1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚሰሜን አሜሪካ

የትራምፕ አስተዳደር የኤኮኖሚ ጦርነት

አበበ ፈለቀ
ማክሰኞ፣ ጥር 27 2017

ዶናልድ ትራምፕ በካናዳ፣ በመክሲኮና በቻይና ላይ የጣሉት ቀረጥ የንግድ ሽኩቻና ስጋትን ፈጥሯል። ትራምፕ ከሜክሲኮና ከካናዳ መሪዎች ጋ ባደረጉት ውይይት የቀረጥ ውሳኔው ለአንድ ወር እንዳይፈጸም ተስማምተዋል። ቻይና በበኩሏ ቅሬታዋን ለዓለም የንግድ ድርጅት ያቀረበች ሲሆን ከአሜሪካ በሚገቡ ዕቃወች ላይ ቀረጥ በመጣል የበኩሏን እርምጃ ወስዳለች።

https://p.dw.com/p/4q0yz
 ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ
አሜሪካን ዳግም ታላቅ አደርጋለሁ ያሉት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ምስል IMAGO/Newscom/GDA

የትራምፕ የኤኮኖሚ ጦርነት

በምረጡኝ ዘመቻቸው እንደዛቱት፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው ቅዳሜ ከካናዳና ከሜክሲኮ በሚመጡ ዕቃዎች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ፣ ከቻይና በሚመጡ ሸቀጦች ላይ ደግሞ 10 በመቶ ቀርጥ መጣላቸውን ተከትሎ፣ የአሜሪካና የሦስቱ ሃገራት እሰጥ አገባ ተጋግሎ፣ ኢኮኖሚውም የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቶ ተስተውሏል። የስደተኞች ጥበቃን፣ የአደንዛዥ እጽ ሽግግርን መግታትና መሰል ጉዳዮችን ከዚሁ የቀረጥ ጭማሪ ጋ አያይዘውታል። ዓለም ባንክንና የአፍሪካ ልማት ባንክ ጨመሮ በበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያገለገሉት የኢኮኖሚ ባለሞያው ዶ/ር ዮናስ ብሩ የፕሬዝዳንቱ የቀረጥ መጣል አላማና ግብ ከኢኮኖሚያዊ ዋጋው በላይ ትራምፕ ከሃገራቱ የሚፈልጉትን ነገሮች ለማግኘት እንደ መደራደርያ መሣርያነት ጥቅም ላይ እንደዋለ ይናገራሉ።

ወዳጅም ሆነ ተቀናቃኝ ሀገር ሳይለዩ ሁሉንም አስገብራለሁ ብለው የዛቱት ትራምፕ፣ የጠበቃቸው የሰላ ተቃውሞና የበቀል እርምጃ ነበር። የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ይሄንኑ ቀረጥ «በኢኮኖሚ መረጋጋት ላይ የተጋረጠ ቀጥተኛ ስጋት» በማለት አውግዘው፣ የእርሻ ውጤቶችን፣ ብረታ ብረትንና አልኮል መጠጦችን ጨምሮ በበርካታ የአሜሪካ ምርቶች ላይ ቀረጥ ለመጣል ዝተው ነበር።

«ለውይይትና ለንግግር ሁል ጊዜም ዝግጁ ነን» ያሉት የሜክሲኮዋ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሸንባውም «ያ ካልሆነ ግን የምንወስዳቸው በርካታ አማራጮችን አዘጋጅተናል» ነው ያሉት ።

ይሄው የአሜሪካ ውሳኔ ከኢኮኖሚያዊ ጫናው ባሻገር በካናዳ ሕዝብ በኩል ከፍተኛ የሆነ የመካድ ስሜትን እንደፈጠረ ያነጋገርኩት በካናዳ፣ ኦንታርዮ ነዋሪ የሆነው ጋዜጠኛ ዳግማዊ ታሪኩ ገልጿል። ይሄው የቀረጥ እሰጥ አገባ በአሜሪካ ኢኮኖሚ ውስጥም ያለመረጋጋትና ሌላ ውጥረትን ፈጥሮ ነው የቆየው። ከቲማቲም፣ እስከ አቡካዶ፣ ከመኪና ዕቃ እስከ ነዳጅ፣ ከእንጨት፣ እስከ ብረታ ብረት በርካታ ዕቃዎች ይወደዱ ይሆናል የሚል ፍርሃት ሰፍኖ ነበር። የክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ ነዋሪ የሆኑትና በሬስቶራንት አና በሪል ስቴት ሥራ ላይ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ለማ ጌታቸውም ይሄንኑ ስጋት ይጋሩታል።

ይሄንን ሁሉ ውጥረት ተከትሎ ነው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሜክሲኮም ከካናዳም መሪዎች ጋር አስቸኳይ የስልክ ውይይት አድርገው የተባለው ቀረጥ ለ30 ቀናት ያህል ተግባራዊ እንዳይሆን የተስማሙት።  በስምምነቱ መሠረትም ካናዳ የአደንዛዥ እጽ ዝውውሩን በድንበሯ በኩል ለመግታት ከአሜሪካ የደህንነት አካላት ጋር የተጠናከረ እርምጃ ለመውሰድ፣ ሜክሲኮ በብኩሏ የስደተኞችንና የአደንዛዥ እጽን ሽግግር ለመግታት በሁለቱ ሃገራት ድንበር ላይ 10 ሺሕ ሠራዊት ለማስፈር ተስማምታለች ።

 ጀስቲን ትሩዶ የካናዳ ጠ/ሚ
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሩዶ ከትራምፕ የቀረጥ ውሳኔ በኋላ መግለጫ ሲሰጡፎቶ ከማኅደር ጀስቲን ትሩዶ የካናዳ ጠ/ሚምስል IMAGO/ZUMA Press

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሰሜን አሜሪካዎቹ ጎረቤቶቻቸው ጋ ለጊዜውም ቢሆን ፍጥጫውን ረገብ ማድረግ ቢችሉም፣ ከቻይና ጋር ያለው ውጥረት ግን  አሁንም እንደቀጠለ ነው። የአሜሪካንን ተግባር ያወገዘችው ቻይና ባወጣችው መግለጫ ቅሬታዋን ለዓለም የንግድ ድርጅት ማቅረቧን ጠቁማ፣ ከአሜሪካ በሚገቡት በከሰልና በፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ላይ የ15 በመቶ፣ በድፍድፍ ነዳጅ፣ በግብርና ማሽኖችና በመኪናዎች ላይ ደግሞ የ10 በመቶ ቀረጥ መጣሏን አስታውቃለች።

ዶናልድ ትራምፕ ይሄው የንግድ ፍጥጫ ወደ አውሮፓም ሊሻገር እንደሚችል መዛታቸውን ተከትሎ ዓለም አቀፉ ገበያ የማሽቆልቆል ስጋትን አንጸባርቋል። የኢኮኖሚ ባለሞያው ዶክተር ዮናስ አሜሪካ ካላት ኢኮኖሚ አንጻር የብሪክስ አባል ሃገራትን ጨምሮ፣ ከምዕራቡም ከምሥራቁም ዓለም ጋ የቀረጥ የንግድ እሰጥ አገባዋን ብትቀጥል የበለጠ የሚጎዱት ሌሎቹ ሃገራት እንደሆኑ ገልጸዋል።

ገና ኋይት ሃውስ ከገቡ ጥቂት ቀናት ያስቆጠሩት ዶናልድ ትራምፕ፣ የአሜሪካን ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ የውጪ ግንኙነት፣ ልማትና ሌሎችንም መስኮች እያመሱና እየቀየሩ መሆናቸው፣ ነገስ ምን ያረጉ ይሆን? ብሎ ካማሰብ ባለፈ የተረጋጋና የሰከነ፣ አስቀድሞ ሊተነበይ የሚችል ፖሊሲና አፈጻጸምን ለማየትም ሆነ ለመጠበቅ አለመቻሉ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፈተና እንደሆነ እየተስተዋለ ይመስላል።

አበበ ፈለቀ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ