1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ነጻነት ፓርቲና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውዝግብ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 13 2017

በትግራይ ክልል በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው የትግራይ ነፃነት ፓርቲ በክልሉ ሰላማዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ መቸገሩ ገለፀ። ፓርቲው የክልሉ አስተዳደር አካላት አባላቶቾን ከውጭ ሐይሎች ጋር በማስተሳሰር ጥቃት እያደረሱባቸው ነው ብሏል። የአስተዳደር አካላት በበኩላቸው የፓርቲው ክስ ይቃወማሉ።

https://p.dw.com/p/4m9R7
የትግራይ ነጻነት ፓርቲ
የትግራይ ነጻነት ፓርቲ መለያ አርማ ፎቶ ከማኅደርምስል Million Haileslassie/DW

የትግራይ ነጻነት ፓርቲና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውዝግብ

በትግራይ ክልል በተቃዋሚነት ከሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሆነው የትግራይ ነፃነት ፓርቲ በሰጠው መግለጫ፥ በአባላቶቹ እና አመራሮቹ ላይ የሚደርስ በደል ተጠናክሮ መቀጠሉ አስታውቋል። የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ አብርሃ ካሕሳይ በክልሉ ሰሜን ምዕራብ ዞን ያሉ የአስተዳደር አካላት፤ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ከኤርትራ ሐይሎች እንዲሁም ከብልፅግና ፓርቲ አካላት ጋር የማስተሳሰር ፍረጃ እንዲሁም ጥቃቶች እያደረሱባቸው መሆኑ ተናግረዋል።

አቶ አብርሃ «አባሎቻችን ላይ የውሸት ፍረጃ እየተሰራጨ፣ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ከሻዕብያ እና ብልፅግና በማያያዝም የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እየተሰራብን ነው። በተለይም በሽረ ክላስተር ባሉ አባሎቻችን እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ከባድ የማስፈራራት ሥራ በተጠናከረ መንገድ እየተካሄደ ነው» ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አለምሰገድ አረጋይ ይህ እየተፈፀመ ነው ያሉት ሕገወጥ ተግባር ፈፃሚዎቹ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ታጣቂ ሐይሎች ናቸው ብለዋል።

የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ይህ በተደጋጋሚ እና በበርካታ አባላቱ ላይ እየተፈፀ ነው ያለው ጥቃት፥ ከማስረጃ ጋር አስደግፎ ለክልሉ ፍትህ ቢሮ ማቅረቡንም አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ አብርሃ ካሕሳይ «ከትግራይ ነፃነት ፓርቲ ውጡ፥ ካልሆነ ሕይወታችሁን ታጣላችሁ፣ ለቤተሰቦቻቸው ደግሞ ልጆቻችሁን የምትፈልጓቸው ከሆነ ከፖርቲው እንዲወጡ አድርጉ ካልሆነ ነገ አታገኝዋቸውም እየተባለ በፀጥታ አካላት ማስፈራራት እየተካሄደ ነው» ነውም ብለዋል።

ይህን አስመልክቶ ከክልሉ አስተዳደር ኮምኒኬሽን ጽሕፈት ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም። ይሁንና በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን አስተዳደር የፀጥታና ሰላም ጽሕፈት ቤት ሐላፊ አቶ ተስፋይ አባዲ፥ የፓርቲውን አባላት ስም እየጠቀሱ ስለ ጉዳዩ ለክልሉ መንግሥታዊ ቴሌቭዥን ጣብያ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሐላፊው አንዳንዶቹን የትግራይ ነፃነት ፓርቲ አባላት ከኤርትራ ሐይሎች ጋር በመተባበር እንዲሁም ሕገወጥ ካሉት በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ከሚመራ አካል ጋር በማያያዝም ገልፀዋቸዋል።

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በክልሉ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው በተደጋጋሚ ይገልፃሉ።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ