1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ተፈናቃዮች ስሞታ

ማክሰኞ፣ መስከረም 14 2017

ከጦርነቱ መቆም በኃላ ወደቀዬአችን እንመለሳለን የሚል ተስፋ በተፈናቃዩ የነበረ ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ በመንግስት የተገባላቸው ቃል ሳይፈፀም ቀርቶ አስቸጋሪ ሕይወት በመጠልያዎች ለመግፋት መገደዳቸው እኚህ አባት ይናገራሉ። እንደ ተፈናቃዩ ገለፀ የክልሉ መሪዎች የተፈናቃዩ ችግር ለመፍታት ከመስራት ይልቅ "በስልጣን ሽኩቻ ተጠምደዋል" በማለት ይወቅሳሉ።

https://p.dw.com/p/4l2a5
ከተፈናቃዮቹ የተወሰኑት ወደየቀያቸዉ ቢመለስም አሁንም በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በየመጠለያ ጣቢያዉ ይገኛሉ
በትግራይ ጦርነት ወቅት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች ወደየቀያቸዉ እንዲመለሱ በቅርቡ በደባባይ ሠልፍ ጠይቀዉ ነበርምስል Million Hailesilassie/DW

የትግራይ ተፈናቃዮች ስሞታ

                       
በትግራይ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መንግስት ወደቀያችን ሊመልሰን የገባልን ቃል አላከበረም በማለት ምሬታቸውን ገለፁ።በትግራይ ጦርነት ወቅት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች እንደሚሉት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እና የፌደራሉ መንግስት ተፈናቃዮችን የመመለስ ተግባርና ኃላፊነታቸዉን ችላ ብለውታል ባዮች ናቸዉ።ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ከመቀሌ
የስድስት ቤተሰብ መሪው አቶ ገብረማርያም ገብረሚካኤል ከጦርነቱ ጅማሮ በፊት ኑሮአቸው በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ፀገዴ ነዋሪ የነበሩ ናቸው። በግብርናና ሌላ የግል ስራቸው ይተዳደሩ የነበሩት እኚህ አባት፥ ጦርነቱ ተከትሎ ከቀዬአቸው ከተፈናቀሉት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መካከል ናቸው። አቶ ገብረማርያም ከቤተሰቦቻቸው እና ሌሎች ተመሳሳይ ተፈናቃዮች ጋር በሽረ በሚገኘው የተፈናቃዮች መጠልያ ጣብያ መኖር ከጀመሩ አራተኛ አመታቸው ተቃርቧል። ከጦርነቱ መቆም በኃላ ወደቀዬአችን እንመለሳለን የሚል ተስፋ በተፈናቃዩ የነበረ ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ በመንግስት የተገባላቸው ቃል ሳይፈፀም ቀርቶ አስቸጋሪ ሕይወት በመጠልያዎች ለመግፋት መገደዳቸው እኚህ አባት ይናገራሉ። እንደ ተፈናቃዩ ገለፀ የክልሉ መሪዎች የተፈናቃዩ ችግር ለመፍታት ከመስራት ይልቅ "በስልጣን ሽኩቻ ተጠምደዋል" በማለት ይወቅሳሉ። 

መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም እርዳታ የማይደርሰው በርካታ ተፈናቃይ የከፋ ሕይወት እየመራ መሆኑ የገለፁልን ተፈናቃዮቹ፣ የሕክምና ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች በሌለበት ሁኔታ ተፈናቃዩ እየኖረ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

በቅርቡ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደርጋር የተወያዩት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ ተፈናቃዮች እስካሁን አለመመለሳቸው ለግዚያዊ አስተዳደር ፈተና ሆኖ እንዳለ ገልፀዋል። እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፃ ከ300 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በሽረ ከተማ ብቻ እንደሚኖሩ በወቅቱ ጠቁመው ነበር። 

ወደየቀያቸዉ ያልተመለሱ ተፈናቃዮች የክልሉንና የፌደራሉን መንግሥታት ባለሥልጣናት ይወቅሳሉ
በትግራዩ ጦርነት ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዉ መቀሌ ከተማ ከሠፈሩ የክልሉ ነዋሪዎች አንዷምስል Million Hailesillassie/DW

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ተፈናቃዮች እስካለፈው ሰኔ 30 ቀን 2016 ድረስ ይመለሳሉ ብሎ አስታውቆ የነበረ ሲሆን ይሁንና ከተወሰኑ ወደ ደቡባዊ እና ሰሜን ምዕራብ የትግራይ ዞኖች ከተመለሱ ውጪ አብዛኛው አሁንም በመጠልያዎች የከፋ ሕይወት እየመሩ ነው። ተፈናቃዩ አቶ ገብረማርያም ገብረሚካኤል የፌደራሉ መንግስት፣ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እና ዓለምአቀፍ ተቋማት ለተፈናቃዩ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባሉ። 

በቅርቡ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተው የነበሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ በትግራይ የተለያዩ ከተሞች ተበትነው ያሉት ተፈናቃዮች ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር መቀጠሉ ገልፀው እንደነበር ይታወሳል።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ