1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትምህርት ማስረጃ መጭበርበር በደቡብ ክልል

ረቡዕ፣ ግንቦት 30 2015

የደቡብ ክልል የህዝብ አስተዳደር እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ‘’ በክልሉ የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች መበራከትና የሠራተኞች ህገ ወጥ ቅጥርና ዝውውር ፈተና ሆኖብኛል ‘’ እያለ ነው ፡፡ ቢሮው የ2015 ዓም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ትናንት በገመገመበት ወቅትም ጉዳዩ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ነው የዋለው ፡፡

https://p.dw.com/p/4SIWA
Äthiopien Wegene Markos
ምስል South Region Public Service and Human Resource Development Office

በደቡብ ክልል ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መስፋፋት አነጋጋሪ ሆኗል

የትምህርት ማስረጃ መጭበርበር በደቡብ

የደቡብ ክልል የህዝብ አስተዳደር እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ‘’ በክልሉ የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች መበራከትና የሠራተኞች ህገ ወጥ ቅጥርና ዝውውር ፈተና ሆኖብኛል ‘’ አለ ፡፡ ቢሮው የ2015 ዓም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ከትናንት በስትያ ሰኞ በገመገመበት ወቅት  ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ነው የዋለው ፡፡

በክልሉ በስፋት የሚታየውን ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ለመለየት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሠፊ ምርመራ መደረጉን የጠቀሱት የክልሉ የህዝብ አስተዳደር እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘይኔ ቢልካ በሂደቱም ቢሯቸው ደረሰበት ያሉትን  ግኝት ይፋ አድርገዋል፡፡ በክልሉ ከ17ሺ በላይ በሚሆኑ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ በተደረገ ማጣራት 1 ሺህ 131 የትምህርት ማስረጃዎች ሀሰተኛ ሆነው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በተጨማሪ በህገ ወጥ ቅጥር ፣ ዝውውር እና የደረጃ እድገት ላይ ተመሳሳይ ማጭበርበር የፈጸሙ መገኘታቸውን የጠቀሱት አቶ ዘይኔ “ በ5 ሺህ 672 የብቃት ማረጋገጫ ላይ በተደረገ ፍተሻ 767 የብቃት ማረጋገጫዎች ሀሰተኛ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ እንዲሁም በ23ሺ መዝገቦች ላይ በተደረገ ፍተሻ ከ4ሺ በላይ የቅጥር፣ የዝውውር እና የደረጃ እድገት በህገ ወጥ መልኩ መፈጸማቸው ተረጋግጧል “ ብለዋል ።

በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃና በህገ ወጥ ቅጥርና ዝውውር ተግባር ከተሳተፉት መካከል በአመራር ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች እንደሚገኙበት የጠቀሱት አቶ ዘይኔ ቢሮው በተገኙ ማስረጃዎች መሠረት አስተዳደራዊ እርምጃና የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያሰፍንም ተናግረዋል፡፡

ዶቼ ቬለ በትምህርት ማስረጃ ማጭበርበር ዙሪያ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ወገኔ ማርቆስ “ ሁኔታው ማህበረቡን  ወደ ውድቀት ሊወስድ የሚችል ነው “  ብለዋል ፡፡ አሁን ላይ የትምህርት ማስረጃ እንደሸቀጥ ከሱቅ የሚገዛ ሆኗል ያሉት ዶክተር ወገኔ “ ይህም እንደአገር ህዝብን የሚጎዳ ፤ መጪው ትውልድም በዕውቀት ፣ በችሎታና በፈጠራ ላይ ያለውን እምነት ሊሸረሽረው የሚችል ነው “ ብለዋል ፡፡

የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃ መስፋፋትን ለመቀነስ የተመራቂዎችን የትምህርት  ማስረጃዎች ማንም አይቶ ሊያረጋግጥ በሚችልበት በአንድ ማዕከል በተዋቀረ ድህረ መረብ አውታር ሊሰባሰብ እንደሚገባ የጠቆሙት ዶክተር ወገኔ በትምህርት ማጭበርበር ተግባር ላይ የተገኙ ግለሰቦችንም አስተማሪ የህግ ቅጣት መጣል እንደሚገባ ተናግረዋል ፡፡

የደቡብ ክልል የህዝብ አገልግሎት እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ጨምሮ  በዘመድ እዝማድና በጎሳ  በመሳሳብ  ተከናውነዋል ባላቸው የቅጥር መዛግብቶች ላይ በየጊዜው  ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል ፡፡ ቢሮው ባለፈው የ2014 ዓም ብቻ በ32 ሺህ መዝገቦች ላይ ባደረገው ምርመራ ተመሳሳይ ችግሮች  ታይቶባቸዋል ባላቸው 5ሺህ በሚጠጉ የትምህርት ማስረጃዎችንና የቅጥር መዛግብቶችን ውድቅ ማድረጉን የሚታወስ ነው ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ታምራት ዲንሳ 

ነጋሽ መሐመድ

ፎቶ ፡ ከደቡብ ክልል የሕዝብ አገልግሎት እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የተወሰደ