የቺቦክ ታጋቾች | አፍሪቃ | DW | 16.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የቺቦክ ታጋቾች

በናይጀሪያ አሸባሪው ቡድን «ቦኮ ሃራም» ልክ ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ በምትገኘው የቺቦክ መንደር አንድ ትምህርት ቤት አጥቅቶ 276 ሴት ተማሪዎችን አገተ። አንዳንዶቹ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከአጋቾቻቸው ማምለጥ ተሳካላቸው፣ የሌሎቹ እጣ ግን እስካዘሬ አይታወቅም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:21
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:21 ደቂቃ

ቺቦክ

የተማሪዎቹ መታገት ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቶ፣ «ሴቶች ልጆቻችንን አምጡልን» የሚሰኝ ዘመቻ መጀመሩ ይታወሳል፣ ዛሬ ከሁለት ዓመት በኋላም የታጋቾቹ ወላጆች እና ጉዳዩ ያሳሰባቸው ተሟጋቾች ይህንኑ ጥያቄአቸውን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል። የታጋቾቹ ወላጆች ባንድ በኩል መሪር ሀዘን ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥታቸው አኳያ ብርቱ ቁጣ እንደሚሰማቸው ያነጋገረችው የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ካትሪን ጌንስለር ገልጻለች።

የእገታውን ሁለተኛ ዓመት ለማስታወስ ብዙ ሰዎች በቺቦክ መንደር በአንድ ትልቅ ዛፍ ስር ተሰብስበው በአንድነት የፀሎት ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል። የታጋቾች ወላጆች ወንጀሉ ከተፈፀመ ከሁለት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቺቦክ በመገናኘት ይህንኑ አሳዛኝ ወቅት በጋራ አስበውታል። እጎአ ሚያዝያ 15፣ 2014 ዓም ሌሊት ነበር የአሸባሪው የቦኮ ሀራም ቡድን ሚሊሺያዎች በ16 እና 18 ዓመት መካከል የነበሩ 276 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጃገረድ ተማሪዎችን ከተኙበት ቀስቅሰው በኃይል የወሰዱዋቸው። 57 ወዲያው አምልጠው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቢቀላቀሉም፣ 219 እስከዛሬ የት እንደደረሱም ሆነ በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ ሳይታወቅ ጠፍተው ቀርተዋል። ሳራያ ስቶቨር አንዷ ናት፣ የሳራያ እናት ሞኒካ ስቶቨር ልጇ በሕይወት መኖሯን ትጠራጠራለች።


« ገና ስለ እገታው ስሰማ ነበር ተስፋ የቆረጥኩት። ልጄን እንደገና በሕይወት አያታለሁ ብዬ ለማሰብ አልችልም። »
ከቀራት ጥቂቶቹ የልጇ ማስታወሻ አንዱ የሆነውን ፎቶግራፏን የምታሳየው ሞኒካ ስቶቨር ልጇን ማጣቷ ብቻ አይደለም አብዝቶ የሚያበሳጫት፣ በእገታው አኳያ የናይጀሪያ መንግሥት የተከተለው አሰራር ም በጣም ቅር እንዳሰኛት ነው የገለጸችው።
« ከመንግሥት በኩል መጥቶ ያነጋገረን የለም። ለታጋቾች ወላጆች ምንም አልተደረገም። ይደረጋል ስለሚባለው ነገር የምንሰማው ከመገናኛ ብዙኃን ነው። እስካሁን ያነጋገሩን ሙርታላ ሙሀመድ ተቋምን በመሳሰሉ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች ብቻ ናቸው። ከናይጀሪያ መንግሥት ግን እስካሁን ያየነውም ሆነ የሰማነው ነገር የለም። »
ቦኮ ሀራም ከሁለት ዓመት በፊት ያገታቸው ልጃገረዶች ወላጆች ከትናንት በስቲያ በቺቦክ ተገናኝተው እገታውን ያሰቡበትን የፀሎት ሥነ ሥርዓት ያዘጋጀው ሙርታላ ሙሀመድ ተቋም ነው። የሙርታላ ሙሀመድ ተቋምን የሚመሩት ወይዘሮ አይሻ ሙሀመድ ኦይቦድ ሲሆኑ፣ እጎአ በ1976 ዓም የተገደሉት የቀድሞው የናይጀሪያ ወታደራዊ መሪ ልጅ ናቸው። ወይዘሮ አይሻ ደብዛቸው የጠፉትን ልጃገረዶች ወላጆች በተደጋጋሚ ጎብኝተዋል። ይሁንና፣ ወደ ቺቦክ መንደር ሲመጡ የመጀመሪያ ጊዚያቸው ነው። ከባድ የጦር መሳሪያ በታጠቁ የናይጀሪያ ጦር አባላት ጥበቃ ተደርጎላቸው ወንጀሉ ወደተፈፀመበት ቦታ የሄዱት እና ባዩት ሁሉ ጥልቅ ሀዘን የተሰማቸው ወይዘሮ አይሻ ወደፊትም የታጋች ወላጆችን ለመርዳት እና ታጋቾችን ለማስለቀቅ ጠንክረው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
« የታገቱት ሴቶች ልጆቻቸው ያሉበት ቦታ እንዲታወቅ እና እንዲገኙ ወደፊትም መስራታችንን እንቀጥላለን። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ፣ በቺቦክ ሕፃናት እና ወጣቶች ካለስጋት እንደገና ወደ ትምህርት ቤት መሄድ የሚችሉበትን ዋስትና ማረጋገጥ እንፈልጋለን። በመጨረሻም፣ ትምህርት ቤቱ እንደገና የሚገነባበት ርምጃ ጥሩ ምልክት ይሆናል ብየ አስባለሁ። »
ትምህርት ቤቱ አሸባሪዎቹ የቦኮ ሀራም ሚሊሺያዎች ከሁለት ዓመት በፊት 276 ን ልጃገረዶች ባገቱበት አስከፊ ጥቃት ወድሞዋል።
ጉዳዩ ያሳሰባቸው ናይጀሪያውያን ተሟጋቾች የቺቦክ ልጃገረዶች ከታገቱ ወዲህ፣ በየቀኑ በአስራ አንድ ሰዓት በመዲናይቱ አቡጃ የአንድነት ምንጭ በተባለው ቦታ እየተሰበሰቡ ማሳሰቢያ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።
« ምን እየጠየቅን ነው? አሁኑኑ «ሴቶች ልጆቻችንን» በሕይወት አምጡልን»። »
ተሟጋቾቹ በዚሁ ጥያቄአቸው የቺቦክ ታጋች ተማሪዎች ተረስተው እንዳይቀሩ እና የናይጀሪያ መንግሥትም ለታጋች ወላጆች በገባው ቃል መሰረት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስድ ነው ጥረት እያደረጉ ያሉት። በቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን የስልጣን ዘመን የታገቱትን ልጃገረዶች ለማስለቀቅ የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ጆናታንን የተኩት ፕሬዚደንት ሙሀማዱ ቡሀሪ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።


« የናይጀሪያ መንግሥት ታጋቾቹ ልጃገረዶች ከቤተሰባቸው ጋር መልሰው እሲኪቀላቀሉ ድረስ አርፎ እንደማይቀመጥ አረጋግጥላችኋለሁ። »
የታገቱት ልጃገረዶች ግን የት እንዳሉ እንደማያውቁም ነበር ያስታወቁት።
እንደ ታጋች ወላጆች ተጠሪ ያኩቡ ንኬኪ አስተያየት፣ የቺቦክን እገታ ማከላከል ይቻል ነበር። ይህም በጣም እንዳስቆጣቸው ገልጸዋል።
« ልጃገረዶቹ እዚህ በነበሩበት ጊዜ አስፈላጊው ጥበቃ አልተደረገላቸውም። ካላንዳች ከለላ ብቻቸውን ነው የነበሩት። በቺቦክ መንደር የተሰማሩት ወታደሮች ቁጥር 15 ብቻ ነበር። አካባቢው አስተማማኝ እንዳልሆነ እና 15 ወታደሮችም ያካባቢውን ጥበቃ ሊያረጋግጡ እንደማይችሉ ያኔ በሚገባ እናውቅ ነበር። »
ይሁን እንጂ፣ የቺቦኩ እገታ አሸባሪው ቡድን የፈፀመው ብቸኛው እገታ አልነበረም። ከዚያ ወዲህ በተከተሉት ዓመታትም በሺዎች የሚቆጠሩ ልጃገረዶች፣ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች የቦኮ ሀራም እገታ ሰለባ ሆነዋል። በቦኮ ሀራም ቁጥጥር ስር የገቡት ሰዎች ቁጥር በውል አይታወቅም። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከአሸባሪው ቡድን ቁጥጥር ማምለጥ የቻሉ ወይም ቡድኑ የለቀቃቸው ልጃገረዶችን በመጥቀስ እንዳመለከተው፣ ቦኮ ሀራም ያገታቸውን ለወሲብ ወይም ለተዋጊነት ይጠቀምባቸዋል ወይም ለአካለ መጠን ያልደረሱትን ታጋቾች፣ በተለይም ሴቶችን በአጥፍቶ ጠፊነት እንዲሰሩለት ያስገድዳል።
የቦኮ ሀራም ጥቃት እና እገታ ተግባር በሰለባዎቹ እና ጥቃቶቹ በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች ላይ የረጅም ጊዜ መዘዝ ማስከተሉ አልቀረም። ሬቤካ ኢስያኩ ለምሳሌ ከቦኮ ሀራም እገታ ማምለጥ ከቻሉት ከ276 የቺቦክ ታጋቾች መካከል አንዷ ናት። ዛሬ ከሁለት ዓመት በኋላም፣ ሬቤካ ሀሳቧ አሁንም በአሸባሪው ቡድን ቁጥጥር ስር ካሉት አቻዎቿ ጋር ከመሆኑ በስተቀር ስለያኔው እገታ መናገር አትችልም።


« እስከዛሬ ድረስ ይመለሱ ይሆን እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። በሕይወት ይኑሩ እንኳን አላውቅም። ያም ቢሆን ሁሌ ከሀሳቤ አይጠፉም። »
ሬቤካ በአሁኑ ጊዜ በመዲናይቱ አቡጃ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ናት። በቦኮ ሀራም ጥቃት ሰበብ የሞኖሪያ አካባቢያቸውን መልቀቅ የተገደዱ ሌሎች ብዙዎቹ ወጣቶች ግን ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አይችሉም። የተመድ በቅርቡ ያካሄደው ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው፣ በወቅቱ በሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ እና በጎረቤት ካሜሩን ወደ 700,000 የሚጠጉ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ከሄዱ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፣ ከ1,800 የሚበልጡ ትምህርት ቤቶች አንድም በእሳት ጋይተዋል ወይም በፀጥታ ምክንያት ተዘግተዋል። እርግጥ፣ የናይጀሪያ መንግሥት በሌላ ቦታ አማራጭ ትምህርት ቤት ለመክፈት ቃል ገብቶዋል። ይሁንና፣ መንግሥት በዚሁ መሰረት የሚገባውን ሁሉ እያደረገ አለመሆኑን የመብት ተሟጋቹ ድርጅት፣ «ሂውመን ራይትስ ዎች» ባለደረባ ማውዚ ሴጉን ተናግረዋል።
« የቦኮ ሀራም ዓመፅ ከተጀመረ ስድስት ዓመት በላይ ሆኖታል። ቢያንስ ከሁለት እና ሶስት ዓመታት ወዲህ ለምሳሌ በቦርኖ ፌዴራዊ ግዛት ትምህርት እንደበፊቱ እንዲቀጥል ማድረጉ ላይ ችግር አለ። ያም ቢሆን ግን ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ካልቻሉት ተማሪዎች መካከል ሶስት ከመቶውን ብቻ ነው በሌላ ቦታ ማስተማር የተቻለው። ይህም በቂ ስራ እየተሰራ አለመሆኑን አረጋግጦዋል። »
የቺቦክ ታጋቾች እና በሌሎች የሰሜን ናይጀሪያ አካባቢዎች የሚኖሩት ወላጆችም ልክ እንደ ማውዚ ሴጉን የሀገራቸው መንግሥት ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ያህል እየሰራ አለመሆኑን አመልክተዋል።

ካትሪን ጌንስለር/አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች