የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር መግለጫ  | ኢትዮጵያ | DW | 02.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር መግለጫ 

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እንዲሁም በቅርቡ በተለያዩ ግጭቶች ሕይወታቸውን ላጡ ወገኞች ሐዘናቸውን በመግለፅ መግለጫቸውን የጀመሩት የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖምያዊ ጉዳዮችን ዳሰዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:26

የዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል መግለጫ

በወቅታዊ ጉዳዮች የትግራይ ክልላዊ መንግስት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተጀመረውን የሰላም መንፈስ እንደሚደግፍ፣ ሁሉም የተዘጉ በሮች እንዲከፈቱ ፍላጎት እንዳለው የተናገሩት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፤ ከሰላም ስምምነቱ ጋር ተያይዞ «በህወሓት በኩሉ ተቃውሞ አለ ተብሎ የሚወራው ውሸት ነው» ብለዋል። የክልሉ መንግስት ከጦርነቱና ከሰላም በኋላ ያልተቋጩ በእንጥልጥል የቀሩት የወሰን፣ አልጀርስ ውል፣ የካሳ ጉዳዮች ተቋማዊ በሆነ መንገድ እንዲዘጉ እንደሚሻ አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ትኩረት የሰጡት ጉዳይ ስለክልሉ ሰላምና የህዝቦች ደህንነት ይመለከታል። ካለፈው ዓመት የቀጠለ ትግራይ ላይ ያነጣጠረ ውንጀላና ትንኮሳ አሁንም ቀጥሏል ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን በውስጥ አቅም ሰላም በማረጋገጥ ከሌላው የተሻለ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል ብለዋል። የትግራይ ሰላምና የህዝቡ ደህንነት ላይ አደጋ ለመፍጠር ከቆየው የውጭ እንቅስቃሴ በተጨማሪ «የውስጥ ተላላኪ» ያልዋቸው አካላትን ተጠቅሞ የሚሠራ አካል መኖሩንም በመጠቆም ህዝቡን በአውራጃ ከፋፍሎ አንድነቱን ለመሸርሸር ከፍተኛ እንቅስቃሴ አለ ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ ችግሮች ትክክለኛ መነሻ ተረድቶ መፍትኄ ከመስጠት ይልቅ ውንጀላዎች ወደ ህወሓት ብሎም ትግራይ ማዞር «ተገቢነት የሌለውና የማያዛልቅ» ብለውታል። በፖለቲካ ችግሮች ምክንያት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተፈናቅለው ወደ ትግራይ የመጡ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር ከአንድ መቶ ሺህ በላይ መድረሱን የገለፁት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፣ ተፈናቃዮቹን መልሶ ለማቋቋም ከኦሮሚያ መንግስት አመራሮች ጋር በቅርበት እየተሠራ ቢሆንም ከአማራ ክልል ጋር ግን እስካሁን የተጀመረ ነገር እንደሌለና ተስፋ የሚሰጥ ሁኔታ እንደማይታይም ጨምረው ገልፀዋል። 

ሌላው ዶክተር ደብረፅዮን ያነሱት ጉዳይ የፌደራል መንግስት በትግራይ ከሚያከናውናቸው የልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ጋር የተያያዘ ነው። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በትግራይ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እየቀጠሉ መሆኑ የተናገሩት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በአንዳንድ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች አለ ባሉት የተሳሳተ አመለካከት ግን ሌላ አዲስ የልማት ፕሮጀክት በትግራይ ይጀመራል የሚል ተስፋ እንደሌለ ገልፀዋል። «ትግራይ የተለየ ተጠቅማለች የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ። ይህ በፌደሬሽን ምክርቤትም ቀርቧል» ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን እነዚህ አመለካከቶች ቀጣይ ፈተናዎች መሆናቸው ተናግረዋል፡።

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች