የቶጎ ፖለቲካዊ ቀዉስና የተቀናቃኞች ስምምነት | የጋዜጦች አምድ | DW | 26.04.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የቶጎ ፖለቲካዊ ቀዉስና የተቀናቃኞች ስምምነት

ሥምምነቱ-እንደተደረገ፣ እንደተነገረዉ ገቢር ከሆነ የትንሺቱ ሐገር ፖለቲከኞች በርግጥ ዘየዱ-ነዉ የሚያሰኝ።የወቅቱን የአፍሪቃ ሕብረት የሊቀመንበርነት ሥልጣን የያዙት የናጀሪያዉ ፕሬዝዳት ኦሉሴጎን አባ ሳንጆም በሳል-ፖለቲከኛ ክቡር ሽማግሌነታቸዉን አስመሰከሩ ያስባለ ነበር።

የቶጎ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ማሕበራት መሪዎች ብሔራዊ ተጣማሪ መንግስት ለመመስረት ተስማሙ።ቶጎን ለረጅም ዘመናት የመሩት ግናሲንግቤ ያዴማ ባለፈዉ የካቲት ከሞቱ ወዲሕ የተቀሰቀሰዉ ዉዝግብ ደም እስከማፍሰስ ደርሶ ነበር።ባለፈዉ እሁድ የተደረገዉ አወዛጋቢ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዉጤት አልታወቀም። በናይጄሪያዉ ፕሬዝዳንት ኦሌ ሴጎን ኦባሳንጆ ሸምጋይነት የተደራደሩት የሐገሪቱ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ዛሬ እንዳስታወቁት ግን የምርጫዉ ዉጤት ምንም ሆነ ምን ተጣማሪ መንግስት ይመሰርታሉ።ይሁንና ስምምነቱ ከተነገረ ከጥቂት ሰአታት በሕዋላ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አልተስማንም ማለታቸዉ ተሰምቷል።

ሥምምነቱ-እንደተደረገ፣ እንደተነገረዉ ገቢር ከሆነ የትንሺቱ ሐገር ፖለቲከኞች በርግጥ ዘየዱ-ነዉ የሚያሰኝ።የወቅቱን የአፍሪቃ ሕብረት የሊቀመንበርነት ሥልጣን የያዙት የናጀሪያዉ ፕሬዝዳት ኦሉሴጎን አባ ሳንጆም በሳል-ፖለቲከኛ ክቡር ሽማግሌነታቸዉን አስመሰከሩ ያስባለ ነበር።ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ስምምነቱ መደረጉ ከተነገረ ከጥቂት ሰአታት በሕዋላ አለመስማማታቸዉን ማስታወቃቸዉ ግን ጉዳዩን በንጥልጥል አስቀርቶታል።

ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ እዚያዉ ናጄሪያ በስደት የሚኖሩት የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሕብረት መሪ ዢልክርስቲን ኦሎፖዮንና የቀድሞዉን የቶጎ አምባገነን መሪ ልጅ ሮር ግናሲንግቤን ካስማሙ በሕዋላ «የቶጎ ነባራዊ ሁኔታ-ዛሬ ዲሞክራሲ የምንለዉን ሥርአት ሙሉ በሙሉ ገቢር ለማድረግ የሚፈቅድ አይነት አይደለም።» ብለዋል።የምርጫዉ ዉጤት ከመታወቁ በፊት ተጣማሪ መንግስት ለመስረት ድርድር ስምምነት ያስፈለገዉም ለዚሕ ነዉ።

ቶጎ ኦባሳንጆ አክለዉ እንዳሉት ለሰላሳ-ስምንት ዘመን የአንድ ሰዉ መንግስት ፀንቶባት የቆየች ሐገር ናት።የጌናሲንግቤ ያዴማ።ያዴማ ብዙዎቹ የአፍሪቃ አምባገነነ ብጤዎቻቸዉ እንዳደረጉት ሁሉ የምዕራቡን ግፊት ለማርካት-ሕዝቡን ለመሸንገል ያሕል ምርጫ ጠርተዉ እራሳቸዉን ተመረጥኩ ከማለት በላይ ትክክለኛዉን ዴሞክራሲ ገቢር አድርገዉ ሞክረዉትም አያዉቁም።

የያዴማን አባገነናዊ መንግስት ለመቃወም የተመሠረቱ የፖለቲካ ማሕበራት ካንድነታቸዉ ይልቅ-ብዙነታቸዉ በጋራ፣ ከመታገል-ይብስ እርስ በርስ መሻኮታቸዉ እንደደመቀ ነዉ።ያዴማ ባለፈዉ የካቲት ድንገት ሲሞቱ ባብዛኛዉ ከሳቸዉ ሌላ መሪ የማያቃዉ ሕዝባቸዉ የሚጓዝበት አቅጣጫ ግራቢጋባ፣ ሐገሪቱ የምትመራበት ሥርአት ቢወለካከፍ ብዙ የሚደንቅ አይደለም።

በቅጡ የተደረጃዉ፣ በሐገሪቱ ጦር የሚደገፈዉ ገዢ የፖለቲካ ማሕበር የሟቹ አምባገነን ልጅ ፎር ግናሲንግቤን በአባታቸዉን መንበር ያስቀመጠዉ-እርምጃዉ ሕይወት፣ ሐብት ንብረት ያጠፋዉም የሥልጣን ሽግግሩ ሕግ፣ ከሕገ-መንግስት ያለፈ የሚያስጠብቀዉ ተቋም፣ ገቢራዊነቱን የሚያስከብር ሐይል፣ እዉቀትም ከዚያች ትንሽ አፍሪቃዊት ሐገር ባለመኖሩ ነዉ።

ፎር-ግናሲንግቤ የወረሱትን ሥልጣን ከሰወስት ሳምንት በሕዋላ ለመልቀቅ የተገደዱት ተቃዋሚዎቻቸዉ ባደራጁት ሕዝብ ሠልፍ አልነበረም።በስፉ ሰበብ ሰዉ በመሞት-መቁሰሉም አልነበረም።የሕዝቡን የተቃዋሚ ፖለቲከኞችንም ጥያቄ ባፍታ ባዳፈኑት ነበር። የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግፊት፣ በተለይም የአፍሪቃ ሕብረት የማዕቀብ ዛቻንና፣ የአምዕራብ አፍሪቃ ማሕበረሰብን የማዕቀብ እርምጃ ሊቋቋሙት ባለመቻላቸዉ-እንጂ።

ግፊቱ የዉጪ ሥለነበረ ባለፈዉ እሁድ የተደረገዉ ምርጫ ነፃና ትክክለኛ መሆኑም ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።ምርጫዉ ከመደረጉ በፊት ሰባት ሰዉ ተገድሏል።ምርጫዉ ከተደረገ በህዋላ ትናንት ደግሞ ሰወስት ተገድሏል።ከአስር በላይ ቆስለዋል።በዉዝግብ፣ ግጭት ተጀምሮ በሰዉ ሕይወት ጥፋት ባሳረገዉ የምርጫ-ዉጤት አልታወቀዉ። ያሸንፋሉ ተብለዉ የሚጠበቁት ፎር ግናሲንግቤና ናይጄሪያ ዉስጥ በስደት የሚኖሩት የተቃዋሚዎቹ የፖለቲካ ማሕበራት ሕብረት መሪ ዢልክሪስት ኦሊፕዮና የምርጫዉ ዉጤት ምንም ሆነ ምን ተጣማሪ ብሄራዊ መንግስት ለመስረት መስማማታቸዉን አስታዉቀዋል።

ስምምነቱን የቀድሞ የቶጎ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይና አርኪ ብላዋለች።የአፍሪቃ ሕብረት ተደስቶበታል።የዩናይትድ ስቴትስ የቶጎ ሕዝብና ፖለቲከኞች የሐገሪቱ ሰላም እንዳይታወክ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ አደራ ብላለች።ዢልክርስት ኦሎፒዮና ፎር ግናሲንግቤ ቴሌዢን ካሜራ ሥምምነቱን በመተቃቀፍ ከፀደቁት ከጥቂት ሰአታት በሕዋላ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሥምምነቱ አለየለትም ማለታቸዉ አጓጊዉን ሁሉ ከንቱ እንዳያስቀረዉ ማስጋቱ አልቀረም።