“የትግራይ መገንጠል?”፣ የበቀለ ገርባ ጤና | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 02.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

“የትግራይ መገንጠል?”፣ የበቀለ ገርባ ጤና

በማህበራዊ መገናኛዎች ሰሞነኛ መወያያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል “ትግራይን የመገንጠል ሀሳብ” የሚለው ላቅ ያለ ትኩረት ስቧል፡፡ በእስር ላይ የሚገኙት የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ የጤንነት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል መባሉ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ ለመከፈት ምክንያት ሆኗል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:13

በዚህ ሳምንት በማህበራዊ መገናኛዎች ዘመቻዎች ነበሩ

በኢትዮጵያውያን የፌስ ቡክ እና ትዊተር ተጠቃሚዎች ዘንድ ከሳምንት ሳምንት የማይበርድ አንድ አጀንዳ ቢኖር የብሔር እና የክልል ጉዳይ ነው፡፡ መልኩን እየቀያየረ እና በሰሞነኛ ጉዳዮች ላይ እየተንተራሰ የሚያወዛግበው ይህ አጀንዳ በዚህ ሳምንትም ከትግራይ ክልል ጋር በተገናኘ መወያያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የነገሩ መነሻ በመቀለ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ሙሉ ወርቅ ኪዳነ ማርያም ለአውራምባ ታይምስ ድረ ገጽ በትግርኛ የሰጡት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ መምህሩ በቃለ ምልልሱ “አብሮነት የሚያገዳድለን ከሆነ መለያየት አማራጭ መሆን አለበት” ሲሉ መናገራቸው በፌስ ቡክ ላይ ከወጣ በኋላ በተለያዩ ጎራ የተሰለፉ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችን አከራክሯል፡፡

ለገዢው ፓርቲ የሚወግነው ጦማሪ ፍጹም ብርሃነ የመምህሩን ሀሳብ ከህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ንግግር ጋር አነጻጽሮታል፡፡ “በትግራይ ህዝብ ላይ የጥላቻ ፖለቲካ እየተካሄደ ነው” ብሎ የሚያምነው ፍጹም የሁለቱን ሀሳብ ለችግሩ በመፍትሄነት በመውሰድ ተከታዩን በፌስ ቡክ ገጹ ጽፏል፡፡ “ከህወሓት ሊቀመንበር ‘ለሃገር ሲባል መስዋእትነት እንከፍላለን’ ተብሏል፡፡ ይሄ ሃሳብ ‘እስከአሁን በቂ መስዋእትነት ተከፍሏል፤ በአንድ እጅ አይጨበጨብም’ በሚል በተጋሩ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሌላው ሃሳብ ምሁራን ‘መለያየትን’ እንደ አማራጭ ጠቁመዋል። ይሄ ሃሳብ ከሊቀመንበሩ ‘የመስዋእትነት’ ሃሳብ የተሻለ ተቀባይነት ቢያገኝም የሚቃወሙት አላጣም። ችግሩ ወዲህ ነው፡፡ የመለያየቱን ሃሳብ የሚቃወሙት ከሊቀመንበሩ የተሻለ መፍትሄ ማምጣት አልቻሉም። ‘ከአባቶች የተረከብናት ኢትዮጵያ ወዘተ’ ከሚል የስሜት ወይም ወኔ ሙግቶች ባለፈ ህዝብን ከጥቃት የሚታደግ፣ ሃገርን ማዳንን ከጥላቻ ፖለቲካ ነፃ ሆኖ ከመኖር ጋር የሚያስታርቅ ሃሳብ ማቅረብ አልቻሉም። አሁን አጀንዳው ተከፍቷል” ብሏል፡፡ 

መለያየት የሚለውን የመቀሌ ዩኒቨርስቲውን መምህር ሀሳብ “የትግራይ ክልልን ለመገንጠል” እንደሚቀነቀን ሀሳብ አድርገው የወሰዱት ክፉኛ ተችተውታል፡፡ ከሀሳቡ ተቃሚዎች መካከል አንዱ ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ ማክሰኞ በፌስ ቡክ ተከታዩን አጋርቷል፡፡ “ትግራይ እኮ የትግራይም ብቻ አይደለችም። የጥንቱን በርካታ የታሪክ አሻራዎቻችንን ትተን የትናንቱን የባድመን ጉዳይ ብናነሳ እንኳ ትግራይ የትግራይ አይደለችም፤ ትግራይ የኢትዮጵያ ነች። ህዝቡም መሬቱም ከመላው ኢትዮጵያ በተዋጣ ደምና አጥንት ተጋምዷል። አንድ ቡድን ተነስቶ በሀገሪቱ ላይ የራሱን ውሳኔ ሊወስን እንደማይችል አለማወቅ “ሀገር ማለት ምን ማለት ነው?” የሚለውን ቀላል እውቀት ማጣት ነው። እውነቱ ግን! የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንግዲህ ከድንበሩ ቆርሶ የሚሰጠው መሬት ይቅርና እፍኝ አፈር የለም! በትግራይ ላይ ማንም የትናንት ሰው ተነስቶ ለመወሰን የሚያስችለው አንድም መድረክ አይኖርም። በፍጹም ስለ ትግራይ መገንጠል ልናወራ አንችልም። ያለፈው ይበቃናል!” ሲል ሀሳቡን አካፍሏል፡፡

አብዱልሃኪም ከድር የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው “ትግራይ መገንጠል አለባት ወይስ የለባትም የሚለው ነገር በዋናነት የሚወሰነው በኦሮሞ፣ በአማራና በደቡብ ሕዝቦች መልካም ፈቃድ ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው። ብለዋል፡፡ የፍጹም ወንድም እና የሆርን አፌርስ ድረገጽ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ዳንኤል ብርሃነ “ትግራይ ትገንጠል ቢባል እንኳ ብቻውን የምትወስነው ጉዳይ አይደለም” በሚለው የአብዱልሃኪም ሃሳብ ይስማማል፡፡ “ያለ ትግራይ ኢትዮጵያን ማሰብ አይቻልም። ስለዚህ ትግራይን የመገንጠል ሀሳብ የኢትዮጲያን ህልውና የማክተምና ያለማክተም ጉዳይ ነው። ይህን ውሳኔ ደግሞ ትግራዮች ብቻቸውን ሊወስኑት አይችሉም። እርግጥ የሀገሪቱ ፖለቲካ በግልብ ኤሊቶች እየተመራ ወደእርስ በእርስ ጦርነት ካመራ ጉዳዩ ውሳኔ እንዳገኘ ሊቆጠር ይችል ይሆናል። አለበለዚያ ትግራዮች ለዘመናት የተሸከሙትን የኢትዮጵያ ጠባቂነት ሚና ድንገት ብድግ ብለው ሊተዉት አይቻላቸውም” ሲል በስተኋላ አወዛጋቢ የሆነውን ጽሁፉን አስነብቧል፡፡ ።

“ትግራይን የመገንጠል ሀሳብ አዲስ ነገር አይደለም” ሲሉ የሚከራከሩት አቤነዘር ሲራክ ሀሳቡ እውን የማይሆንበትን ምክንያት በፌስ ቡክ ጽሁፋቸው ጠቅሰዋል፡፡ “ሲጀመር ህወሓት ኢትዮጵያዊ የሆነው የስልጣንና የጥቅም ጉዳይ ሆኖበት እንጂ ትግራይን የመገጠል አጀንዳማ እንደ ድርጅት የተነሳበት (founding principle) አቋም ነው፡፡ በርግጥ የትግራይ ህዝብ ለመገንጠል ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እውነታ አለው ወይ? የሚለው ሌላ እራሱን የቻለ ክርክር ነው፡፡ አስፈላጊም አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ትግራይ ታሪክ ከኢትዮጵያ ጋር የተተበተበ ነው፡፡ የህወሓት ፓለቲከኞች የኢትዮጵያን ፓለቲካ ስልጣን ማንንም ሳይስጠጉ እየመሩት ነው፤ታዲያ መገንጣል እያሉ ቡራ ከረዪ ለምን አስፈለገ ለምትሉ? መልሱ ግልፅ ነው፡፡ የዜግነታቸው (ኢትዮጵያዊነታቸው) ዋነኛ መሰረት ማለትም ስልጣናቸው እና ጥቅማቸው ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ገብቷል። ለህወሓት ሰዎች ኢትዮጵያዊነት ያለ ስልጣን እና ጥቅም ሊገባቸው ስለማይችል ነው” ሲሉ ሞግተዋል፡፡ 

የቀድሞው የአንድነት ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ ዘለቀ ረዲ የትግራይ የመገንጠል ሀሳብ ከየት የመነጨ ነው የሚለውን ረዘም ባለው የፌስ ቡክ ጹሁፋቸው መፈተሽ መርጠዋል፡፡ “ይህ ያልታደለ የትግራይ ህዝብ በየጊዜው እየተነሱ እንውቅልሃለን የሚሉ አንዳንድ ሰዎችን አያጣም። የወለዳቸውና ጡቱን አጥብቶ ያሳደጋቸው ልጆቹ መልሰው ጡቱን እየነከሱት አነሱ እየፋፉ ህዝብ አየመነመነ ለረጅም ጊዜ እባብ በበላ ዳዋ ተመታ እንዱሉ፤ ሌላው በበላ እሱ አየተወቀሰ መከራውን ሲበላ እንደከረመ ይታወቃል። ዛሬም ቢሆን በየቦታው በወንድሞቹ እየደረሰበት ያለው ወቀሳና ከሰሳ ወልዶ ባሳደገው በሕወሓት ካድሬዎች የመጣበት ቸግር ነው።  

በትግራይ ያሉ ገበሬዎች፣ ነጋዴዎች በሥርዓቱ የሚደርስባቸውን ግፍና በደል ሌላው ህብረተሰብ ሊረዳለት አልቻለም። በዚህ ላይ ለዚህች ሀገር መበታተን ሌት ተቀን ሲሰሩ የነበሩትና አሁንም እየሰሩ ያሉት እኩያን ነገሩን በማጋጋል ትግሉ ከህወሓት ኢህአዴግ ጋር ሳይሆን ከትግራውያን ጋር እንዲሆን አደረጉት። ሞኝ ምን እንዲሉ የነዚህ አጥፊዎች ሴራ ያልገባቸው አንዳንድ የዋሃን ትግሉ ከፓርቲው ይልቅ ወደ ህዝቡ እንዲዞር እምቡር እምቡር አሉ። ይህች መንገድ ነች የእንገንጠል ሴራ ይዛ የመጣችው” ሲል የሀሳቡ መነሻ የሚሉትን ለማስረዳት ሞክረዋል። 

በዚህ ጉዳይ የተነሳውን ክርክር የምንቋጨው አወዛጋቢውን ቃለ ምልልስ ከመቀለ ዩኒቨርስቲው መምህር አቶ ሙሉወርቅ ጋር ያደረገው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ በጉዳዩ ላይ ፌስ ቡክ በሰጠው አስተያየት ይሆናል፡፡“ በእኔ ቃለምልልስ ላይ መምህር ሙሉወርቅ የህገመንግስቱን አንቀጽ 39 አማራጭ እያቀረበለት ያለው ‘ከእናንተ ጋር የሚደረግን አብሮነት ፈጽሞ አልቀበልም፤ ባይሆን እየገደልኳችሁ ልኑር’ እያለ ላለ አካል ነው፡፡  ግን ሀሳቡን ካመጣችሁት አይቀር አንድ ነገር ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያን የመሰረተ የህብረተሰብ አካል፣ ራሱ በመሰረታት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግን አብሮነት ውግዘት፣ ጥፋትና ሞትን ብቻ በጊዜ ሂደት ይዞለት ከመጣ አንቀጽ 39ን እንደአማራጭ ቢታሰብ ምንድነው ችግሩ?” ሲል ጠይቋል ዳዊት፡፡ 

ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳያችን ተሻግረናል፡፡ ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች እንደ ፌስ ቡክ እና ትዊትር ባሉ ድረ ገጾች ሀሳባቸውን ከማካፈል ሌላ ትኩረት እንዲያገኙ ለሚሿቸው ጉዳዮች ዘመቻ ያካሄዱባቸዋል፡፡ ረቡዕ ጥር 23 ይፋ የተደረገውን ለድፍን አንድ ወር እንደሚቆይ የተነገረለት “የዓድዋን ድል በዓል በፌስ ቡክ እናክብር” የሚለው ዘመቻ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለዚህ የፌስ ቡክ ዘመቻ በቀናት ውስጥ ወደ አንድ ሺህ ገደማ ሰዎች ፍላጎታቸውን ያሳዩ ሲሆን በርካቶች ከወዲሁ የፕሮፋይል ምስላቸውን አድዋን በሚያስታውሱ ፎቶዎች ሲያስጌጡ ተስተውለዋል፡፡ 

ትላንት ሐሙስ በፌስ ቡክ እና በትዊትር የተካሄደው ሌላኛው ዘመቻም እንዲሁ በርካቶች ተሳትፈውበታል፡፡ ዘመቻው በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ አሳሳቢ የጤንነት ሁኔታ የሚመለከት ነው፡፡ የምክትል ሊቀመንበሩ ልጅ ቦንቱ በቀለ አባቷ ደም ግፊታቸው በመጨመሩ ምክንያት የግራ አይናቸው መጎዳቱን ለመገናኛ ብዙሃን መግለጿን ተከትሎ ነበር “አስቸኳይ ህክምና ለበቀለ ገርባ” በሚል መሪ ቃል ዘመቻ የተከፈተው፡፡ 

ጋዲሳ ሆማ በፌስ ቡክ “ኦቦ በቀለ ገርባ በህግ ጥላ ሥር ያሉ ሰው ናቸው። እንኳንስ በመንግሥት በግፍ ታስሮ እንቅስቃሴው የተገደበ ሰው ይቅርና ማንኛውም ዜጋ ጤንናቱ ተጠብቆ የመኖር መብት አለው። እስረኛን ህክምና ከልክሎ የጤና እክሎች ልታከሙ ከማይችሉበት ደረጃ እስክደርሱ መጠበቅና የሰዎችን አካልና ህይወት አደጋ ላይ መጣል ፍጹም ኢሰብአዊነት ነው” ሲል ጽፏል። ሚልኪሳ ጪምዲሳ ተመሳሳይ መልዕክት በትዊተር ገጹ አስፍሯል፡፡ “እስረኞች ህክምና የማግኘት መብት አላቸው፡፡ እንደ ተባበበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ ከሆነ መንግስት አንድ ሰው ካሰረ እና በቁጥጥር ስር ካዋለ የእርሱን ደህንነት እና በህይወት መቆየት ለመጠበቅ የጤና አገልግሎት የማቅረብ ኃላፊነት አለበት” ሲል ለአቶ በቀለ ተሟግቷል፡፡

አብዲ ለሜሳ “የህክምና አገልግሎት መንፈግ የኢትዮጵያ መንግስት በፖለቲካ እስረኞች ላይ ከሚፈጽመው ወንጀል ውስጥ የከፋው ነው” ብሏል በትዊተር ገጹ፡፡ ሮማን ግርማ ደግሞ በፌስቡክ  “በፖለቲካ እምነታቸው ምክንያት በእስር ቤት የተቆለፈባቸው መሆኑ እና ያለፉባቸው ኢ-ፍትሀዊ ነገሮች አልበቃ ያሉ ይመስል አሁን ደግሞ ተገቢውን የህክምና ክትትል ተነፍገዋል” ስትል ተቃውሟዋን ገልጻለች፡፡ 

ዘካርያስ ዘላለም በትዊተር “በቀለ ገርባ ከሚለቀቁ እስረኞች መካከል ይሆናሉ በሚል ጭላንጭል ተስፋ የነበራቸው ቤተሰቦቻቸው የተመለከቱት ነገር ቢኖር እስራቸው መቀጠሉን ፣ የጤናቸው እና የዓይናቸው ሁኔታ በጣሙኑ ማሽቆልቆሉን ብቻ ነው፡፡ 2018 በእርግጥም አስከፊ ዓመታቸው ነው” ሲል ትዝብቱን አጋርቷል፡፡ ዘውዱ ታደሰ በበኩላቸው “በፍትህ ስም እልህ ለመወጣት ህክምና ከልክሎ ያውም ሚሊዬኖች ከሀላው እሚከተሉትን ሰው እንዲህ ማንገላታት ለዴሞክራሲ መዳበርም ይሁን እነሱ እንደሚሉት ለብሔራዊ እርቅ ሳይሆን የሚጠቅመው ይባስ ለሌላ ሀገራዊ ቀውስ በር ከፍች ነገር ስርዐቱ እየሰራ እንደሆነ ሹመኞቹ ሊያውቁ ይገባል” ሲሉ በፌስ ቡክ ማስጠንቀቂያ አዘል ጹሁፋቸው ቋጭተዋል።

የዛሬውን መሰናዷችንን የምንጠቃልለው በሌላ እስረኛ ጉዳይ ነው፡፡ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል የታሰሩት የልብ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የእስር ጊዜያቸውን በመጨረሳቸው መፈታት ቢገባቸውም ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ በሽብር በመከሰሳቸው ጉዳያቸውን በእስር ላይ ሆነው እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ዶ/ር ፍቅሩ በዚህ ሳምንት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የጻፉት ግልጽ ደብዳቤ በፌስ ቡክ ከወጣ በኋላ በርካቶች ተቀባብለውታል፡፡ ደብዳቤውን ለንባብ ያበቃው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ነው፡፡ ጋዜጠኛ ጌታቸው ስለ ደብዳቤው ይዘት እና ስለ ማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች አስተያየት የተናገረውን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።  

ተስፋለም ወልደየስ 

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic