የትግራይ ነጻነት ፓርቲ አባላቶቼ ግድያና እንግልት ተፈጸመባቸው አለ
ዓርብ፣ ጥቅምት 8 2017የትግራይ ነጻነት ፓርቲ አባላቶቼ በትግራይ ክልል አስተዳደር በተለያዩ ዞኖች እየተገደሉ፤ እየተሰቃዩ፤ እየታፈኑ እና እየታሰሩብኝ ነው ሲል ከሰሰ ። የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደጀን መዝገበ በትግራይ ክልል ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ አስቸጋሪ ሆኗል ብለዋል ።
በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው የትግራይ ነፃነት ፓርቲ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው በክልሉ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ ከባድ እና የሕይወት ዋጋ የሚያስከፍል ሆንዋል ሲል አስታውቋል። የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር እንደሚለው በተለይም ከቅርብ ግዜ ወዲህ በትግራይ ክልል በከፍተኛ ደረጃ የተንሰራፋው ሕገወጥ የማዕድናት ምዝበራ የተቃወሙ በሰሜን ምዕራብ ዞን ያሉ የፓርቲው አባላት እና አመራሮች ግድያ፣ ድብደባ፣ እስራት እና እንግልት እየደረሳቸው መሆኑ የገለፀ ሲሆን አንድ የፓርቲያው አባል በታጣቂዎች ታፍኖ ከተወሰደ በኃላ መገደሉ እንዲሁም ሌሎች 16 የፓርቲው አባላትና አመራሮች እስር እና እንግልት እንደደረሳቸው ገልጿል።
የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ደጀን መዝገበ "ስልጣን ላይ ያለው ሐይል ለመናገሩ የሚያስነውር ግፍ በአባላቶቻችን እና አመራሮቻችን ላይ እየፈፀመ ነው። በተለይም በሰሜን ምዕራብ ዞን ይህ አካባቢ ነፃ ግዛታችን ነው በማለት፣ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ እዚህ አካባቢ መንቀሳቀስ የለበትም እየተባለ፣ ፓርቲያችን የብልፅግና ተላላኪ ነው የሚል ውሸት እየተለጠፈ፣ አባላቶቻችን እና አመራሮች ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸው ከባድ ህይወት እያለፉ ነው" ብለዋል።
ሕይወቱ ካለፈ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ አባል በተጨማሪ፥ ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች መኖራቸው፣ ይህ ጥቃት የከፋው ደግሞ ከህወሓት ጉባኤ በኃላ ባለው ግዜ ነው ሲሉ ጠቁመዋል። በትግራይ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ ከመቼውም ግዜ በላይ ፈታኝ የሆነበት ሁኔታ እንዳለ የገለፁት የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደጀን መዝገበ፥ የክልሉ አስተዳደር በትግራይ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት ከመስራት ይልቅ ተቃዋሚዎች ማሳደድ ላይ ተጠምዷል ሲሉ አክለው ገልፀዋል።
ዶክተር ደጀን "ፍፁም ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ነው እያደረግን ያለነው። መስራት ካለባቸው ለምን የተፈናቀለው ህዝባችን ለመመለስ አንሰራም፣ ስርዓት ለማስተካከል ለምን እንሰራም፣ ከዚህ ይልቅ መንግስት ለማቆም ለምን አንሰራም። እየተገፋን ነው። መጨረሻው ምን ይሆናል አናውቅም" ሲሉ አክለዋል።
የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ይህ በአመራሮቼ እና አባላቶቼ ላይ እየደረሰ ነው ያለው በደል እንደማይታገስ እና ለሕግ እንደሚያቀርበው ገልጿል። በዚህ የፖርቲው ክስ ዙርያ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ