1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጸጥታ ችግር ተፈናቅለው የነበሩ የቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች ወደ ግብርና ስራ ገብተዋል

ረቡዕ፣ ነሐሴ 8 2016

ከምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ሸሽተው የነበሩ እና ከስድስት ወር በፊት ወደ ጊምቢ የተመለሱ ነዋሪዎች የተወሰኑት ወደ ግብርና ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይም በመጀመሪያ ዙር ከአማራ ክልል በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም ወደ ጊምቢ የተመለሱ ነዋሪዎች ሰሊጥ እና በቆሎ አምርቷል፡፡

https://p.dw.com/p/4jS0f
የጊምቢ ወረዳ ተፈናቃዮች እቃ ይዘው ሲመለሱ
የጊምቢ ወረዳ ተፈናቃዮች ሲመለሱምስል Negassa Desalegn/DW

የቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች ወደ ግብርና ስራ ገብተዋል

የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት/ቡሳ ጎኖፋ በመጀመሪያ ዙር የተመለሱ አርሶ አደሮች ወደ እርሻ ስራ ተሰማርተው የተለያዮ ሰብሎችን መዝራታቸውን ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው መድሀኒት እጥረትን በተመለከተ ለወባ በሽታ መከላከል የተፈናቀሉ ዜጎች ያለቡት ቦታ በቂ በሆነ መልኩ መሰራጨቱን የጽ/በቱ ኃላፊ ነጻነት አለማየሁ ተናግረዋል፡፡ 
ከጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በ2014 ዓ.ም በሠላም እጦት ምክንያት ወደ አማራ ክልል ሸሽተው በተለያዩ ካምፖች የነበሩ ነዋሪዎች በሁለት ዙር ወደ ቀድሞ ቀአያቸው ከወራት በፊት ተመልሰዋል፡፡ በ2 ዙር ወደ ጊምቢ የተመለሱት ከ1ሺ በላይ ዜጎች  በተጠገኑ ቤቶችና በተዘጋጀው መጠለያዎች መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ በቅርቡም በአካባቢው የተመለሱ ዜጎች ወደ ግብርና ስራ በመግባት እንደ ሰሊጥና ማሽላ ያሉ ሰብሎችን መዝራታቸውን ያነጋርናቸው ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ 

የወባ በሽታ ስርጭት በጊምቢ ወረዳ

አርሶ አደሮቹ በአካባቢው በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ሁኔታም የተሻሻለ መሆኑን በመግለጽ አብዛኛው በመጀመሪያ ዙር ወደ ቤታቸው የተመለሱ አርሶ አደሮች ወደ ግብርና ስራ መግባታቸውን ሌሎች ያነጋርናቸው የቶሌ ቀበሌ ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ በቀበሌው የህክምና ተቋም ባለመኖሩ ለተሸለ ለህክምና ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውና አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም የወባ በሽታ ከአራት ዓመት ወዲህ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ የመድሀኒት እጥረትም እልባት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡

«የወባ በሽታ መድሀኒት ለሁሉም ወረዳዎች ተሰራጭቷል»

የምዕራብ ወለጋ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት/ቡሳ ጎኖፋ በበኩሉ በሁለት ዙር 1700 ሰዎች ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን በመግለጽ በመጀመሪያ ዙር የተመለሱ  ወደ ግብርና ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡ የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ/አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት ኃላፊ ነጻነት አለማየሁ ወደ ቶሌ ለተመሰሉ ሰዎች የሰብአዊ ድጋፍ ወቅቱን ጠብቆ እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ መድኃኒት እጥረት ተብሎ ለቀረበው ቅሬታም የወባ በሽታ መድሀኒት እጥረት አለመኖሩን ጠቁመው በዞኑ በዘመቻ መልክ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ሌሎች የህክምና መድሀኒቶችና ቁሳቁሶ እጥረት ሊኖር ይችላል ብለዋል፡፡ 
"በመጀመሪያ ዙር የመጡት ወደ ግብርና ስራ ገብተዋል፡፡ ያሉበት ሁኔታም የተሻለ ነው፡፡ ሁለተኛ ዙር የተመለሱት ደግሞ እርሻ ከተጀመረ በኃላ ስለመጡ ስራ አልጀመሩም፡፡ በሚቀጥለው ወደ ስራ ይገባሉ፡፡ ድጋፍን በተመለከተ ቦታው ላይ የድጋፍ ችግር የለም፡፡  መድኃኒትን በተመለከተ ወባ በሽታ በስፋት አለ ለዚህ ደግሞ በዞናችን ዘመቻ ተደርጎ ሁሉንም ወረዳዎች መድሀኒት ተዳርሷል፡፡"

በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳን ጨምሮ ከ15 በላይ ወረዳዎች ውስጥ ወባ በሽታ ስርጭት በስፋት መኖሩን የዞኑ ጤና ጽ.ቤት ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ በቶሌ ቀበሌ ከዚህ ቀደም 247 የሚደርሱ ሰዎች በወባ ተይዘው እንደነበር በመግለጽ በአሁኑ በወቅት በአካባቢው በሰዎች ላይ የሚደረሰው ጉዳት መቀነሱንም ጽ/ቤቱ ጠቁመዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

ልደት አበበ
ኂሩት መለሰ