በሽተኞችን በመርዳት ላይ ቢሆንም በሌላ በኩል በፀጥታ ሀይሎች የሚገደሉ መኖራቸዉም ይነገራል።ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ 2 ሰዎች ከጸጥታ ሀይሎች በተኮሰ ጥይት ቆስለዋል።ያም ሆኖ ግን አሁንም ድረስ ያለ በቂ መረጃ ወደ የመን የሚመጡ የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት ስደተኞች በርካቶች ናቸዉ።
«የመጣነው  ከሳምንት በፊት ከኢትዮጵያ ነው። 5 ሺህ ሰዎች በአንድ ቡድን ዉስጥ ነበርን። ጦርነት አለ ብለን አላሰብንም ነበር። ነገር ግን ጦርነትና ብዙ ችግር አለ።"
የመን ከጎርጎሮሳዊዉ 2015 ዓ/ም ጀምሮ በጦርነት የምትታመስ ሀገር ስትሆን በዚህ ሳቢያ 22 ሚሊዮን ማለትም 80 በመቶ የሀገሪቱ ዜጎች  የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።3 ሚሊዮን ሰዎች ሀገር ለቀዉ ተሰደዋል። በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለሞት መዳረጋቸዉን ዘገባዎች ያሳያሉ።

ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic