የትራምፕ መዘዝ | ዓለም | DW | 14.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የትራምፕ መዘዝ

የኢራኑ ፕሬዝደንት ሐሰን ሩሐኒ እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ ያሻቸዉን የሚያደርጉት «አንዳድ» ያሏቸዉ የአካባቢዉ መንግስታት ሥለሚተባበሯቸዉ በማለት ሪያዶችን ባሽሙር ሸንቁጠዋቸዋል።አሜሪካማ፤ ሮሐኒ አክለዉ እንዳሉት ድሮም ሐቀኛ አደራዳሪ አልነበረችም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:58

የኔታንያሁ አፀፋ ለፍልስጤሞች ትዕዛዝ፤ ለሌሎቹ «ከኛ ሌላ ላሳር» ስላቅ ነዉ።

የኢስላማዊ ትብብር ድርጅት (OIC በእንግሊዝኛ ምፃሩ) ጉባኤ ምሥራቃዊ እየሩሳሌም የፍልስጤም መንግሥት ርዕሠ-ከተማ መሆንዋን በይፋ እዉቅና ሰጠ።ኢስታንቡል ቱርክ ዉስጥ ትናንት ለአስቸኳያ ጉባኤ የተሰበሰቡት የ57ቱ የድርጅቱ አባል ሐገራት መሪዎች እና ተወካዮች ሌሎች መንግሥታትም ምሥራቃዊ እየሩሳሌም የፍልስጤም ርዕሠ-ከተማነቷን እዉቅና እንዲሰጡ ጠይቀዋል።የመሪዎቹ ጉባኤ የተጠራዉ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ መላዋ እየሩሳሌም በእስራኤል ርዕሠ-ከተማነት ዕዉቅና መስጠታቸዉን በመቃወም ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

 

ነጋዴዉ ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ ሰሞኑን አንዴ ሴቶችን አለፍላጎታቸዉ ተዳርተዋል፤ለማማገጥ ሞክረዋል-ደግሞም ለፕሬዝደትነት የበቁት በሩሲያ የስለላ ድጋፍ ነዉ የሚለዉን ጥርጣሬ እና ወቀሳ ለማስተባበል እየባተሉ ነዉ።ባለፈዉ ሳምንት ሮብ ከዋሽግተን የረጩት አዋጅ የቀሰቀሰዉ ቁጣ እና ተቃዉሞ ግን እንደ ቋያ እሳት ከሐገር-ሐገር እያዳራሰ፤ሐገራቸዉን እና እስራኤልን ከብዙዎች እየነጠለ ነዉ።

ትራምፕ አወዛጋቢዋን እየሩሳሌምን የእስራኤል ርዕሠ-ከተማነት ዕዉቅና የሰጡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ዉሳኔ ጥሰዉ፤ አረቦች ለሰባ ዓመታት የተሟገቱ፤ መቶሺ ወገኖቻቸዉን የገበሩለትን ፍላጎት፤ ምክንያት ዕቅድ ደፍልቀዉ መሆኑ አላከራከረም።

ዉሳኔዉን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስከ አዉሮጳ ሕብረት፤ ከዓረብ ሊግ እስከ አፍሪቃ ሕብረት የዓለም ማሕበራት እና

መንግስታት መቃወማቸዉም ሐቅ ነዉ።ጠንካራዉ ተቃዉሞ የተሰማዉ ግን የዓረቡን ዓለም እንመራለን ከሚሉት ከሪያድ ነገስታት አይደለም።ከካይሮ አምባገነኖችም አይደለም።ከቱርክ እንጂ።ከብዙዎቹ የዓረብ መንግሥታት ይበልጥ ከዋሽግተንም ከቴል አቪቭም ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላት ቱርክ እንደ ሐገር የትራምፕን ዉሳኔ አወገዘች።እንደ የኢስላማዊ ትብብር ድርጅት (OIC) ሊቀመንበርነቷ ድርጅቱ ዉሳኔዉን በጋራ እንዲያወግዝ አስቸኳይ ጉባኤ ጠራች።ጉባኤዉ ምሥራቃዊ እየሩሳሌም በኃይል የተያዘች ግን የፍልስጤም ዋና ከተማ ናት ብሎ ወሰነ።ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶሐን ለእስራኤልም አልተመለሱ።

                               

«እስራል (የሌሎችን ግዛት) በኃይል የያዘች መንግሥት ናት።እስራኤል አሸባሪ መንግሥትም ናት።እየሩሳሌምን እንደ ፍልስጤም ርዕሠ-ከተማነት እዉቅና ያልሰጡ ሐገራት አሁን እዉቅና መስጠት አለባቸዉ።ዛሬ ምሥራቃዊ እየሩሳሌም የፍልስጤም ርዕሠ-ከተማ መሆኑን እናዉጃለን።»

ዩናይትድ ስቴትስ የእስራኤል ጥብቅ ወዳጅ፤ የፍልስጤም መሪዎች ደጓሚ፤ የሁለቱ አደራዳሪም ነች።ከእንግዲሕ ግን፤ የፍልስጤሙ ፕሬዝደንት ማሕሙድ አባስ ትናንት እንዳሉት አሜሪካ አትታመንም።

                                

«ዩናይትድ ስቴትስ ከእንግዲሕ እዉነተኛ የሠላም አደራዳሪ አይደለችም።እንደ ፍልስጤም፤ እንደ አረብ እንደ ሙስሊምም፤ ዩናይትድ ስቴትስን በሰላም አደራዳሪነት አንቀበልም።ምክንያቱም ለሠላም አደራዳሪነት መሠረታዊዉ መመዘኛ ሐቀኝነት እና ምክንያታዊነት ነዉ።»

የኢራኑ ፕሬዝደንት ሐሰን ሩሐኒ እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ ያሻቸዉን የሚያደርጉት «አንዳድ» ያሏቸዉ የአካባቢዉ መንግስታት ሥለሚተባበሯቸዉ በማለት ሪያዶችን ባሽሙር ሸንቁጠዋቸዋል።አሜሪካማ፤ ሮሐኒ አክለዉ እንዳሉት ድሮም ሐቀኛ አደራዳሪ አልነበረችም።

                                      

«ዩናይትድ ስቴትስ

ሐቀኛ ሸምጋይ ሆና አታዉቅም።የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር በቅርቡ የወሰደዉ እርምጃም፤ የፍልስጤሞችን ጉዳይ ለመፍታት አሜሪካ ቀና ሚና እንድትጫዎት ለሚመኙ ሰዎች በግልፅ አሳይቷል።ዩናይትድ ስቴትስ የፅዮናዉያንን ፍላጎት ለማሳካት ብቻ መቆምዋንና ለፍልስጤም ፍትሐዊ ጥያቄ ደንታ እንደሌላት የሚያረጋግጥ ነዉ።»

የትራምፕን ዉሳኔ አዉሮጶች እንዲቀበሉ ለማግባባት ፓሪስ እና ብራስልስን የጎበኙት የእስኤል ጠቅላይ ሚንስትር የቤንያሚን ኔታንያሁ አፀፋ ለፍልስጤሞች ትዕዛዝ፤ ለሌሎቹ «ከኛ ሌላ ላሳር» ዓይነት ስላቅ ነዉ።

                                   

«እየሩሳሌምን በተመለከተ ፍልስጤሞች እዉነቱን ተቀብለዉ ለሰላም መሥራት እንጂ ለፅንፈኝነት እና ሌላ ሐቅ ለመቀበል መጣር የላባቸዉም።እየሩሳሌም የእስራኤል ርዕሠ-ከተማ ብቻ ሳትሆን የሁሉም ኃይማኖቶችን የማምለክ ነፃነትን የምናስከብር እኛ ብቻ ነን።በመካከለኛዉ ምሥራቅ ማንም የማያስከብረዉን ነፃነት የምናስከብር እኛ ብቻ ነን።ሌሎቹ በሚያሳፍር ሁኔታ ይሕን ማድረግ አቅቷቸዋል።ለዚሕም ነዉ ይሕ ሁሉ መግለጫ እኛን የማያጓጓዉ።በስተመጨረሻዉ እዉነቱ ይፀናል፤ እና እነሱም እንደሌሎቹ ሁሉ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነቷን ተቀብለዉ ኤምባሴያቸዉን ያዞራሉ።»

57 አባል ሐገራትን የሚያስተናብረዉ የኢስላማዊ ትብብር ድርጅት (OIC) የተመሠረተዉ የሙስሊሞቹ ሰወስተኛ ቅዱስ ሥፍራ፤ የእየሩሳሌሙ አል-አቅሳ መስጊድ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1969 በእሳት መጋየቱን በመቃወም ነበር።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic