የትግራይ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የፀጥታ ጉዳይ
ረቡዕ፣ ኅዳር 11 2017በትግራይ እና ዓፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች ለመፍታት፣ ከአካባቢዎቹ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀዬአቸው ለመመለስ እና ሁለቱ ክልሎች እንዲሁም የተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል የሚያገናኙ ተዘግተው የነበሩ መንገዶች ለማስከፈት ያለመ የተባለ ግንኙነት በትግራይ እና ዓፋር ክልል አመራሮች ሲካሄድ የቆየ ሲሆን የዚህ ተቀጥያ የተባለ መድረክ ደግሞ የአፋር ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበ ትናንት በመቐለ ተካሂዷል። በሁለቱ ክልል አመራሮች መካከል ስለተደረሰው ስምምነት የተናገሩት የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳደር አቶ ሀፍቱ ኪሮስ፥ የተዘጉ መንገዶች ሊከፈቱና ከአዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀድሞ መኖርያቸው ሊመለሱ መግባባት መደረሱ ገልፀዋል።
ከአፋር ክልል በኩል ከመንግሥት አመራሮች በተጨማሪ የሀገር ሽማግሌዎችም በመቐለ መድረክ የተሳተፉ ሲሆን፥ የሕዝቦችን ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ ይሠራ ብለዋል። ከጦርነቱ መቆም በኋላ ከትግራይ ወደ ዓፋር እና ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የሚያገናኙ መንገዶች የተከፈቱ ቢሆንም የደኅንነት ስጋት እንዳላቸው በመንገደኞች ይገለፃል።
በሌላ በኩል በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው ከተፈናቀሉ ከአራት ዓመት በላይ እንደሆናቸው የሚገልፁት በተለያዩ መጠልያዎች ያሉ የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች የኢትዮጵያ መንግሥት ወደቀድሞ መኖርያቸው እንዲመልሳቸው ጥሪ አቅርበዋል። ከተፈናቃዮች መካከል የሆኑ ወጣቶች፥ የተፈናቃይ ዜጎች ድምፅ የሚያሰማ እና ችግሮች ለመፍታት ያለመ ያሉት የወልቃይት ሲቪክ ማኅበረሰብ የተባለ ተቋም ያደራጁ ሲሆን፥ ይህ አደረጃጀት ትናንት በሰጠው መግለጫ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ የምዕራብ ትግራይ ተወላጆች የመመለስ ተስፋ እያጡ ሊቢያን ጨምሮ ወደተለያዩ ሃገራት በገፍ እየተሰደዱ ነው ብሏል። «እንደ ማኅበረሰብ ተበትነን አንቀርም፣ ይህን ለመቀየር እንታገላለን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ተፈናቃዩን ለመመለስ ሀላፊነቱን ይወጣ» ሲሉም የሲቪክ ተቋሙ አስተባባሪ አድሓኖም ሰረፀ ተናግረዋል።
አድሓኖም ሰረፀ «የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ መንግሥት ይህ ሕዝብ የትም ተበትኖ መቅረት ስለሌለበት ወደቀዬአችን እንዲመልሰን እንላለን። ይህ ሕዝብ ወደ ቦታው ሳይመለስ በዚህ ሀገር ሰላም ይፀናል ብለን አናምንም። ዝም ብለን ተበትነን ልንቀር አንችልም፣ ያሉን ሁሉንም መፍትሔዎች እንጠቀማለን» ብልዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮችን ለመመለስ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እየሠራ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይሰማል። ይሁንና ባለፈው ዓመት መጨረሻ ወደቀዬአቸው ተመልሰዋል ከተባሉ በቁጥር ያነሱ የፀለምት እና ራያ ተፈናቃዮች ወጭ ከጦርነቱ መቆም ሁለት ዓመት በኋላም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አሁንም በትግራይ ክልል በተለያዩ መጠለያዎች ኑሯአቸውን እየገፉ ነው።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ