የቴሌኮም አጠቃቀም ህግና CPJ | ኢትዮጵያ | DW | 22.06.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የቴሌኮም አጠቃቀም ህግና CPJ

ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተዉ CPJ የኢትዮጵያ መንግስት በግለሰብ የቴሌኮም አጠቃቀምን አስመልክቶ ያወጣዉ አዋጅ የጋዜጠኞችን ተግባር ችግር ላይ የሚጥል ነዉ ሲል ስጋቱን ገለፀ። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪቃ አማካሪ ቶም ሮድስ

default

 የህጉ ዝርዝር እና አፈፃፀሙ ግልፅ እንዳልሆነ ቢገልፁም የግለሰቦች ኢንተርኔትን ተጠቅሞ የድምፅ ግንኙነት ማድረግን  ሁሉ የሚያሳስብ እንደሆነ ነዉ ያመለከቱት።

በኢንተርኔት የቴሌኮሙኒኬሽንን አገልግሎት መጠቀም እስከ 15ዓመት በሚደርስ እስር እንደሚያስቀጣ የሚገልፅ ህግ መዉጣቱ ነዉ ሰሞኑን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተዘገበዉ። አብዛኞቹ እንደዉም ለይተዉ ስካይፕ የተሰኘዉን እና በኢንተርኔት በድምፅ መነጋገርን የሚፈቅደዉ ስልት መታገዱ ነዉ ሲገልፁ የታየዉ። CPJ እንደዘረዘረዉ 99 በመቶ በገዢዉ ፓርቲ የተያዘዉ ምክር ቤት በቴሌኮም ላይ ይደረጋል የሚባለዉን ማጭበርበር ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚል ያሳለፈዉ ህግ ማንኛዉንም ዓይነት የቴሌኮሙኒኬሽን መስመር ወይም መሳሪያን አሸባሪ መልዕክት ለማስተላለፍ መጠቀም ወይም እንዲተላለፍበት ምክንያት ማድረግ በአከራካሪዉ ፀረሽብር ህግ በእስራትና በገንዘብ ሊያስቀጣ ይችላል።

NO FLASH Microsoft und Skype

ከዚህም ሌላ ህጉ የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች ወደአገር ዉስጥ የማስገባት፤ የመሸጥና በንብረትነት የመያዝን ስልጣን ለመረጃና ኬሙኒኬሽን ቴክኒዎሎጂ ሚኒስቴር መስጠቱንም ድርጅቱ በመግለጫዉ ጠቅሷል። CPJ ግልፅ ባልሆኑ አገላለፆች የተሞላ ነዉ የሚለዉ ይህ ህግ ጋዜጠኞች መረጃ ለመፈለግ በሚያደርጉት ጥረት ለክስ ሊዳርጋቸዉ ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል። የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪቃ አማካሪ ቶም ሮድስ ስለህጉ ሲናገሩ፤

«ይህ የቆየ ህግን ዳግም የማደስ ዓይነት አቀራረብ ነዉ፤ ህጉ በኢንተርኔት የቴሌኮሙኒኬሽን ግንኙነትን ያግዳል። በርካታ ሀገር ዉስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች እንደነገሩኝ አብዛኞቹ የዚህ ዓይነት አገልግሎቶች ታግደዋል፤ በይፋ ግን አይደለም።» 

በግል ኮምፒዩተር የሚደረጉ የኢንተርኔት የድምፅ ግንኙነቶችን እንደማያግድ በዘገባቸዉ የጠቀሱ የተለያዩ መገናኝ ብዙሃን ይልቁንም ይህ ህግ ትኩረቱ፤ በኢንተርኔትን አማካኝነት ለንግድ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን መጠቀምን የሚመለከት እንደሆነ ይገልፃሉ። እንደነዚህ ወገኖች አገላለፅ ህጉ የግለሰብን የግል የኢንተርኔት የድምፅ ግንኙነት የማይነካበት ሁኔታ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ የግለሰቦች Skype እና መሰል የቀጥታ የኢንተርኔት የድምፅ ግንኙነቶችን ህጉ እንደማይፈቅድ የገለፁ ዘገባዎች ወጥተዋል። ቶም ሮድስ የጉዳዩ አደናጋሪነት እዚህ ላይ ነዉ ይላሉ፤

«አዎ ያነዉ አንዱ ክርክር፤ በርግጥ መንግስት ህጉን መከለካከል ያመጣቸዉ ሁለቱ መከራከሪያዎች አንቺ በትክክል እንዳልሺዉ ነዉ። በመሠረቱ እንዲህ ያለዉ ግንኙነት ከተገቢዉ ገደብ በላይ ከሆነ የመንግስትን ቴሌኮም ገቢ መሻማቱ አይቀርም። ምክንያቱም ሰዎች ለአገልግሎቱ አይከፍሉምና። እናም በግሌ የግለሰብ አጠቃቀምን አይመለከትም የሚለዉን መከራከሪያዉ በግልፅ አልተረዳሁትም ምክንያቱም ይህ የግለሰብ አጠቃቀም ነዉ ዉሎ አድሮ ንግዱን የሚጎዳዉ። እናም እኔ የግል አጠቃቀምን ሊያግድ የተቀረፀ መሆኑን ነዉ የማምነዉ፤ ይህን መከራከሪያ የሚፃረር ነገርም አላየሁም።»

ሀገር ዉስጥ ካሉ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ስላገኙት መረጃ ሮድስ ሲያስረዱ ደግሞ ይህን ብለዋል፤

«እርግጥ ነዉ እዚያ የሚገኙ አንዳንድ ጋዜጠኞችን አነጋግሬያለሁ፤ አንዳንዶቹ አዲስ አበባ ናቸዉ ሌሎቹ ደግሞ ስደት ላይ ይገኛሉ። በመሠረቱ በጣም ሰግተዋል፤ ምክንያቱም በበርካታ ሰበቦች በኢንተርኔት የቀጥታ ግንኙነት መገንገያዎች ላይ እጅግ የተመረኮዙ ናቸዉና። አንደኛዉ ከዋጋ አንፃር ወጪ ይቆጥባል፤ ምክንያቱም ምስራቅ አፍሪቃና የአፍሪቃዉ ቀንድ ሀገሮች መካከል ስልክ ለመደወል በጣም ዉድ ነዉ፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከእነዚህ ስልቶች በአንዱ ብትጠቀሚ ደህንነቱ በጣም አስተማማኝ ነዉ፤ ግለሶቦች ግንኙነቱን ለመጥለፍም ያዳግታቸዋል፤ እናም በዚህ ምክንያት እኔ ያነጋገርኳቸዉ በርካታ ጋዜጠኞች እንዲህ ያለዉ ይፋዊ እገዳ የመገናኛ መንገዶችን እጅግ ስለሚያጠባቸዉ በጣም ተደናግጠዋል።»     

ህጉ ሊያስከትል ይችላል ስላሉት ተፅዕኖ ደግሞ ሲናገሩ፤

«ለመናገር ያስቸግራል፤ ማለቴ ያን ህግ ተግባራዊ ካደረጉ በኢንተርኔት ካፌዎች የሚደረጉ ግንኙነቶችን ያዉካል በግለሰብ ደረጃም እንዲሁ፤ ህጉ ያለዉን ችግር በግልፅ ለመናገር በዉስጡ የሚጣረስ እዉነታዎች አሉት፤ ያ ደግሞ ለየትኛዉ ድርጊት ምን ዓይነት ቅጣት ሊከተል እንደሚችል ለማወቅ ያዳግታል ለምሳሌ እነዚህ የመገናኛ ስልቶች መጠቀም እና ይህን አገልግሎቶች ለተጠቃሚ ማቅረብ ላያ ያለዉ የእስራት ጊዜ የመደራረብ ሁኔታ ይታይበታል።»  

አያይዘዉም ቶም ሮድስ ዘገባዉን ከመፃፋቸዉ አስቀድሞ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉን የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት አለመሳካቱንም አመልክተዋል። ድርጅታቸዉ ለመረጃ እና ለጋዜጠኞች ነፃነት የሚያደርገዉን ሙግት እንደሚቀጥልበትም ገልፀዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic