1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከኤርትራ ጋር ሰላም ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገለፀ

ሰኞ፣ መስከረም 20 2017

ኤርትራን ጨምሮ ከሌሎች ሁሉም አጎራባች ህዝቦች ጋር ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር እንደሚሰሩ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ። በሌላ በኩል ከህወሓት ጉባኤ ራሳቸው ያገሉ የፓርቲው አመራሮች ዛሬ በመቐለ "ህወሓት ማዳን" የተሰኘ መድረክ አካሂደዋል።

https://p.dw.com/p/4lEbY
Getachew Reda
ምስል Million Haileselassie/DW

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኤርትራን ጨምሮ ከሁሉም ጋር ሰላም ለመፍጠር እየሰራ ነው ተባለ

ኤርትራን ጨምሮ ከሌሎች ሁሉም አጎራባች ህዝቦች ጋር ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር እንደሚሰሩ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ። አቶ ጌታቸው ከኤርትራ መሪዎች ጋር ግንኙነት እንደሚያደርጉ፥ ከዶክተር ደብረፅዮን ለቀረበ መረጃ ምላሽ ሰጥተዋል። በሌላ በኩል ከህወሓት ጉባኤ ራሳቸው ያገሉ የፓርቲው አመራሮች ዛሬ በመቐለ "ህወሓት ማዳን" የተሰኘ መድረክ አካሂደዋል። 

በሁለት ጎራ ተከፍለው ያሉትየህወሓት አመራሮች፥የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በተለያዩ ቦታ ነዋሪዎች በመሰብሰብ አንዳቸው ሌላኛው ሲወቅሱ ነበር ያሳለፉት። እንደ ይፋዊ የህወሓት ገፅ መረጃ ጉባኤ ያደረገው ህወሓት ከፍተኛ አመራሮች፥ በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በምትገኘው እና ከኤርትራ ጋር በምትዋሰነው ኢሮብ ወረዳ 'ህዝባዊ' የተባለ የውይይት መድረክ ያካሄዱ ሲሆን፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ የመሩት በተመሳሳይ 'ህዝባዊ' የተባለ መድረክ ደግሞ ትላንት እሁድ በመቐለ ከተመረጡ የትግራይ ደቡብ ምስራቅ ዞን ነዋሪዎች ጋር ተካሂዷል።

በትላንቱ የመቐለው 'ስብሰባ እና ድጋፍ የመግለፅ የመድረክ' ለመሳተፍ በሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ለመቐለ ቅርብ ርቀት ካሉ ወረዳዎች መጥቶ የነበረ ሲሆን በዚሁ ሁነት፥ በእነ ዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን በተለያዩ አንጃዎች ሲወቀስ ተስተውሏል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኤርትራን ጨምሮ ከሁሉም ጋር ሰላም ለመፍጠር  እየሰራ ነው
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኤርትራን ጨምሮ ከሁሉም ጋር ሰላም ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አቶ ጌታቸው ገልፀዋልምስል Million Haileslasse/DW

በዚሁ መድረክ የተናገሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ፥ ከኤርትራ ጨምሮ ከሌሎች ሁሉም አጎራባች ህዝቦች ጋር ሰላም ለማስፈን መስራታቸው እንደሚቀጥሉ የገለፁ ሲሆን ዶክተር ደብረፅዮን ከሚመሩት የህወሓት ቡድን ከዚህ በፊት ተሰራጭቶ ለነበረ መረጃ ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ "ሚስጥር መሆኑ ነው፥ ከኤርትራ ጋር ይገናኝ የነበረው እሱ ነው ብለው በቅርቡ ሲያጋልጡ ነበር።ከኤርትራ ጋር የተለየ ግንኑነት የለኝ፥ የምልከው ወርቅ የለኝም። የትግራይ ህዝብ ሰላም የሚሆንበት ዕድል ካለ ለማየት ነው የተገናኘነው። አሁንም አላቆምም፥ የትግራይ ህዝብን የሚጠቅም ነገር ካለው ይቀጥላል። ይሁንና ግን ፀረ የሆነ ሐይል ግንኙነት አልመሰርትም። ከኤርትራ ጋር ሆኞ እገሌ ለመምታት፣ ከፌደራል ጋር ሆኞ እገሌ መምታት ወደሚል ጨዋታ አልገባም። የትግራይ ህዝብን ወደሌላ የጦርነት መድረክ ወደሚያስገባ ነገር ለምን እገባለሁ" ብለዋል።

በቅርቡ የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሰጡት መግለጫ፥ ህወሓት ከውጭ ሐይል ጋር ግንኙነት እንዳለው አስመስሎ በአቶ ጌታቸው ረዳ መገለፁ በማንሳት በሰጡት አስተያየት ግንኙነቱ የተደረገው በራሳቸው በአቶ ጌታቸው ረዳ መሆኑ ጠቁመው ነበር።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤልምስል Million Hailesilassie/DW

የህወሓት አመራሮች ልዩነት በሰፋበት በዚህ ግዜ፥ ዛሬ ደግሞ ከህወሓቱ ጉባኤ ራሳቸው ያገለሉእና በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩ የፓርቲው አመራሮች "ህወሓት ማዳን" የተሰኘ መድረክ በመቐለ ያካሄዱ ሲሆን፥ ጉባኤ ያደረገው ሐይል በክልሉ አደጋ የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች እያካሄደ እንዳለም ገልፀዋል። በዚሁ "ህወሓት ማዳን" የተሰኘ መድረክ የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ሰፊ እና መሰረታዊ መሆኑ ጠቁመዋል። አቶ ጌታቸው "ልዩነታችን እልህ ሳይሆን፥ መሰረታዊ ነው። የአካሄድ፣ የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት ልዩነት መሆኑ ሁሉ አባላችን ሊረዳ፥ ከላይ እስከታች የተፈጠረ መደናገር ግልፅ ለማድረግ እንዲያግዘን ትኩረት አድርገን እንመክራለን" ብለዋል።

በቅርቡ ጉባኤ አድርጎ የነበረው ህወሓት፥ መስከረም 6 ቀን 2017 ዓመተምህረት ባወጣው መግለጫ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 ከፍተኛ አመራሮች ከፓርቲው ማገዱ አስታውቆ እንደነበረ ይታወሳል።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ 

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

አዜብ ታደሰ

ፀሐይ ጫኔ