የትግራይ ኃይሎች ከደቡብ ጎንደር ዞን ለቀው መውጣታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ | ኢትዮጵያ | DW | 23.08.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የትግራይ ኃይሎች ከደቡብ ጎንደር ዞን ለቀው መውጣታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ

የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ተቆጣጥረዋቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል ከደቡብ ጎንደር ዞን ለቀው መውጣታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ። የትግራይ ኃይሎች ከተቆጣጠሯቸው የደቡብ ጎንደር አካባቢዎች ለቀው የወጡት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ጋር ከተደረገ ውጊያ በኋላ ነው ተብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:30

የትግራይ ኃይሎች ከደቡብ ጎንደር ዞን ለቀው መውጣታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ

ህወሓት ለቀናት ተቆጣጥሯቸው የነበሩ የደቡብ ጎንደር ዞን ከተሞች በመንግስት ኃይሎች ነፃ መውጣታቸውን የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደርና ነዋሪዎች አመለከቱ። የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት ሥራ መጀመሩንም ዞኑ አስታውቋል፡፡

የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራ ክልል በመዝለቅ በሰሜን ወሎና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም በአፋር ክልል አንዳንድ ወረዳዎች ዘልቀው ጥቃት አድርሰዋል። በርካታ አካባቢዎችንም ተቆጣጥረዋል፡፡ በተለይ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ነፋስ መውጫ፣ ጨጨሆ፣ ክምር ድንጋይ ጉና እና ሌሎች ከተሞችን ተቆጣጥሮ ሰንብቷል፡፡ ህወሓት ወደ ደብረታቦር ከተማ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ ህይወትና ንብረትም ማውደሙን የደቡብ ጎንደር ዞን ብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ደጀኔ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው ሰሞኑን በተደረገ የተቀናጀ ኦፕሬሽን “ወራሪ” ያሉት ኃይል ከዞኑ ሁሉም ከተሞች ተጠራርጎ ወጥቷል ነው ያሉት፡፡ህወሓት በቆይታው መሰረተ ልማቶችንና በርካታ ንብረቶችን ማውደሙን የተናገሩት አቶ ጥላሁን፣ መልሶ የመገንባት ስራው መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ ለአገር ውስጥ መገናኛ ድርጅቶች በሰጡት አስተያየት የህወሓት ኃይሎች ከዞኑ በኃይል እንዲወጡ መደረጋቸውን አመልክተው የመልቀም ስራ ይቀራል ብለዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑ የነፋስ መውጫ ተወላጅ ለዴይቼ ቬለ እንዳሉት የትውልድ ቦታቸው ነፃ መውጣቱን ማረጋገጣቸውንና ወደ ቦታው ለመሄድና ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡ሁለት የደብረታቦር ከተማ ነዋሪዎችም አሁን በከተማው የተረጋጋ ሁኔታ እንዳለ ነው የተናገሩት፡፡ የህወሓትን አስተያየት ለማካተት ያደረግሁት ጥረት የመገናኛ መስመሮች በሙሉ ዝግ በመሆናቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡

ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሰ 
 

Audios and videos on the topic