የትግራይ ጦርነት፤ የባይደን ማዕቀብ ዝግጅትና አንድምታዉ | ዓለም | DW | 21.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የትግራይ ጦርነት፤ የባይደን ማዕቀብ ዝግጅትና አንድምታዉ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሰሜናዊ ኢትዮጵያ እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶችና ጦርነቶች «ልዩ ልዩ ጥሰቶች» ፈጽመዋል የተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ ገንዘብ ዝውውርና ወደ ሀገር በሚገቡ የመከላከያና ወታደራዊ ንግዶች ላይ ቁጥጥርና ገደብን የሚጥል አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ መፈረማቸው ይፋ ሆኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:49

ማዕቀቡ እንዴት ይታያል?

ጥቅምት 14,2013 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ ትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ሕወሃት ድንገተኛ ጥቃት መፈፀሙን መንግሥት ከገለፀ በኋላ የተቀሰቀሰው የትግራዩ ጦርነት በሶስት ሳምንታት ጊዜያት ውስጥ መጠናቀቁ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ይፋ ቢሆንም፤ ሁለቱም ተፋላሚ ኃይላት የአሸናፊነትና የአጥቂነት ድልን በየተራ እየጎሰሙ እነሆ ግጭቱ አድማሱን አስፍቶ ያለምንም መቋጫ ድፍን አንድ ዓመት ሊሞላው የአንድ ወር እድሜ ብቻ ቀርቶታል:: በዚሁ ለወራት በዘለቀው አስከፊ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሲቭል እና ተዋጊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል:: አያሌ የግለሰቦች፣ የድርጅቶችና የመንግሥት ተቋማት ንብረቶች እንዲሁም መሰረተ ልማቶች ወድመዋል:: በ 100 ሺህዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎችም ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲሰደዱና እንዲፈናቀሉ ተገደዋል:: የዓለማቀፍ ረድኤት ድርጅቶችን እጅ የሚጠባበቀው የሃገሪቱ ሕዝብ ቁጥርም በየዕለቱ በእጅጉ እያሻቀበ ነው:: የኢትዮጵያ መንግሥት "የስምንት ወራት የሰላም ማስከበር ዘመቻ ተልዕኮዬን አጠናቅቄያለሁ፤ የትግራይ ክልል ከእንግዲህ የግጭት የስበት ማዕከል ሊሆን ከማይችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል፤ ጊዜውም የእርሻ ወቅት በመሆኑና የእርዳታ ሥራዎችን በተሳለጠ ሁኔታ እንዲከናወን ለማስቻል የተናጥል የሰብዓዊ እርዳታ ተኩስ አቁም አውጃለሁ" በማለት ሰራዊቱ ከትግራይ ክልል እንዲወጣ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቋል:: ሆኖም ክልሉን ከጊዜያዊው አስተዳደር የተረከበው የትግራይ ኃይላት በጦርነቱ ምክንያት ተይዘውብኛል ያላቸው ግዛቶች እንዲለቀቁ፣ የኤርትራ ሰራዊት ትግራይን ለቆ እንዲወጣ፣የፖለቲካ እስረኞችን ያካተተ በድርድር ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲካሄድ፣ ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታን በተገቢው ሁኔታ ለማዳረስ የሚረዳ መተላለፊያ ኮሪዶር እንዲከፈትና ሌሎችንም ቅድመ ሁኔታዎች በማስቀመጥ ግጭቱን ወደ አማራ እና አፋር ክልልሎች አስፍቶታል:: በዚህም በቀጠለው ጦርነት በርካታ ሕይወት ሲጠፋ ግማሽ ሚልዮን የሚጠጉ ሰላማዊ ዜጎችም መፈናቀላቸው እየተነገረ ነው:: 


ሰብዓዊ ቀውሱን ለማስቆም፣ ግጭቱ እንዲያበቃና የሰላም ወይይት በአፋጣኝ እንዲጀመር በተደጋጋሚ ስትወተውት የቆየችው ዩናይትድስቴትስ ከአሁን ቀደም በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ፣ በአማራ ክልል እና በሕወሃት አመሪሮች ላይ የጉዞ ዕቀባ ማድረጓ ቢታወቅም፤ እርምጃው የታሰበውን መፍትሄና ውጤት አለማምጣቱን በመግለጽ ባለፈው አርብ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሰሜናዊ ኢትዮጵያ እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶችና ጦርነቶች "ልዩ ልዩ ጥሰቶች ፈጽመዋል የተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ በተለይም በገንዘብ ዝውውርና ወደ ሀገር በሚገቡ የመከላከያና ወታደራዊ ንግዶች ላይ ቁጥጥርና ገደብን የሚጥል አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ መፈረማቸው ይፋ ሆኗል:: ዕቀባው ግጭቱ እንዲራዘም አስተዋጽዖ ያደረጉ፣ ሰብአዊ አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ ተደራሽ እንዳይሆን ያስተጓጎሉ፣ ተኩስ አቁም እንዳይደረግ በቀጥታ የተከላከሉና ተባባሪዎቻቸው ሁሉ ተቋማትና ፓርቲዎች ላይ ጭምር ትኩረት ያደረገ መሆኑም ተገልጿል::ለመሆኑ የዩናይትድስቴትስ ህግ ፕሬዝዳንቱ ያለ ኮንግረስ ውይይትና ውሳኔ እስከምን ድረስ ነው በውጭ ሀገራት ጉዳይ ጣልቃ ገብ ውሳኔና ማዕቀብ የመጣል ስልጣን የሚሰጠው? በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ የተጣለው አዲሱ ተጨማሪ ዕቀባ በሀገራቱ፣ በአፍሪቃ ቀንድም ሆነ በወዳጅ ሀገሮቻቸው ልዩ ልዩ ትብብር እና ግንኙነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምን ይመስላል? 
የአሜሪካን የማዕቀብ ውሳኔ የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረውና ራሱን የትግራይ ኃይሎች የሚለው ቡድን በደስታ መቀበሉን ሲገልጽ ኢትዮጵያም ሆነች ኤርትራ "የሀገርን ሉዓላዊነት የሚጎዳ ተግባር በማዕቀብ ለድርድር አይቀርብም" የሚል አንድምታ ያለው ምላሽ ሰጥተዋል:: የዋሽንግተን መንግሥት በበኩሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በኩል ማዕቀቡ ገቢራዊ ከመሆኑ አስቀድሞ ለተወሰኑ ቀናት እንዲያጤኑት ቢያስገነዝብም ሰሞኑን ይኸው የአሜሪካ የማዕቀብ መመሪያ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ለውይይት እንደሚቀርብ ነው ያስታወቀው:: ጉዳዩ በምክር ቤቱ አሜሪካ የፈለገችውን ውሳኔ ባያመጣ እንኳ ሌሎች ሸሪኮቿም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ መጎትጎቷ አይቀርም ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግምታቸውን ከወዲሁ እየገለጹ ይገኛሉ:: ይህ ከሆነ ኢትዮጵያም ሆነች ኤርትራ አቋማቸውን የሚቀይሩበት ሁኔታ ይፈጠራል ወይስ "ህልውናና ሰላም ማስከበር" ባሉት ዘመቻ ይገፉበታል? ከዚህ ሌላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባይደን የትግራዩን ጦርነት ተከትሎ የንፁሃን ዜጎች ግድያ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሰብዓዊ እርዳታ መስተጓጎል በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ቢገልፁም በተለይም ግጭቱ እየተስፋፋ ቀጠናዊ ይዘት እየያዘ መሄዱና በአሜሪካ የውጭ ፖሊስ ላይ ታላቅ ስጋት መደቀኑንም አልሸሸጉም:: ዶይቼ ቨለ "DW" በማዕቀቡ አጠቃላይ ይዘት፣ ፍትሃዊነትና አንድምታው ዙሪያ አስተያየቶቻቸውን እንዲያጋሩት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን አነጋግሯል:: ባለፉት 23 ዓመታት በሰሜን አሜሪካ የግለሰቦች የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት /ሲቭል ሊበርቲ ዩንየን/ ምክትል ፕሬዝዳንትና በማሳቹሴትስ የወንጀል ተከላካይ ጠበቆች ማህበር ፕሬዝዳንት በመሆን ያገለገሉት አንጋፋው የህግ ባለሙያ ደረጄ ደምሴ ቡልቶ በአሜሪካ ህግ ኮንግረሱ ፕሬዝዳንቱ ከሀገሪቱ ጥቅም ጋር በተገናኘ በተናጥል ከፍተኛ ሳይሆን መለስተኛ የገንዘብ ዝውውርና ኢኮኖሚ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ በግለሰቦችና ተቋማት ላይ የማግኒትስኪ ማዕቀብን ጨምሮ የመጣል ስልጣን እንደሰጠው ለዶይቼ ቨለ አብራርተዋል:: ብዙዎች አሁን የተጣለው አዲሱ ማዕቀብ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ከባድ ጉዳት የሚያስከትል ቢመስላቸውም በዝርዝር መመሪያው ውስጥ ጦርነቱን ያስፋፋ ፣ የዕርዳታ አቅርቦቱን ያስተጓገሎ ፣ የእርዳታና የዓለማቀፍ ተቋማት ሰራተኞች ላይ ጥቃት ያደረሰ፣ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያና ማፈናቀል እንዲሁም ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀመ ፣ ተቋማትንና ንብረቶችን ያወደመ የሚሉት በግለሰብና በተቋማት ላይ የቀረቡ የዕቀባና ነጥቦች ሕወሃትም ተጠያቂ እንደሚያደርጉት ነው ያስረዱት:: ከዚህ ሌላ የሃገርን የግዛት ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የጣለ የሚለው የተጠያቂነት ዝርዝር ሃሳብ ከሱዳን እና ግብጽ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያጠኑ የሚያደርግ ሲሆን በፋይናንስ ረገድም ለጦርነቱ እገዛ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ላይ ዕቀባ መደረጉ ከመንግሥት ይልቅ በውጭ የሚገኙ አባላቱ ድጋፍ ለሚንቀሳቀሰውና የተለያዩ ንብረቶችን በዲያስፖራ ደጋፊዎቹ አማካኝነት ላፈራው ሕወሃት እንቅስቃሴውን የሚገታ ነው ሲሉ የህግ ባለሙያው ጨምረው ተናግረዋል:: 


የአሁኑ የአሜሪካ ማዕቀብ ወይም መመሪያ ከበፊቱ የሚለየው ህግ መሆኑና በፕሬዝዳንት ባይደን የተፈረመ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ግጭቱ እየተስፋፋ ቀጠናዊ ይዘት እየያዘ መምጣቱና ይህም ለአሜሪካ የውጭ ፖሊስ ብሄራዊ ስጋት መደቀኑ በጉልህ መገለፁ ነው የሚሉት የህግ ባለሙያውና በኤር ላንገን ኑረንበርግ ዩኒቨርሲቲ በዶክትሬት መርሃግብር ትምህርታቸውን የሚከታተሉት አቶ ዮናስ መብራቱ በበኩላቸው "የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካን ማዕቀብ ከሰባዊ ዕርዳታ በላይ መሆኑን በመግለጽ አድሎአዊና ሚዛናዊ ያልሆነ ሲል" ጠንከር ባለ ቃል መቃወሙን በማውሳት ለሰላም ድርድሩ እንደማይገዛ የሚገልፅ የሚመስል መግለጫ ማስተላለፉን ነው ያስረዱት:: ድርድርን መሰረት ያደረገ ውይይት እና የተኩስ አቁም ከፍተኛ መዋዥቅ ለገጠመው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ለሕዝቡ ኑሮና ሰብዓዊ አገልግሎቱን በትግራይም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በተገቢው ሁኔታ እንዲዳረስ የሚጠቅም በመሆኑ የአሜሪካ ውሳኔ እጅግ ወቅታዊና ለሁሉም ወገኖች ጠቃሚ ነው ሲሉ ተናግረዋል::ተኩስ አቁሙአለማድረግ የሰላማዊ ዜጎች ሰቆቃ እንዲቀጥል ፣ ስደት፣ እንግልትና መፈናቀል ግድያና ሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲባባስ የማደርግ ሀገሪቱንም ክፉኛ የሚጎዳ ነው ሲሉም ባለሙያው ጨምረው አብራርተዋል:: ሁሉም ወገኖች በድርድር ላይ ለተመሰረት ውይይትና ለተኩስ አቁም ስምምነት ተገዢ ሊሆኑ ይገባል ያሉት አቶ ዮናስ ስለ ሉዓላዊነት እየተናገሩ የኤርትራን ጦር ማዝመት ውሃ አይቋጥርም ሲሉ በመንግሥት ላይ ያላቸውን ቅሬታ አልሸሸጉም::በሌላ በኩል በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ፕሮግራም የፋኩልቲ ዳይሬክተርና የኒውዮርኩ ግዙፉ መድኃኒት አምራች ኩባንያ ካምፓኒ ፋይዘር የስታትስቲክስ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ደምሴ ዓለማየሁ "ቀደም ሲል በትጥቅ ዘመን በአሜሪካ መንግሥት አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ፓርላማ አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው ሕወሃት ጋር የባይደን አስተዳደር ለድርድር ተቀመጡ ብሎ እስከ ማዕቀብ መድረሱ ፍፁም አድሏዊና የሀገሪቱንም ሉአላዊነት የሚዳፈር እርምጃ ነው" በማለት ዕቀባውን ክፉኛ ነቅፈዋል:: መንግስት በሕወሃት ላይ ሲያካሂድ የቆየውን ሰላም የማስከበር ዘመቻ በጦር ስትራቴጂ ለውጥ ሰበብ ከትግራይ ወደ አማራና አፋር ክልል እንዲሻገር ማድረጉ ሕወሃት ሕጻናት ወታደሮችን ጭምር መልምሎ በማሰለፍ አያሌ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመትን በክልሎቹ እያደረሰ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ደምሴ እርምጃው መንግስት ጥቂት የማይባል ደጋፊዎቹን እንዳሳጣው ነው የገለጹት:: እነ አሜሪካ ከሕወሃት ጋር ድርድር ይደረግ የሚሉት የ 27 ዓመታቱን የሕዝባችንን ሰቆቃ ለማርዘም በመሆኑና ድርድር የሚለው ሃሳብ ትጥቅ ያነገቡ እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉ ታጣቂ ኃይላት የጀመሩትን በአማራ እና ኦርቶዶክስ በሌሎችም ሕዝቦች ላይ የሚያካሂዱትን ፍጅት እንዲያጠናክሩ በር ስለሚከፍት መንግግስት የዜጎቹን ደህንነት ለማስጠበቅ ሰላም በማስከበሩን ዘመቻ እንዲገፋበት ጠይቀዋል:: 
ከሶስት ወራት በፊትም ግንቦት 15, 2013 ዓ.ም ዩናይትድስቴትስ ከትግራይ ግጭት ጋር በተያያዘ እየተፈፀሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችቸና ጥቃቶች እየተባባሱ መሄዳቸውን በማውሳት በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለስልጣናት፣ በወታደራዊ እና ደኅንነት ኃላፊዎች በተጨማሪም በአማራ ክልል መደበኛና ኢ-መደበኛ የፀጥታ አባላትና ተባባሪ ግለሰቦች እንዲሁም የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የጉዞ ወይም የቪዛ ዕቀባ መጣሏ የሚታወስ ነው:: ባለፈው ወርም የአሜሪካ ጠቅላይ ግምጃ ቤት የኤርትራ ጦር በትግራይ ከፍተኛ የመብት ጥሰት አስገድዶ መድፈርና የንፁሃን ዜጎች ግድያ ፈጽሟል በማለት በኤርትራው ጦር ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ፊሊጶስ ወልደዮሃንስ ላይ ማግኔቲስኪ የተሰኘውን በአሜሪካ ውስጥ ባላቸው ልዩ ልዩ ንብረትና ገንዘብ በተጨማሪምሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ላይ ማዕቀብ መጣሏ አይዘነጋም:: ዕቀባው ዲፌንስ ትሬድ ኮንትሮል ፖሊሲ የተሰኘውን በሕዝብ ላይ ጥቃት የሚፈፀምባቸውን የቴክኖሎጂ ፣ ኮምፒውተሮችና ሶፍትዌሮችንም ግብአቶች ቁጥጥር የሚጨምር ነው:: አዲሱ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ማዕቀብ ሰሞኑን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ውይይት ይደረግበታል ተብሏል።


እንዳልካቸው ፈቃደ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic