1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ኃይሎች ማስጠንቀቂያ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 5 2016

አቶ ጌታቸው ረዳ ከኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መገናኘታቸውን የሕወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ይፋ አደረጉ ። ግንኙነቱ በሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ ውሳኔ መሰረት የተደረገ እንደነበር የገለፁት ሊቀመንበሩ፥ ስለተደረገው ግንኙነትም የፌደራሉ መንግስት እንዲያውቅ መደረጉን ገልጠዋል።

https://p.dw.com/p/4kTOo
የትግራይ ኃይሎች አዛዥ፤ ጀነራል ታደሰ ወረደ
የትግራይ ኃይሎች አዛዥ፤ ጀነራል ታደሰ ወረደምስል Million Haileselassie/DW

በጀነራል ታደሰ ወረደ የቀረቡ ክልከላዎች ላይ ከሁለቱ የሕወሓት ቡድኖች የተሰማ አስተያየት የለም

አቶ ጌታቸው ረዳ  ከኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መገናኘታቸውን የሕወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ይፋ አደረጉ ። ግንኙነቱ በሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ ውሳኔ መሰረት የተደረገ እንደነበር የገለፁት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፥ ስለተደረገው ግንኙነትም  የፌደራሉ መንግስት  እንዲያውቅ መደረጉን ገልጠዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ በትግራይ ክልል ያለውን ፖለቲካዊ ልዩነት ለማርገብ የተለያዩ ክልከላዎች በትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ተላለፏል ። 

በሕወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረው ፖለቲካዊ ልዩነት እየተባባሰ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ገለልተኛ አቋም እንደያዙ የሚገልፁት የትግራይ ኃይሎች፥ በሁለቱ የሕወሓት ቡድኖች መካከል እያየለ የመጣው መፋጠጥ እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል። የትግራይ ኃይሎች አዛዥ እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጄነራል ታደሰ ወረደ በሰጡት መግለጫ በሁለቱ አካላት በኩል ያለው መፋጠጥ እንዲረግብ ያለመ ክልከላዎች መቀመጣቸው ዐሳውቀዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተቆጣጠረው ክንፍ በየአካባቢው የሚያደርገው የሥልጣን ሹምሽር እንዲቆም፣ በማንኛውም የትግራይ አካባቢ የሚደረግ የድጋፍ ይሁን የተቃውሞ ሰልፎች እንዲከለከሉ፣ ጉባኤ ያደረገው ሕወሓት የሚያቀርበው የሥልጣን ይገባኛል ጥያቄ እንዲያቆይ መወሰኑ የገለፁት የትግራይ ኃይሎች አዛዥ የሆኑት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥  በጎራ ተለያይተው እየተወቃቀሱ ያሉ አካላትም ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።  ክልከላዎቹ ለረዥም ግዜ የሚዘልቁ ሳይሆን ፖለቲካዊ ትኩሳቱ ለማብረድ ያለሙ እና ከሁለቱ አካላት ጋር በመነጋገር የሚፈፀሙ መሆናቸው ጄነራሉ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት
አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንትምስል Million H. Silase/DW

ይህ የጄነራሉ መግለጫ በአንዳንዶች ዘንድ ሥልጣን ወደ ትግራይ ኃይሎች መጠቅለል ተደርጎ ተወስዶ እየተገለፀ ነው። በዚህ ጉዳይ ዙርያ፥ ወታደራዊው ኃይሉ ሲቪላዊ ሥልጣን ተቆጣጠረ ማለት አንችል ይሆን ? ተብሎ ከዶቼቨለ ለቀረበላቸው ጥያቄ ጄነራል ታደሰ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጄነራል ታደሰ "በፍፁም፥ የፀጥታ ኃይሉ የፀጥታ ሐይል ነው። ፀጥታ ለማስከበር ነው ይህ የምናደርገው። የፀጥታ ክፍተት ተፈጥሯል። የትግራይ ሕዝብ ድህንነት የተጠበቀ እንዲሆን፣ የህዝብ አንድነት እንዲረጋገጥ፣ ፖለቲከኞች ሰከን እንዲሉ ይህ የሚደረገው። ከዚህ ውጭ ፖለቲካዊ ስልጣን የሚይዝ፣ የያዘ የለም። ማግባባት እና መግባባት እንጂ ማስገደድም የለም። እንጂ ስልጣን ይዘህ ይህ አድርጉ ይህ አታድርጉ አይደለም እየሆነ ያለው" ብለዋል።

በእነዚህ በጀነራል ታደሰ ወረደ የቀረቡ ክልከላዎች ዙርያ ከሁለቱ የሕወሓት ቡድኖች የተንፀባረቀ አስተያየት የለም

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ ሰጥተዋል። በአብዛኛው በእርሳቸው እና በፓርቲያቸው ዙርያ የሚቀርቡ ክሶች አስመልክተው ማብራርያ የሰጡት ሊቀመንበሩ፥ በተለይም ከኤርትራ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ለሚቀርበው ክስ ምላሽ ሰጥተዋል።

የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ ሰጥተዋል
የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ ሰጥተዋልምስል Million Haileselassie/DW

ዶክተር ደብረፅዮን በመግለጫቸው በሕወሓት ውሳኔ መሰረት፥ አቶ ጌታቸው ረዳ ከኤርትራ መንግስት ባለሥልጣናት ጋር ከወራት በፊት በዱባይ መገናኘታቸው ይፋ አድርገዋል።

ደብረፅዮን "ፕሬዝደንት ጌታቸው  ከኤርትራ መሪዎች ጋር ግንኙነት አድርጓል። ሥራ አስፈፃሚው እና እኔ የማውቀው ግንኙነት ተደርጓል። ይህ መጥፎ አይደለም። ለሰላም ብለን ነው። ያለፈው በተጠያቂነት አሠራር ይታያል፥ አሁን ግን ወደ ችግር አታስገቡን፣ ወሰኖች ነፃ አድርጉ፣ ሰው ያግቱ ነበር አታግቱ ለማለት፣ እንስሳት ይዘርፉ ነበረ ሰዎች ያስሩ ነበር አቁሙ ለማለት ከኤርትራ መሪዎች ጋር በውጭ ሀገር ግንኙነቱ ተደርጓል። ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ እንዲያውቁት ተደርጓል። እሳቸውም ከእናንተ ጋር ቅሬታ አላቸው ተገናኙ ብለዋል። ይህ የታወቀ ነው። ይህ ስህተት የለውም። ጌታቸው ግን አይጠቅስም፣ ሌሎች አሉ የሚገናኙ ነው የሚለው" ሲሉ ተናግረዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ