የቶማስ ሳንካራ 30ኛ ሙት ዓመት | አፍሪቃ | DW | 14.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የቶማስ ሳንካራ 30ኛ ሙት ዓመት

የቀድሞው የቡርኪና ፋሶ ፕሬዚደንት ቶማስ ሳንካራ በጎርጎሪዮሳዊው ጥቅምት 15፣ 1987 ዓም  በአንጻራቸው በተካሄደ መፈንቅለ መንግሥት ተገደሉ። ይኸው ደም አፋሳሽ ድርጊት በኢምፔርያሊዝም አንፃር በነበራቸው አቋማቸው የአፍሪቃ ቼ ጉቬራ የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸውን ሳንካራ ሕይወት በአጭሩ ቀጭቶታል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:48
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:48 ደቂቃ

የቶማስ ሳንካራ 30ኛ ሙት አመት

ታህሳስ፣ 1949 ዓም በሰሜን አፐር ቮልታ የተወለዱት ሳንካራ ሀገራቸው  ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ተላቃ ነፃነቷን ስታገኝ የ12 ዓመት ልጅ ነበሩ። ወጣቱ የጦር  ሻምበል ቶማስ ሳንካራ በ1983 ዓም በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ከያዙ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አፐር ቮልታ የሚለውን የሀገራቸውን መጠሪያ ወደ ቡርኪና ፋሶ ወይም ሲተረጎም የቀና ሰዎች ሀገር ብለው በመቀየር፣ በሀገራቸው መንግሥታቸውን  ከቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ በግልጽ ያራቁ ተራማጅ ያሏቸውን ሶሻሊስት ፖሊሲዎችን አስተዋወቁ። የኪውባ ዓብዮት እና የቀድሞው የጋና ፕሬዚደንት ጄሪ ሮውሊንጊስ አድናቂ የነበሩት ሳንካራ   ከሙስና የጸዳች እና  ከጎረቤት አፍሪቃውያት ሀገራት ጋር አንድ የሆነች ቡርኪና ፋሶን ለማቋቋም  ነበር  ያለሙት።  
ሳንካራ የተከተሉትን ሶሻሊስታዊ አመራር በዕድሜ የገፉት ቡርኪናቤዎቹ  የቀድሞው ርዕሰ ብሔር ከሞቱ  አሁን ከ30 ዓመታት በኋላ በጥርጣሬ ቢመለከቱትም፣ በወጣቱ ዘንድ ትልቅ አድናቆት አትርፎላቸዋል። 30ኛ የሙት ዓመታቸውን  ምክንያት በማድረግም ለሳቸው ክብር  አንድ መታሰቢያ እንዲሰራ በመጠየቅ ሰሞኑን አደባባይ ወጥተዋል። 
ሳናካራ በስልጣን በቆዩባቸው አራት ዓመታት ፣ በተለይ ቅድሚያ የሰጡት አላግባብ የሚባክን የመንግሥት ወጪን ለመቀነሱ እና የጤናውን፣ የትምህርቱን እና ከቡርኪና ፋሶ ሕዝብ መካከል ብዙውን ከፊል የሚሸፍኑትን የገበሬዎችን ሁኔታ ለማሻሻሉ ተግባር ነበር። በራሳቸው አመራር ዘመን በየመንደሮቹ የጤና ጥበቃ ማዕከላት ተቋቁመዋል፣ በ1984 ዓም ለምሳሌ ተንቀሳቃሽ የጤና ቡድኖችም በሁለት ሳምንት ውስጥ ከሁለት ሚልዮን የሚበልጡ ሕፃናት መክተባቸው ይታወሳል።  በዚያው ዓመትም መሬትን ወደ መንግሥት እጅ ካስገቡ በኋላ የግብርናው ምርት ጨምሯል። በ1986 ዓም ም 35,000 ቡርኪናቤዎች ን በሶስት ወራት ውስጥ ማንበብና መጻፍ ተምረዋል።  ሳንካራ ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን  ለማገልገል ቆርጠው የተነሱ ተወዳጅ መሪ እንደነበሩ በሊቢያ የቀድሞው የቡርኪና ፋሶ አምባሳደር  ሙስቢላ ሳንካራ ያስታውሳሉ።


 « ቶማስ በድሆች ዘንድ ፣ ፍትሕ እና መደመጥን በሚፈልጉት ዘንድ ተቀባይነት ነበረው። ምንም እንኳን ድሀ ቢሆኑም፣ በቡርኪና ፋሶ ዜግነታቸው ኩራት የሚሰማቸው ሁሉ ቶማስን ይረዱት ነበር። ቶማስን ልዩ የሚያደርጋቸው ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው የነበራቸው ክብር እና ፍቅር ነው። »
ሳንካራ ፖሊሲዎቻቸውን በጠነከረ አመራር ገቢራዊ ማድረጋቸው፣ ለምሳሌ፣ ባንድ በኩል ሕዝቡን የሚቆጣጠሩ የዓብዮቱ ተከላካይ ኮሚቴዎችን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፍትሕ የሚሰጡ የዓብዮቱ ሕዝባዊ ችሎቶችን አቋቁመው እንደነበር ይነገራል። ፖሊሲዎቻቸውን በመቃወም የስራ መቆም አድማ ያደረጉ መምህራንን ከስራ አባረዋል፤ በአንፃራቸው የተንቀሳቀሱ የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሙያ ማህበራት አባላትን በቁጥጥር እንዲውሉ አድርገዋል።
ከቀድሞ የሊቢያ መሪ ሞአመር ኧል ጋዳፊ እና ከቀድሞው የጋና ፕሬዚደንት ጄሪ ሮውሊንግስ ጋር የቅርብ ግንኙነት በማድረጋቸው ከጎረቤት ኮት ዲ ቯር እና ቶጎ ጋር ጠንካራ ልዩነት ውስጥ የገቡት ሳንካራ ቡርኪና ፋሶን ብቻ ሳይሆን ሌሎች አፍሪቃውያት  ሀገራትን ጭምር ከምዕራቡ ዓለም ጥገኝነት የማላቀቅም ፍላጎት ነበራቸው ። አውሮጳውያን ቅኝ ገዢዎች በአህጉሩ የፈፀሙትን ብዝበዛ በማመልከት አፍሪቃውያት ሀገራት ከምዕራቡ የተበደሩትን የውጭ ዕዳ መክፈል እንዲያቆሙ ያሳሰቡበት ጥሪያቸው የቀድሞዎቹን ቅኝ ገዢዎች ሳያስደነግጥ አላለፈም።  አፍሪቃውያቱ ሀገራት ዕዳቸውን ለምዕራባውያኑ ባይከፍሉ ምዕራባውያኑ እንደማይሞቱ፣ አፍሪቃውያን ግን ይሞታሉ የሚል መከራከሪያ ነበር ያቀረቡት። 


ሳንካራ በታማኝነታቸው እና በተራ አኗኗራቸው ከብዙዎቹ አቻዎቻቸው የተለዩ አድርጓቸዋል። ፕሬዚደንቱ ሁለት ልጆቻቸውን የሰፊው ሕዝብ ልጆች ወደሚሄዱበት የመንግሥት ትምህርት ቤት ይልኩ እንደነበርና ቀዳማዊቷ እመቤትም በሀገሪቱ የመጓጓዣ ዘርፍ ውስጥ የነበራቸውን ስራ  መቀጠላቸው አይዘነጋም። ከርሳቸው በፊት በነበረው መንግሥት ይጠቀምባቸው የነበሩት የናጠጡት ተሽከርካሪዎችን ሸጠው ለራሳቸው አነስተኛ መኪና መጠቀማቸው እና ሚንስትሮቻቸውም የሳቸውን አርአያ እንዲከተሉ ማድረጋቸው ይታወሳል።  
የሳንካራ አመራር ግን ከአራት ዓመት አልበለጠም። ጥቅምት 15 ፣ 1987 ዓም ወደ አንድ ልዩ የካቢኔ ስብሰባ ሲሄዱ በአንጻራቸው መፈንቅለ መንግሥት ባካሄዱት እና በፕሬዚደንቱ ታማን ጠባቂዎች መak,ከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ወቅት ተገደሉ። ሳንካራ ከፈረንሳይ እና ከኮት ዲቯር ጋር መልካሙን ግንኙነት አለመፍጠራቸው ለመገደላቸው አንድ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረም ተንታኞች ይናገራሉ። 

ሳንካራ  ለቦሊቪያዊው ቼ ጉቬራ በተደረገ መታሰቢያ ስነ ስርዓት ላይ  ዓብዮተኞችን እና ግለሰቦችን መግደል ይቻላል፣ ሀሳብን ግን መግደል አይቻልም ሲሉ አንድ የኪውባ ዓብዮት ጦር መኮንን በመጥቀስ ከተናገሩ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር የተገደሉት። ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ የቡርኪና ፋሶን አመራር ለሶስት አሰርተ ዓመታት ያህል ፣ ከ1987 እስከ 2014 ዓም የያዙት ፈላጭ ቆራጩ ካምፓዎሬ በሳንካራ ፖሊሲዎች አማካኝነት የተመዘገቡ ውጤቶችን ማፍረስ ጀመሩ። ከሶስት ዓመት በፊትም ሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ በማድረግ የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ያደረጉት ሙከራ ባስነሳባቸው የሕዝብ ተቃውሞ ከስልጣን ተወግደው ወደ ጎረቤት ኮት ዲቯር ተሰደዋል።
 የሳንካራ አድናቂ ወጣቶች ሰሞኑን የሳንካራን ፎቶግራፍ  ይዘው አደባባይ በወጡበት ጊዜ የኒህኑ መሪ ራዕይ አስታውሰዋል።
«    ማመፁን ማሳየት ለማይችል ባርያ ለዚሁ ለደረሰበት መጥፎ እጣ ሌላ ሰው ሊያዝንለት አይገባም። በባርነት ቀንበር የሚገኘው ይኸው ግለሰብ በንቀት የሚያየውን እና እኔ ነፃ አወጣሀለሁ የሚለውን ባርያ አሳዳሪውን በተመለከተ ስህተት ከሰራ ለዚሁ ስህተቱ  ራሱ ተጠያቂ ነው። ትግል ብቻ ነው ነፃ ሊያወጣው የሚችለው። »
ከ2015 ወዲህ ሀገሪቱ በሮኽ ማርክ ካቦሬ በመመራት ላይ ስትሆን፣ ብዙዎቹ የሀገሪቱ ዜጎች በአዲሱ ፕሬዚደንት ዘመን እውን ይሆናል ብለው የጠበቁት ተሀድሶም ሆነ የቶማስ ሳንካራ አሟሟት እና የገዳዮቻቸው ማንነትም በግልጽ ይታወቃል የሚል ተስፋቸው ሳይሟላ ቀርቷል። 
ስለ ቶማስ ሳንካራ የህይወት ታሪክ እንደጻፉት ብሩኖ ጃፍሬ አባባል፣ ሳንካራ የተገደሉበትን መፈንቅለ መንግሥቱን የጠነሰሱት ምክትላቸው እና ወዳጃቸው የነበሩት ብሌይዝ ካምፓዎሬ ናቸው ተብለው ይጠረጠራሉ። 
« ሳንካራ የገደሉት ሰዎች የብሌይዝ ካምፓዎሬ የፀጥታ ኃላፊ  እና ኋላም ላይ በሀገሪቱ በሁለተኛ የስልጣን ደረጃ ላይ በነበሩት ዢልቤር ዲየንዴሬ እዝ ስር ነበሩ። ከግድያው ጋር በተያያዘ በተጨባጭ ያሉ መረጃዎች እንነዚህ ናቸው። የዕዙ አባላት ስምም በሚገባ ይታወቃል። »   
ብሌይዝ ካምፓዎሬ ለሳንካራ ግድያ በኃላፊነት እንደማይጠየቁ ቢያስታውቁም፣ በሌሉበት በቡርኪና ፋሶ ክስ ተመስርቶባቸዋል። 

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ


 

Audios and videos on the topic