የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆልና የአፍሪቃ ኅብረት ሐውልቶች | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 07.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆልና የአፍሪቃ ኅብረት ሐውልቶች

የአፍሪቃ ኅብረት ለአጼ ኃይለ ሥላሴ ልክ እንደ የቀድሞ የጋና መሪ የፓን አፍሪቃ አቀንቃኝ ሐውልት እንዲቆምላቸው መወሰኑ ብዙዎችን አነጋግሯል። ሐውልቱ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚንሥትር መለስ ዜናዊም እንዲሠራ መወሰኑ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር አጀንዳ ኾኗል። በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆሉን የተመለከተው ዘገባ አነጋጋሪ ኾኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:23

የአፍሪቃ ኅብረት ሐውልቶች

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆልን የሚመለከት ዘገባ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ኾኗል። የአፍሪቃ ኅብረት ለኢትዮጵያ ንጉሥ ለአጼ ኃይለ ሥላሴ ልክ እንደ የቀድሞ የጋና መሪ የፓን አፍሪቃ አቀንቃኝ ሐውልት እንዲቆምላቸው መወሰኑ ብዙዎችን አነጋግሯል። ሐውልቱ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚንሥትር መለስ ዜናዊም እንዲሠራ መወሰኑ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር አጀንዳ ኾኗል። 

 

አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪቃ ኅብረት ቅጽር ግቢ ከእንግዲህ የጋናው የቀድሞ ፕሬዚዳንት የክዋሜ ንክሩማህ ሐውልት ብቻውን አይቆምም። የአፍሪቃ ኅብረት የያኔው የአፍሪቃ አንድነት አባት የሚባሉት ኢትዮጵያዊው ዓፄ ኃይለሥላሴም ሐውልት እንዲቆም ወስኗል።  ከሁለቱ የፓን አፍሪቃ አቀንቃኞች በተጨማሪ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሐውልትም በቅጽር ግቢው እንዲቆም ተወስኗል። የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኗል። የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት እያሽቆለቆለ መሆኑን የሚገልጥ ዘገባ ሌላው የሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ዐብይ ርእስ ነበር።የአፍሪቃ ኅብረት የዛሬ አምስት ዓመት ግድም ለጋናው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ያስቀረጸውን ሐውልት አዲስ አበባ በሚገኘው ቅጽር ግቢው አስመርቆ ይፋ ሲያደርግ በብዙዎች ዘንድ ቅሬታ አስነስቶ ነበር። ቅሬታው የጋናው ድኅረ-ቅኝ ግዛት የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ለምን ሐውልት ተሠራላቸው በሚል አልነበረም። 
ሐውልቱ የዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን አንድ ሰሞን ለማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ሥላቅ እንደዳረገው ምሥል ግራ በተጋባ ቀራጺ ተቀረጸ ተብሎም አይደለም። የብዙዎች ቅሬታ ለአፍሪቃ ኅብረት መመሥረት እና መቆም ዋነኛ ባለውለታ ተደርገው የሚጠቀሱት የኢትዮጵያው የመጨረሻ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመዲናቸው በአዲስ አበባ የመዘንጋታቸው ነገር ነበር። 

ይኽን የታዘበው ዘካሪያስ ዘላለም በትዊተር ገጹ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲህ ብሏል። «የአፍሪቃ የዲፕሎማሲ ኃይል እንዲዋሃድ ማን ሚና እንደተጫወተ በግልጽ እንናገር ከተባለ ያ ለኃይለሥላሴ በደንብ ይገባቸዋል» ብሏል። ዛካሪያስ ንጉሡ የመጀመሪያውን የወሎ ረሀብ ችላ ያሉ አምባገነን መሪ እንደነበሩ በማከል፤ ሆኖም ለአፍሪቃ ኅብረት የጣሉት መሠረት ግን ዕውቅና ተነፍጎት ሊታለፍ እንደማይችል ያስረግጣል። 

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች የዓፄ ኃይለሥላሴን የአፍሪቃ አንድነት ተጋድሎ ወደጎን በመግፋት፤ ሀገሪቱ በጣሊያን ፋሺስት ጦር ስትወረር ጥለው ኮብልለዋል፤ ለራሳቸው ዝናም ሲበዛ ለፍተዋል ሲሉ ኮንነዋል። ብዙዎች ግን በተመሳሳይ ሐውልቱ ለንጉሡ መታሰቢያ መሠራቱ ይገባዋል የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል። 


ዳሩ ቤስት በትዊተር ገጹ በእንግሊዝኛ ባሰፈረው ጽሑፍ ዓጼ ኃይለሥላሴ ለአፍሪቃ አንድነት የነበራቸውን ታታሪነት ገልጧል። «ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪቃ መሪዎችን እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰአት በማነጋገር ካዛብላንካ ምናምን እያሉ ለሦስት መከፋፈላቸውን እንዲያቆሙ አሳምነዋቸዋል» ሲል ጽፏል። የዛሬ አምስት ዓመት የጋናው ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ሀውልት እንዲቆም በማድረግ የኃይለ ሥላሴን ሆን ብሎ እንዲዘለል አድርጓል ሲልም የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን ኮንኗል። 

የአፍሪቃ ኅብረት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊውም በቅጽር ግቢው ሐውልት ለማቆም መወሰኑ በርካቶችን በተቃራኒ ጎራ አሰልፎ አከራክሯል። ምናልባት ከፌስ ቡክ የመረጥናቸው ተከታዮቹ አስተያየቶች የተቃርኖ ሐሳቡን የሚያጎሉ ይመስላሉ። «መለስ ዜናዌ ምን ቤት ነው በአፍሪካ ህብረት ሀውልት የሚቆምለት?» ሲል ይንደረደራል ሰማኸኝ ጋሹ አበበ በፌስ ቡክ ገጹ። «እንደምገምተው ህወሀት ለኃይለ ሥላሴ ሀውልት የምታቆሙ ከሆነ ለመለስም ካላቆማችሁ አንፈቅድም በማለቱ መሆን አለበት።ትንሽ ቆሎ ይዘህ ካሻሮ ተጠጋ ነው ነገሩ። የሚለው ሰማኽኝ «የጥላቻ ፖለቲካ መሀንዲስ» ሲል የገለጻቸው የመለስ ዜናዊን ሀውልት ለፓን አፍሪካኒዝም እድገት ከፍተኛ ተጋድሎ ካደረጉት ከአፄ ከኃይለ ሥላሴና ከክዋሜ ንክሩማ ጐን ቆሞ ማየት ያበሳጫል» ሲልም ውሳኔውን በጽኑ ተቃውሞዋል። 

አዲሱ ቸኮል በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ፦ «ለመለስና ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሀውልት እንዲሠራ መወሰኑን ተከትሎ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ አንድም ተቃውሞ አላየሁም፤ የመለስ ላይ ግን አይቻለሁ» ሲል ይንደረደራል። «ችግሩ ለመለስ ሀውልት እንዲሠራ የተወሰነው የአፍሪቃ ኅብረት አዲስ አበባ እንዲቆይ አድርጓል መባሉ ነው፡፡ ሀውልት እንዲሠራለት መነሻ የሆነው ግን እሱ አይደለም» ሲልም ምክንያቶቹን ያብራራል አዲሱ።  

«መለስ አፍሪቃ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪቃ ኅብረት በሚቀየርበት ሂደት ትልቅ ሚና ነበረው» በማለት ይቀጥላል አዲሱ፤ ትልቅ ያለውን ሚና ግን በጽሑፉ አልጠቀሰም። «ቀጥሎ የአፍሪቃ አጀንዳ በነበረው ኔፓድም ፊታውራሪ ነበር። በአየር ንብረት ለውጥ እና የፀረ-ድህነት ዓለም አቀፍ ዘመቻዎች ከማንም በላይ የአፍሪቃ ድምፅ ሆኖ አገልግሏል። በዘመናችን አፍሪቃን በተመለከተ በዓለም አቀፍ መድረኮች የመለስን ያህል የታገለ/የተደራደረ የለም። እውነቱ ይሄ ነው» ብሏል አዲሱ። 
በአንድ ወቅት አቶ መለስ በተለይ የዓለም የሙቀት መጠን መጨመርን አስመልክቶ በነበረው ድርድር አፍሪቃን የሚጎዳ ስምምነት ፈጽመዋል፤ ለበለጸጉት ሃገራት የሚጠቅም ውሳኔንም ተቀብለዋል በሚል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የትችት ርእስ ሆኖ ነበር። 

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆልን አስመልክቶ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ለንባብ ያበቃው ጽሑፍ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የብዙዎች መነጋገሪያ መሆን የቻለ ሌላኛው ርእስ ነበር። «የትምህርት ጥራቱ በአስደንጋጭ ሁኔታ አሽቆልቁሏል ተባለ» በሚል ርእስ ነው የቀረበው ጽሑፍ። «የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ማንበብና መፃፍም ሆነ ሂሳብ ማስላት አይችሉም የኮሌጅ ተመራቂዎች የ8ኛ ክፍል ፈተናን በብቃት ማለፍ አልቻሉም» እያለ ይቀጥላል ጽሑፉ። «የአገሪቱ የትምህርት ጥራት ከዓለም አቀፉ መስፈርት እጅግ ያነሰ ደረጃ ላይ» እንደሚገኝ ያተተው ዘገባ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካቶች በቀጥታ አስተያየት እንዲሰነዝሩ አድርጓል። «መንግሥት ቁጥር ላይ እንጂ ጥራት ላይ አይሠራም፤ ትውልዱ በትምህርት ቢደኸይ ቁብ አይሰጠውም» የሚሉ አስተያየቶች ጎላ ብለው ወጥተዋል። 

ይኽው ርእስ በዶይቸ ቬለ የፌስቡክ ገጽ ላይ ለውይይት ቀርቦ ነበር። በርካታ የጽሑፍ እና የድምፅ አስተያየቶች ደርሰውናል። 
«በጥራት ጉዳይ ብሔረዊ ውርደት ላይ ነን» ይላል ዓቢይ ግርማ የተባለ የዶይቸ ቬለ የፌስቡክ ተከታታይ፡፡ ዓቢይ ይኽን ያስባለውን ምክንያት ሲገልጥም እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ «ለምሳሌ በዚህ ሥርዓት ተምሮ ሥራ ላይ ያለ አንድ ባልደረባዬ እኝህ መሪ ማናቸው ?ብዬ ብጠይቀው ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ናቸው አለኝ» ሲልም ጽሑፉን ከምስል ጋር አያይዞ አቅርቧል። ምስሉ ላይ ዓጼ ቴዎድሮስ ከነጉንጉናቸው ጦር እና ጋሻ ይዘው እንደተኮሳተሩ ይታያል። 

መምህር እንደሆነ የገለጠልን ሌላኛው የፌስቡክ ተከታታያችን ሥዩም ኦሎንጄ ደግሞ የትምህርት ጥራቱ ማሽቆልቆልን አስመልክቶ ሲናገር የተቆጣ ይመስላል፦ «ስለዚህ ምን ይጠበስ!» በማለት ይጀምራል መምህር ሥዩም። 

መምህሩ ለሞያው ክብር በማይሰጥበት ማኅበረሰብ ውስጥ እየኖረ «ስለ ትምህርት ጥራት ማውራት ከንቱ ነገር» እንደሆነም ይናገራል። ሥዩም የትምህርት ጥራቱ እንዲሻሻል መፍትኄ ያላቸውን ነጥቦች አስፍሯል። «በመጀመሪያ የመምህሩ ማንነት መለኪያ የሆነው የኢኮኖሚ ደረጃው መሻሻል እለበት። ሲቀጥል የፖለቲካ ጫና ወይም በካድሬ መመራት ሁኔታ መቅረት አለበት ምክንያቱም የሚቀርቡ ሪፖርቶች ሐቀኝነት የጎደላቸው ናቸው። በመቀጥል አሁን ያለው የአስተዳደር ሁኔታ መምህሩን አያገባህም የአንተ ሀላፍነት መመራት እንጁ መምራት አይደለም የሚል ይመስላል» ሲል የመፍትኄ ሐሳቦቹን ዘርዝሯል። ከዚያም ባሻገር  መምህሩ ሊደመጥ  እና «ተማሪውን የሚቀርፅበት ሙሉ ኃላፊነት» ሊሰጠው እንደሚገባ በመግለጥ ሐሳቡን ያጠቃልላል።

በአጭር መልእክት መቀበያ ስልክ ቁጥራችን ከኢትዮጵያ የደረሰን መልእክት እንዲህ ይነበባል።  «ሠላም ዶይቸ ቬሌዎች የኢትዮጵያ ትምህርት በገደል ላይ ፈረስ መጋለብ እንደ ማለት ነው። ዮኒ ከመርሳ ሰሜን ወሉ» የዩናይትድ ስቴትሱ አድማጫችን የላከልን የአጭር መልእክት ደግሞ፦ «:ሆን ተብሎ አገርንና ትውልድን ለመግደል የሚደረግ የአሻጥር አካል መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል» ሲል ይንደረደራል። «አብዛኛው መምህር ከመደበኛ ሥራው ይልቅ በፕሮፖጋንዳና በጆሮ ጠቢነት ተመድቦ» የሚሠራ ነው ሲልም ያጠቃልላል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች