የትራምፕ እገዳ እና የባህል ተፅዕኖ | ባህል | DW | 03.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የትራምፕ እገዳ እና የባህል ተፅዕኖ

የአሜሪካ የዴሞክራሲ ባህል በሁለት የተለያዩ ሃሳብ ጥጎች ላይ እንደልብ የመወያያት የመቃወም መብት የሚሰጥ ነዉ። አሁን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከተመረጡ በኋላ የሚታየዉ የተቃዉሞ ሰልፍ አዲስ ነዉ። በአሜሪካን ሃገር ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በኋላ እንዲህ አይነት ተቃዉሞ ታይቶ አይታወቅም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 17:19

የዶናልድ ትራምፕ የእገዳ ዉሳኔ

«ለነገሩ የሰዉ ልጅ ባህሪ የሚታወቀዉ መድረክ ላይ ሲወጣ ነዉ። ለምሳሌ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከመመረጣቸዉና ስልጣን ከመያዛቸዉ በፊት ባለኃብት ናቸዉ። ባለኃብቱ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸዉ በፊት ለሴት ያላቸዉ አክብሮትም ሆነ በባህላቸዉ በንግግራቸዉ ስለሚያሳዩት ሥነ-ስርዓት ጉዳይ ያጤነዉና የገመገመዉ ሰዉ አልነበረም። አንድ ሰዉ አገርን ሲያስተዳድር ስርዓት ሊኖር ይገባል ከሚል አንጻር ሲታይ ትራምፕ በኛ አገር አነጋገር ሲገለጽ «ጋጠወጥ » ቢባል ይሻላል። አነጋገራቸዉ ጋጠወጥነት የተላበሰ ሰዉ ናቸዉ።»

በዓለ-ሲመቱ ተፈጽሞ ሙሉ በሙሉ ስልጣኑን ከተረከቡ 15 ቀናት አልደፈኑም፤ በየቀኑ በሚያወጡት ሕጎቻቸዉ ግን ዓለምን ማስደንገጣቸዉን የልዕለ ኃያልዋን ሃገር ነዋሪዎች ደሞ ማሸማቀቃቸዉን ቀጥለዋል፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ። ዛሬ ደሞ ምን ትዕዛዝ ያስተላልፉ ይሆን የዓለም የየዕለት ጥያቄ ሆንዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕን አስመልክቶ በመግቢያዉ ላይ አስተያየትዋን የሰጠችን በዩናይትድስቴትስ መዲና ነዋሪዋ  ጋዜጠኛ ቅድስት ተስፋዬ ናት።  በየእለቱ አጀብ የሚስብሉት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፉት ቀናት ከሰባት የዓለም ሃገራት የሚመጡ ዜጎች ወደ ሃገሪ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አይገቡም የሚል ትዕዛዝን ካስተላለፉ በኋላ የሰዉ ለሰዉ ግንኙነቱ አብሮ መኖሩ  የባህል ልዉዉጡ ሁሉ አጠያያቂ ደረጃ ላይ መሆኑ እየተነገረ ነዉ። ይህ ዝግጅታችን የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የጉዞ እገዳና በሕዝብ መካከል ያለዉን ባህላዊና ፖለቲካዊ ብሎም የሰዉ ለሰዉ ትስስር ላይ የሚያስከትለዉን ተጽኖ ይመለከታል።

 

ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በየእለቱ አዲስ አጨቃጫቂ ነገር ይዘዉ ብቅ ሳይሉ ቀርተዉ አያዉቁም፤ የአሜሪካ ነዋሪም ከበዓለ ሲመታቸዉ የጀመረ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች እየተቃወማቸዉ ሰላማዊ ሰልፍ መዉጣቱን ቀጥሎአል። እራሳቸዉም ቢሆኑ በምረጡኝ ዘመቻ የተናገሩትን ነገር መፈፀም በመጀመራቸዉ በቃሌ የምገኝ ነኝ ሲሉ ነዉ ራሳቸዉን በኩራት የሚገልፁት፤ አንዳንዶች ጤነኛ መሆናቸዉን ሁሉ የሚጠራጠሩ አሉ። ትራንፕ ከቀናቶች በፊት ከሰባት ሃገራት ዜጎች ወደ ዩኤስ አሜሪካ እንዳይገቡ ትዕዛዝ ካስተላለፉ በኋላ እንኳ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጀርመናዉያን የዚህ የዶናልድ ትራምፕ ሕግ ሰለባ መሆናቸዉ ተነግሮ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ እነዚህ ዜጎች ከጀርመን ዜግነት ሌላ ትራምፕ ወደ ዩኤስ አሜሪካ እንዳይገቡ ካገዱባቸዉ ሃገራት የመጡናና ይህንኑ የትዉልድ ሃገራቸዉን የዜግነት መለያ በሁለተኛ መታወቅያነት በመያዛቸዉ ነበር፤ አሁን ግን ሁለት ዜግነት ያላቸዉን የአዉሮጳ ነዋሪዎች አይነካም ተብሎአል። ድሮም ቢሆን እኮ ከአሜሪካዉያን ጋር ይህ ነዉ የሚባል ግንኙነት የለንም ያሉን በዶይቼ ቨለ የአረብኛ ቋንቋ ክፍል ጋዜጠኛና የኢራቅ ጉዳይ ከፍተኛ ተንታኝ ሃሰን ሁሴን እንደተናገሩት፤

«በዚህም አለ በዝያ በኢራቅና በዬናይትድ ስቴትስ መካከል የነበረዉ ባህላዊ ግንኙነት እጅግ ጠባብና የአንድ ወገን ነበር ማለት ይቻላል። አሁን ትራምፕ ባሳለፉት ዉሳኔ ጭልጭል የሚለዉ ግንኙነታችን እስከነጭራሹ አክትሞአል። »

ጋዜጠኛና የኢራቅ ጉዳይ ከፍተኛ ተንታኝ ሃሰን ሁሴን ትራምፕ በዋሽንግተኑ ቤተ-መንግሥት ከሚቀመጡ ይልቅ እዚዉ በተሽቆጠቆጠዉ ሰማይ ጠቀሱ ህንጻቸዉ ቢደበቁ ድህንነታቸዉ የተጠበቀ ይሆናል፤ ሲሉም ነዉ፤ መልክት ያስተላለፉላቸዉ።

« ለትራምፕ ምንም አይነት መልክት ማስተላለፍ የሚቻል አይመስለኝም። እንደሚታወቀዉ ሰዉየዉ 70ዓመታቸዉ ነዉ። በዚህ ዘመናቸዉ ከህይወታቸዉ ምንም ትምህርትን አልቀሰሙም። በ70 ዓመታቸዉ ልነግራቸዉ የምችለዉ ዉዱ ትራንፕ ዋይት ሃዉስ ከምትኖ እዛዉ በነበርክበት በሰማይ ጠቀሱ ብልጭልጩ ፎቅ ቤትህ ምትቀመጥ ደህንነትህ የተጠበቀ ይሆናል»  ከማለት ሌላ ምንም ልመክራቸዉ አልችልም። በጣም የሚያሳዝነዉ ይህ ሰዉ አሜሪካዉያንን መምራቱ ነዉ።» 

ቱጃሩ ዶናልድ ትራምፕ  ማን አለብኝነታቸዉ የስልጣን መንበሩን ከተቆናጠጡ በኋላ ብስዋል ያለን በዩናይትድ ስቴትስ ሲኖር ሦስት አስርተ ዓመታትን ያስቆጠረዉ ታዋቂዉ ገጣሚ ኢሳያስ ልሳኑ ፕሬዚዳንቱ ሰዉኛ ነገር የላቸዉም ሲል ይገልፃቸዋል።

« አዎ፤ በመጀመርያ በአሜሪካ ታሪክ እንዲህ አይነት ነገር ሲከሰት የመጀመርያዉ ይመስለኛል። በአነጋገር ደረጃ ፀያፍ የሆነ መስመር የለቀቀ በሴቶች ላይ ያላቸዉ ንቀትና የጋጠወጥነት ባህሪ በሰዉ ስብዕና ዉስጥ ሊገለጽ የሚችል አይደለም። ቀደም ሲል ከሚስታቸዉ ዉጭ ሞክረዋል የተባሉ ቀደምት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ድምፅ አጥተዉ የተወገዙበት ሃገር ነዉ ያለነዉ፤ ግን አሁን ፕሬዚደንት ሆነዉ የተመረጡት በአነጋገራቸዉ እኔ ከማቀዉና ከኖርኩበት ከተማርኩት ከአሜሪካ ባህል በጣም በተቃራኒ የሚቆም ሆኖ ነዉ ያገኘሁት። የፕሬዚዳንቱ ባህሪ ፀያፍ አነጋገር ብቻ ሳይሆን በድርጊትም የሚገለጽ ሆንዋል። እኔ ብቻ ነኝ፤ እኔ ትክክል ነኝ ከኔ ዉጭም መሰማት የለበትም፤ እኔ ያልኩት ካልሆነ እኔ ነኝ አሸናፊዉ የሚል ስሜት ጭምር ነዉ ያላቸዉ፤ ትንሽ እንኳ ትሁት የመሆን ዝንባሌ የላቸዉም።»

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራንም የማን አለብኝነት ባህሪ እንዲህ ይገናል ብሎ የጠበቀ አልነበረም ስትል የምትገልፀዉ በዝያዉ በዋሽንግተን አካባቢ ነዋሪ የሆነችዉ ጋዜጠኛ ቅድስት ተስፋዬ በበኩልዋ በተለይ በዲሲና አካባቢዋ የተለያየ የዓለም ሃገር ዜጎች እንደሚኖሩ ነግራናለች። አሜሪካ ዉስጥ የሚኖሩት የሜክሲኮ ተወላጆችም ቢሆኑ እጅግ ብጡ ናቸዉ።    

« ማንም ሰዉ ይህ ይመጣል ብሎ የጠበቀ አልነበረም። እዚህ እኛ በምንኖርበት በዋሽንግተንና አካባቢዋ ያለዉ ኅብረተሰብና በሌላ አካባቢ የሚኖረዉ ኅብረተሰብ አንድ ላይሆን ይችላል። እዚህ አካባቢ የሚኖረዉ ሰዉ ግን ከሌላ ዜጋ ጋር ተዋህዶ መኖርን ለምዶታል።  በተለይ ደግሞ በአሜሪካን ሃገር በጣም ብዙ የሜክሲኮ ዜጎች ይኖራሉ። እናም ይህ አይነቱ ዉሳኔ ሲተላለፍ የሚያስፈራዉ ዉጭ ለሚኖረዉ ማኅበረሰብ ወይም ሃገራት ብቻ ሳይሆን እዚሁ ሃገር ዉስጥ ከሚኖሩት ዜጎች ጋር ያለዉ ሁኔታ ጭምርም ነዉ። ዉሳኔዉ ልጆችን ከሌሎች ልጆች ጋር እንዳታጫዉች ሊያደርግ ይችላል። በተለይ በልጆች ላይ የሚፈጥረዉ ነገር በጣም ከባድ ነዉ ያስፈራል። በዚህ አጋጣሚ በሰባት ሃገራት ላይ የጉዞ እገዳ ተጣለ ተባለ እንጂ ፕሪዚዳንት ትራምፕ በዚህ ብቻ ይገታሉ የሚል ግምት የለኝም» 

በሥነ-ግጥሞቹ የሚታወቀዉና በዝያዉ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ሲኖር ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ያስቆጠረዉ ሳምሶን ደምሴ ተፈራ በበኩሉ የአሜሪካ ዴሞክራሲ ፈተና ላይ መዉደቁን ይናገራአል።

«የአሜሪካ የዴሞክራሲ ባህል በሁለት የተለያዩ ሃሳብ ጥጎች ላይ እንደልብ የመወያያት የመቃወም መብት የሚሰጥ ነዉ። አሁን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከተመረጡ በኋላ የሚታየዉ የተቃዉሞ ሰልፍ አዲስ ነዉ። በአሜሪካን ሃገር ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በኋላ እንዲህ አይነት ተቃዉሞ ታይቶ አይታወቅም። ሰሞኑን በሚወጡት ህጎች ላይ በጣም ጠንከር ያሉ ተቃዉሞዎች እየታዩ ነዉና ፤ ይህን ግን አቻችሎ ወደ መሃል ማምጣት የሚችል ሃሳቦች ያስፈልጋሉ። አሁን በአገሪቱ የሚታየዉ ሁለት የተካረረ ፅንፍ የያዘ አካል ነዉ ። ይህን ለመፍታት የብዙኃን መገናኛዎች፤ ፖለቲከኞችም ኃላፊነት አለባቸዉ። አሁን የአሜሪካ ዴሞክራሲ ፈተና ዉስጥ ይመስለኛል። ይህን ፈተና እንዴት አድርጎ እንደሚያልፍና እንደሚወጣዉ አብረን የምናየዉ ይሆናል። »

እንዲህ አይነቱ ባህሪና አቋም በሦስተኛዉ ዓለም አይደለም ዘመናዊ ከሚባሉት ከፕሬዚዳንቱ ይቅርና  ከአንድ ተራ ሰዉ የማይጠበቅ ነዉ። ትራምፕ የሚናገሩት ባህሉም ሆነ የፖለቲካዉ አቅጣጫ የሚያመራዉ ወዴት እንደሆነ አይታወቅም ሲል የሚጠይቀዉ ጋዜጠኛ ኢሳያስ ልሳኑ በመቀጠል፤

«ልዕለ ኃያል በምንላት ሃገር  ዉስጥ ተቀምጠን እንዲህ ያለ ነገር መስማታችን የሚያሳዝንም ነዉ የሚያስገርምም ነዉ። ነገሩ ወዴት አቅጣጫዉ እንደሚሄድ መገመት ያዳግታል ባይ ነኝ። በኢትዮጵያ ባህል ሲታይ ደግም ጨርሶ አይገናኝም። እዚህ በምናዉቀዉ በዘመነዉ ሃገር እንኳ ተቀባይነት የሌለዉ አካሄድ ነዉ ፕሬዚዳንቱ ያላቸዉ»

ፕሬዚደንት ትራምፕ በተደጋጋሚ «አሜሪካ ትቅደም» ሲሊ ተደምጠዋል። ምናልባት ይህ አንባገነንነት አያያዛቸዉ ከሌላዉ አህጉር ተጋብቶባቸዉ ይሆን? ገጣሚ ኢሳያስ ልሳኑ ጥርጣሪ አለዉ፤

«እኔ እንደዉ ይቅርታ ይደረግልኝና እሳቸዉ ብቻ ሳይሆን አንዳንዱ ነገር የተጠና ይመስለኛ። በተለይ ከዚህ ከነጭ የበላይነት ስሜት ከአዉሮጳዉያኑ መምጣት ጋር በየድብቁ በየጓዳዉ ይደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎች አክራሪ ነጭ ጽንፈኞች የሚያደርጉት በጎርጎረሳዊ 2024 ዓ,ም የነጭ ቁጥር አናሳ ይሆናል ስለተባለ ያንን ከአሁኑ መያዝ አለብን የሚሉት ክፍሎች መከተል አለባቸዉ ትሬዚዳንቱ የሚሉትን ርምጃ እየወሰዱ ነዉ ያሉት።  እሳቸዉ የሚወስዱዋቸዉ ርምጃዎች እንደዉ በጋጠወጥነት ይታያሉ በአነጋገራቸዉ ብልግና የተነሳ ትኩረታቸዉ ወደዛ አመዘነ እንጂ አሁን በስራ አስፈጻሚዉ አማካኝነት የሚወስዱዋቸዉ ርምጃዎች የተጠኑና ምናልባትም አሻግሮ ለሚያዩ አሜሪካንን ንጹህ አዉሮጳዉያን ያለበት ሃላቃዉ ኅብረተሰብ ነጭ የሆነበትን ኅብረተሰብ ከመገንባትና ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ነዉ ብዬ አምናለሁ። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነዉ የስደተኞችን ህግ ማዉጣት ነዉ፤ ሁለተኛ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን ማግለል ነዉ፤ በተገን ጠያቂዎች ላይ አሁን የወጣዉ ፖሊሲም በቀጣይነት አሜሪካዉስጥ የሚገቡትን የሌላ ሃገር ዜጎች ፤ ማለት ነጮች ከነጮች ዉጭም የሚቆጣጠሩበት መስክ ነዉ። እና በቀላል መታየት የለበትም የተጠናና ስራዬ ብሎ እየተካሄደ ያለ ጉዳይ ነዉ። ግን እዚህ ላይ ይሳካላቸዋል ማለት አይደለም።……. በእኛ በኩል ግን ትግላችንም ሆነ ፀሎታችን እንዳይሳካላቸዉ ነዉ»

ዓለም እየተቀየረ የሰዉ ስዉነቱ ሥነ-ምግባር እየጠፋ በሚለዉ ሃሳብ ጋዜጠኛ ቅድስት ተስፋዬ ትስማማለች። 

የመናዊዉ የዶይቸ ቬለ ጋዜጠኛ አሊ በበኩሉ በዚያም አለ በዚህ ፕሬዚደንት ትራምፕ ለመታወቅ ብለዉ እባኮ የተሳሳተ ፖለቲካ አያራምዱ ሲል መልክቱን አስተላልፎአል።

« አቶ ትራምፕ እባኮ ታዋቂ የሚሆኑበትን መንገድ ብቻ አያስቡ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችንም በወንጀለኝነት በጅምላ አይጠርጥሩ፤ ሃይማኖትንም በወንጀል ጥርጣሪ ዉስጥ አይክተቱ ነ። የእርሶ ጠላት አንድ ሃይማኖት አልያም አንድ ኅብረተሰብ ሳይሆን ጠላትዎ በሙስሊሙ ዓለም እየመሩት ያለዉ ጦርነት ነዉ። ዩኤስ አሜሪካ በዚያ አካባቢ የያዘችዉን የተሳሳተ የፖለቲካ አቋም በመቀየር ፤ አንባገነኖችን ለማባረር ርዳታዋን መለገሷን መቀጠል  ይኖርባታል»

 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ 

 

 

 

    

  

Audios and videos on the topic