1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትኞቹ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሊገቡ ይችላሉ?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጳጉሜን 2 2014

ኢትዮጵያ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የሚመዘገብ ተቀጽላ ኩባንያ አቋቁመው የባንክ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚፈቅድ ፖሊሲ አጽድቃለች። ፖሊሲው የውጭ ባንኮች ቅርንጫፍ እንዲከፍቱ፤ አክሲዮን በመግዛት በሽርክና ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር እንዲሰሩ ይፈቅዳል። የትኞቹ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ? የአገር ውስጥ ባንኮችስ ምን ያክል ዝግጁ ናቸው?

https://p.dw.com/p/4GXbY
Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የትኞቹ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሊገቡ ይችላሉ?

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ባንኮች "ከፍ ላለ ውድድር" እንዲዘጋጁ የካቲት 15 ቀን 2014 የሰጡትን ማስጠንቀቂያ እውን የሚያደርገው ፖሊሲ ባለፈው ቅዳሜ ጸድቋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2014 ያጸደቀው ፖሊሲ "የባንክ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት" የሚያደርግ ነው። የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ያለውን ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፤ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር፤ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንዲሳለጥ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እንደሚደረግ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ቁጥጥር ዳሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው ይኸ ፖሊሲ "አንድ ውጭ አገር ያለ ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመሠረት እና የሚመዘገብ ተቀጽላ ኩባንያ አቋቁሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የባንክ አገልግሎት እንዲሰጥ" የሚፈቅድ መሆኑን ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል።

"ሁለተኛው የአገባብ ስልት አገር ውስጥ እየሰሩ ያሉ ባንኮች ላይ ወይም አዳዲስ ባንኮች ላይ አክሲዮን በመግዛት በሽርክና ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር" ተጣምረው የሚሰሩበት መንገድ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍሬዘር የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ እንዲከፍቱ ወይም ከዚህ ቀደም ያደርጉት እንደነበረው በውክልና ቢሮ ሥራቸውን እንዲያከውኑ እንደሚፈቀድ ዘርዝረዋል።  

በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት "የውጭ ሀገር ዜጎች ወይም በከፊልም ሆነ በሙሉ በውጭ ሀገር ዜጎች ባለቤትነት ሥር ያሉ ድርጅቶች ወይም የውጭ ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ሥራ ማካሔድ ወይም የባንክ ሥራ የሚያካሒድ ቅርንጫፍ ሊያቋቁሙ አይችሉም።" ከዚህ በተጨማሪ "በኢትዮጵያ ውስጥ በተቋቋሙ ባንኮች አክሲዮን መያዝ" በጳጉሜ 2011 በወጣው የባንክ ሥራ ማሻሻያ አዋጅ መሠረት ተከልክለው ቆይተዋል። የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ የውጭዎቹ ባንኮች ወደ አገሪቱ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅደው ሕግ እየተረቀቀ እንደሆነ ተናግረዋል።

Yinager Dessie Belay, äthiopischer Nationalplanungskommissar
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ የውጭዎቹ ባንኮች ወደ አገሪቱ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅደው ሕግ እየተረቀቀ እንደሆነ ተናግረዋል።ምስል picture-alliance/M.Kamaci

የትኞቹ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሊገቡ ይችላሉ?

የኢትዮጵያ መንግሥት ለባንክ አገልግሎት ዘርፍ የሚያዘጋጀው ፖሊሲ እና ሕግ የውጭዎቹ ባንኮች ወደ ገበያው ለመግባት በሚኖራቸው ፍላጎት ላይ የራሱን ሚና እንደሚጫወት በዴሎይት አማካሪ ተቋም የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮ የኮርፖሬት ፋይናንስ እና ኤኮኖሚ አማካሪ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ሲሳይ ይናገራሉ።

"ኮርፖሬት ላይ ብቻ መተኮር አለባችሁ ብትላቸው ብዙዎቹ [ወደ ኢትዮጵያ] ለመምጣት ፍላጎት አይኖራቸውም። ወይም እናንተ ማተኮር ያለባችሁ የማምረቻው ዘርፍ ላይ ብቻ ነው ብትላቸውም ፍላጎት አይኖራቸውም" የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ "ከኢንደስትሪ አኳያ ስሱ የሆነ ነገር ካልሆነ በስተቀር ከዚያ ውጪ ላለ ነገር መከልከል አለባቸው ብዬ አላስብም" ሲሉ አስረድተዋል።

"ከፖሊሲ አኳያ ይኸን ትሰራላችሁ ይኸን አትሰሩም" ከሚል ገደብ በተጨማሪ "በግል ባንኮች ውስጥ ምን ያህል እንዲገዙ ይፈቀድላቸዋል?" የሚለው ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የመግባት ፍላጎታቸውንም ሆነ "ይዘው የሚመጡትን ገንዘብ" እንደሚወስን አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል። 

ከዚህ ቀደም ከቱርክ ዚራት ባንክ፣ ከደቡብ አፍሪካ ስታንዳርድ ባንክ እንዲሁም ከኬንያ ኬሲቢ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የመግባት ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል። በገንዘብ ጉዳዮች ላይ በ174 አገሮች የማማከር አገልግሎት የሚሰጠው ቢንደር ዳይከር ኦተ (BDO) የኢትዮጵያ ቢሮ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ክብረት ወደ አገሪቱ ገበያ የመግባት "ፍላጎታቸውን" እርሳቸው ለሚመሩት ኩባንያ የገለጹ ዓለም አቀፍ እና አኅጉራዊ ባንኮች መኖራቸውን ይናገራሉ።

"እጅግ በጣም ትላልቅ ባንኮች እዚህ አገር መጥተው ከትናንሽ ባንኮች ጋር ለመስራት ፈቃደኛ አይደሉም" የሚሉት አቶ ሚሊዮን "የጅምላ አይነት የባንክ አገልግሎት" ቀልባቸውን ሊገዛ እንደሚችል ተናግረዋል።

Äthiopien Commercial Bank of Ethiopia in Addis Abeba
የኢትዮጵያ ባንኮች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ቢያድግም አሁንም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገበያው ከፍተኛ ድርሻ አለው። የውጭ ባንኮች ወደ ገበያው ሲገቡ ለአነስተኛ እና መለስተኛ ባንኮች ብርቱ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። ምስል DW/E. Bekele

"የጅምላ ንግድ ማለት መንግሥትን ጨምሮ ትላልቅ ለሆኑ ተቋማት ብቻ ገንዘብ በማቅረብ ከእነሱ ጋር ለመስራት የሚመጡ ባንኮች አሉ። እንዲሁም እነዚህ ባንኮች ገንዘብ ለአገር ውስጥ ባንኮች ይሰጡ እና፤ የአገር ውስጥ ባንኮች ለግለሰቦች እና ትናንሽ ኩባንያዎች እንዲሰጡ አብረው ሊሰሩ ይችላሉ" ሲሉ አቶ ሚሊዮን አስረድተዋል። አኅጉራዊ ባንኮች በአንጻሩ አቶ ሚሊዮን እንደሚሉት "ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር አብረው ሊሰሩ፤ ከተፈቀደላቸው እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ባንኮች ለግለሰቦች እና ለተቋማት እያበደሩ" ለመስራት ወደ ኢትዮጵያ ያቀናሉ።

አቶ ቴዎድሮስ ግን ከዓለም አቀፍ ባንኮች ይልቅ አኅጉራዊዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ሊያመሩ እንደሚችሉ ያስረዳሉ። ለዚህም የብሪታንያው በርክሌይስ ባንክን ጨምሮ የአውሮፓ ባንኮች ከኢትዮጵያ ከሚቀራረቡ የአፍሪካ አገሮች ገበያዎች ውድድር መቋቋም አቅቷቸው አሊያም ሥራቸው አዋጪ ባለመሆኑ ጥለው መውጣታቸውን በማሳያነት ይጠቅሳሉ። "እንደነ ስታንዳርድ ባንክ፣ አክሰስ ባንክ፣ ኬሲቢ፣ ኢኩዊቲ ባንክ ያሉ አኅጉራዊ ባንኮች" የኢትዮጵያ ገበያ ጠባይ ከሚሰሩባቸው አገሮች ጋር ስለሚቀራረብ ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚችል አቶ ቴዎድሮስ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዘዋወር እና ተዘግተው የቆዩ ዘርፎችን ለውጭ ባለወረቶች ለመክፈት የምታደርገው ጥረት የሰሜኑ ጦርነት ጥላ አርፎበታል። መንግሥት በቴሌኮም ዘርፉ መሠማራት ለሚፈልጉ በግንቦት 2012 ጥሪ ሲያቀርብ አስራ ሁለት ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን ቢያሳውቁም በመጨረሻው ጨረታ የተሳተፉት ግን ሁለት ብቻ ነበሩ። ለኩባንያዎቹ ማፈግፈግ በምክንያትነት ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አንዱ ነበር።

ፍላጎት ያሳዩ የቴሌኮም ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ጨረታ ለምን አፈገፈጉ?

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመላካች ነገር ከተናገሩ በኋላ እኛንም የሚያነጋግሩን በጣም ብዙ የውጭ ባንኮች አሉ" የሚሉት የውጭ ባለወረቶችን ፍላጎት በሥራቸው ምክንያት ቀረብ ብሎ የመታዘብ ዕድል ያላቸው አቶ ሚሊዮን "ምንም እንኳ የፖለቲካው እና የጦርነቱ ሁኔታ በንግድ ላይ አሉታዊ አስተዋጽዖ ቢኖረውም አሁንም ከአገሪቱ ስፋት፣ ከአገሪቱ የሕዝብ ብዛት አንጻር እና ገና ብዙ ዘርፎች አለመነካታቸውን ስለሚያውቁ እዚያ ላይ ለመስራት እጅግ በጣም ፍላጎታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ። ይኸን ደግሞ እኛም በገሀድ አይተንዋል" ሲሉ አስረድተዋል።

FinCEN Files / Barclays, London
ጣልያን ኢትዮጵያን በወረራ በተቆጣጠረችባቸው አምስት ዓመታት ባንኮ ዲ ኢታሊያ፣ ባንኮ ዲ ሮማ ፣ ባንኮ ዲ ናፖሊ፣ ባንኮ ናስዮናል ዴል ላቮሮን የመሳሰሉ ባንኮቿ በአገሪቱ ሥራ ጀምረው ነበር። ጣልያኖች ከኢትዮጵያ በተባረሩበት 1933 ከብሪታኒያ ወታደሮች ጋር ወደ አገሪቱ ያመራው ባርክሌይስ ባንክ በአዲስ አበባ ሥራ ጀምሮ ነበር። ይሁንና ከሁለት ዓመታት በኋላ እርሱም ከኢትዮጵያ ጥሎ ወጥቷል። ምስል picture-alliance/Photoshot

እነማን ነበሩ?

የኢትዮጵያ ገበያ ለውጭ ባንኮች እንግዳ አይደለም። ባንኮቹ በኢትዮጵያ የሰሩባቸው ዓመታትም ሆነ ለአገሪቱ ያበረከቱት አስተዋጽዖ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ጣልያን ኢትዮጵያን በወረራ በተቆጣጠረችባቸው አምስት ዓመታት ባንኮ ዲ ኢታሊያ፣ ባንኮ ዲ ሮማ ፣ ባንኮ ዲ ናፖሊ፣ ባንኮ ናስዮናል ዴል ላቮሮን የመሳሰሉ ባንኮቿ በአገሪቱ ሥራ ጀምረው ነበር። በአስመራ ከቀሩት ባንኮ ዲ ሮማ እና ባንኮ ዲ ናፖሊ በቀር ሌሎቹ የጣልያን ኢትዮጵያን በቅኝ የመግዛት ሙከራ ሲከሽፍ ሥራቸውን አቁመዋል።

ጣልያኖች ከኢትዮጵያ በተባረሩበት 1933 ከብሪታኒያ ወታደሮች ጋር ወደ አገሪቱ ያመራው ባርክሌይስ ባንክ በአዲስ አበባ ሥራ ጀምሮ ነበር። ይሁንና ከሁለት ዓመታት በኋላ እርሱም ከኢትዮጵያ ጥሎ ወጥቷል። የመጀመሪያው የግል ባንክ በጎርጎሮሳዊው 1964 በኢትዮጵያውያን የተቋቋመው የአዲስ አበባ ባንክ ነው። ባንኩ ሁለት ሚሊዮን ብር ካፒታል የነበረው ሲሆን 40 በመቶው ድርሻ መቀመጫውን በለንደን ባደረገው ናሽናል ኤንድ ግሪንድሌይ ባንክ (National and Grindlay Bank) የተያዘ ነበር። 

አጼ ምኒልክ በ1897 በእንግሊዞች ቁጥጥር ሥር ከነበረው የግብፅ ባንክ ጋር በተፈራረሙት ውል መሠረት በ1ዐዐ, ዐዐዐ ፓውንድ በተቋቋመው ሀበሻ ባንክ (Bank of Abysinia) የተጀመረው የኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት በርካታ የታሪክ አንጓዎች አሉት። ገበያውን የመቆጣጠር ሥልጣን በተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድረ-ገጽ እንደሰፈረው በአሁኑ ወቅት 27 የንግድ ባንኮች በሥራ ላይ ይገኛሉ።

የቀድሞው የኅብረት ባንክ እና የኢትዮጵያ የባንክ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ ብርሀኑ ጌታነህ እነዚህ የአገሪቱ ባንኮች ከዓለም አቀፉ ገበያ ሊገቡ ከሚችሉት ጋር ለመወዳደር ዝግጁ ለመሆናቸው ጥርጣሬ አላቸው። "እኛ አገር አብሮ የመስራት ጉዳይ ብዙ ፈተና ያለበት ነው። ባንኮቹ የተቋቋሙበትን ሥረ-መሠረት ስታየው አንዳንዱ በብሔር ነው። አንዳንዱ መሠረቱ በሐይማኖት ሊሆን ይችላል። በጾታም አለ። የእኛ አገር የባንክ አደረጃጀት ድብልቅልቅ ነው። ይኸም ሆኖ ወደ 60 በመቶ የገበያውን ድርሻ የሚይዘው የመንግሥት ባንክ ነው። ይኸ ባለበት ሁኔታ እስካሁን ያደረጉት ዝግጅት ምንም የለም ብዬ ነው የማምነው" ሲሉ አቶ ብርሀኑ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ምን ዓይነት ውድድር?

የኢትዮጵያ ባንኮች የሚሰጡት አገልግሎት ኬንያን ከመሳሰሉ ጎረቤቶቿ እንኳ ሲወዳደር "ኋላ ቀር" እየተባለ ይወቀሳል። ቢንደር ዳይከር ኦተ (BDO) የተባለው የፋይናንስ አማካሪ ተቋም የኢትዮጵያ ቢሮ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን የአገሪቱ ባንኮች በማስያዣ ብድር የሚሰጡበትን ስልት "ኋላ ቀር እና ለአገር ዕድገትም የማይጠቅም" እያሉ ይነቅፋሉ። አቶ ሚሊዮን የውጭ ተወዳዳሪ ባንኮች ሲገቡ በገበያው የሚቀርበው አገልግሎት "የፋይናንስ ትንተናን መሠረት ያደረገ እና ውድድርን መሠረት ያደረገ" ሊሆን እንደሚችል ይጠብቃሉ። በገበያው ውድድር የሚፈጠር አገልግሎት በተለይ የብድር አቅርቦት "በጣም አዋጪ እና እጅግ አበረታች የሆኑ መዋዕለ-ንዋዮችን" የሚደግፍ ሊሆን እንደሚችልም አቶ ሚሊዮን እምነታቸውን ገልጸዋል።

Äthiopien Addis Abeba Tsehay Insurance & Nib Bank
በአሁኑ ወቅት 27 ባንኮች በገበያው እንደሚገኙ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድረ ገጽ የሰፈረ መረጃ ይጠቁማል። ሌሎች በምሥረታ ላይ የሚገኙ ከ20 በላይ ባንኮች ገበያውን ለመቀላቀል ፈቃድ መጠየቃቸውን ዶይቼ ቬለ ለመረዳት ችሏል። ባንኮቹ ከውጭዎቹ ለሚገጥማቸው ውድድር ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ምስል DW/E. Bekele Tekle

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ጥቅምት 2014 ባንክ ለመመስረት የሚያስፈልገውን ዝቅተኛ ካፒታል ከ500 ሚሊዮን ብር ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ አድርጓል። ይሁንና በምሥረታ ላይ የሚገኙ ከ20 በላይ ባንኮች ፈቃድ መጠየቃቸውን ዶይቼ ቬለ ለመረዳት ችሏል። የኢትዮጵያ እና የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን የባንክ ገበያ በቅርብ የሚከታተሉት አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት ባንኮቹ ቁጥራቸው ቢበዛም በገበያው ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉት ግን ጥቂቶች ብቻ ይሆናሉ።

"ጠንካራ የሚሆኑት ከ1 እስከ 10 ካሉት በላይ አይሆኑም። ከዚያ በታች ያሉት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደንበኛ ወይንም ቅርንጫፍ ያላቸው ካሉ ትላልቆቹ ትናንሾቹን ከገበያ ገፍተው ያስወጧቸዋል" የሚሉት አቶ ቴድሮስ የአገር ውስጥ ባንኮች ቁጥር እስከ 40 ቢደርስ እንኳ "አንዳንዶቹ ፈቃዱን ይዞ መቀመጥ ካልሆነ በስተቀር ገበያው ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ አይኖራቸውም" ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭዎቹ በሚገጥማቸው ውድድር "እንዳይቀጭጩ፣ መጨረሻ ላይም እንዳይጠፉ ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው" ሊሰሩ የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸው አቶ ብርሀኑ ጌታነህ ይመክራሉ። የቀድሞው የኅብረት ባንክ ፕሬዝደንት "ለምሳሌ ሁለት ሶስት ባንኮች አንድ ላይ ቢጣመሩ የሥራ ማስኬጃ ወጪያቸውን ያቃልላሉ። ሁለተኛ ተደራሽነታቸውን ያሰፋሉ። ሶስተኛ የካፒታል አቅማቸውን ያጠናክራሉ" ሲሉ የመወሀድን ፋይዳ ይገልጹታል።

የኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ለውጪዎቹ ቢከፈት ማን ተጠቅሞ ማን ይጎዳል?

አቶ ብርሀኑ ሁለተኛ አማራጭ አድርገው የሚያቀርቡት የአገር ውስጥ ባንኮች ከተወዳዳሪዎቻቸው ልቀው ለመገኘት  የሚያስችሏቸው ስትራቴጂዎች መንደፍ ነው። የቀድሞው የባንክ ባለሙያ "ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት፣ የሴቶች፣ የተማሪዎች እና የመሳሰሉት ላይ እንሰራለን ብለው ማሰብ አለባቸው" ይላሉ። ሶስተኛው አማራጭ ወደ ገበያው ከሚገቡ ባንኮች ጋር በሽርክና መስራት ሲሆን  የመጨረሻው "የውጭ ባንኮችን እንቅስቃሴ አይቶ ከዚያ በኋላ እርምጃ መውሰድ ነው።" አቶ ብርሀኑ "ስትራቴጂው የራሱ ጥቅምም ጉዳትም ስላለው ይኸንን ካሁኑ በጥልቀት በማጥናት መዘጋጀት አለባቸው ብዬ አምናለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

ዘርፉ የሚፈልገው የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ቴክኖሎጂ የአገር ውስጥ ባንኮች ድንበር ተሻግረው ወደ ገበያው ከሚገቡ የውጭ ተቋማት የሚወዳደሩባቸው ተጨማሪ ዘርፎች ናቸው። የኢትዮጵያ ባንኮች አገልግሎቶቻቸውም ሆነ ቅርንጫፎቻቸው በአዲስ አበባ እና ከተሞች ላይ ያተኮሩ ናቸው እየተባሉ ይተቻሉ። በኢንተርኔት እና በሞባይል ስልኮች አማካኝነት የሚቀርቡ የባንክ አገልግሎቶች ዘርፉን እየቀየሩ በመሆኑ የሚስማሙት አቶ ቴዎድሮስ ሲሳይ እና አቶ ሚሊዮን ክብረት ከውጭ ከሚገቡ ባንኮች በርከት ያሉ ቅርንጫፎች አይጠብቁም። የውጭዎቹ ባንኮች በተካኑባቸው የኢንተርኔት እና የሞባይል ባንክ አገልግሎቶች የፋይናንስ ተደራሽነትን ሊያሰፉት እንደሚችሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ