የትግራይ ክልል ባለሃብቶች በባንኮች ላይ ያቀረቡት አቤቱታ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 6 2017ባንኮች የጦርነቱ ወቅት ወለድ እንድንከፍል እያስገደዱን ነው በማለት በትግራይ የሚገኙ ነጋዴዎች እና ባለሀብቶች ቅሬታ አቀረቡ። በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ለረዥም ግዜ ባንክ ተዘግቶ የነበረ ቢሆንም፥ ከተከፈተ በኃላ ባንኮች በትግራይ ሰጥተዉት ለነበረ ብድር፥ ተበዳሪዎች ከእነ ወለዱ እንዲመልሱ እያስገደዱ ነው በማለት የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማሕበራት ገልጿል።
በአጠቃላይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግርች ተቀዛቅዞ በቆየ እንቅስቃሴ ምክንያት ተቸግረው እንዳሉ የሚያነሱት በትግራይ የሚገኙ ነጋዴዎች እና ሌሎች በአገልግሎት ሰጪነት የተሰማሩ ባለሀብቶች፥ በዚህ ላይ ባንኮች የጦርነቱ ወቅት የብድር ወለድ እንድንከፍል እያስገደደን ነው በማለት ቅሬታቸው በማቅረብ ቀጥለዋል። በትግራይ የሚገኙ ከባንኮች ብድር የወሰዱ ባለሃብቶች እንደሚያነሱት፥ በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ሁሉም የመንግስት እና ግል ባንኮች ተዘግተው በቆዩበት፣ ገንዘብ ማንቀሳቀስ በማይቻልበት፣ ከፍተኛ ውድመት በደረሰበት ሁኔታ፥ የፋይናንስ ተቋማት የጦርነቱ ወቅት ወለድ ጭምር እንድንከፍል ማስገደዳቸው ሐላፊነት የጎደለው እና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚያስከትል ብለውታል።
ይህ ችግራቸው በተደራጀ መንገድ ማቅረብ መጀመራቸው የሚያነሱት እነዚሁ ነጋዴዎች፥ በጋራ የመከሩበት መድረክም ትላንት በመቐለ አካሂደዋል። በዚሁ የትግራይ የንግድና ዘርፍ ማሕበራት ምክርቤት ያዘጋጀው መድረክ የተናገሩት ባለሃብት አቶ ዘርኡ ገብረሊባኖስ፥ ባንኮች ብድን ከነወለድ መልሱ ሊሉ ሳይሆን በሕገወጥ መንገድ ዘግተውት ለነበረ የህዝብ ሀብት ካሳ ላከፍሉ ነው የሚጠበቀው ብለዋል።
ባለሃብቱ "ህዝብ ባንኮቹ አምኖ ገንዘቡ ብያስቀምጥም፥ በመንግስት ታዘው ተዘግተው ህዝቡ ያስቀመጠ የራሱ ገንዘብ ተነፍጎ ነው የቆየው። በዚህም ህዝቡ ለብዙ ችግር ተጋለጠ። ይህ ባንኮቹ የሚያስጠይቃቸው ጭምር ነው። ይህ ሁሉ በደል ሳያንስ አሁን ደግሞ የወለድ ወለድ ክፈሉ የሚሉበት አግባብ አለ ወይ ?" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማሕበራት የትግራይ ነጋዴዎች እና ባለሃብቶች ጥያቄ ይዞ ለክልሉ አስተዳደር እና ለፌደራል መንግስቱ አቤት ሲል መቆየቱ የሚገልፅ ሲሆን፥ ለደረሰው ውድመት እና የተፈጠረው ኪሳራ የሚመጥን መፍትሔ አለመገኘቱ ያነሳል። የነጋዴዎቹ ማሕበር አመራር የሆኑት ዲበኩሉ አለም ብርሃነ "ከጥቅምት ወር 2013 ዓመተምህረት ጀምሮ በመንግስት አስቸኳይ አዋጅ በራቸው ዘግተው የቆዩ የፋይናንስ ተቋማት፥ ነጋዴው ብድሩ በግዜው ሊከፍል ቢፈልግ እንኳን መቀበል በማይችሉበት ሁኔታ እያሉ፣ የትግራይ ነጋዴ ገንዘብ እያለው ጭምር በረሃብና በሽታ እየተሰቃየ እንደነበረ እየታወቀ፥ የደንበኞቻቸው ጠበቃ ሊሆኑ ሲገባቸው ብድር ከነወለዱ ክፈሉ እያሉ መንቀሳሰቀሳቸው ፍትሓዊ አይደለም። ባንኮቹ ከረዥም ግዜ ደንበኛቸው ጎን እንዲቆሙ እና ማሕበራዊ ሐላፊነታቸው እንዲወጡ እንጠይቃለን" ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና የህወሓት ድርድር ተግዳሮቶች
ይህ በባለሃብቶች እና በፋይናንስ ተቋማት መካከል ባለልዩነት ዙርያ የጠየቅናቸው የሕግ ምሁሩ አቶ ዓወት ልጃለም በበኩላቸው፥ በአበዳሪው እና ተበዳሪ ካለ ውል በዘለለ፥ ሁኔታው ግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልገው ያነሳሉ።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የባለሃብቶቹ ችግር እንደሚገነዘብ እና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጠው እየሰራ መሆኑ ይገልፃል። እነዚህ ለኪሳራ ተዳረግን ያሉ በትግራይ የሚገኙ ባለሃብቶች፥ ፍትሓዊ የሚሉት ምላሽ እስኪያገኙ በተለያየ መንገድ ጫና መፍጠራቸው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ
ሸዋዬ ለገሰ