የታዳጊ አገሮች የልማት ዕጣና የዓለም ባንክ ዘገባ | ኤኮኖሚ | DW | 21.09.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የታዳጊ አገሮች የልማት ዕጣና የዓለም ባንክ ዘገባ

የዓለም ባንክ ትናንት ዋሺንግተን ላይ ያወጣው የዚህ ዓመት የልማት ዘገባው የድሆች የዕድል እኩልነት መጠናከር ለሕብረተሰብ የኤኮኖሚ ዕድገት መዳበር ወሣኝ መሆኑንም አመልክቷል። የባንኩ የኤኮኖሚ ጠበብት በዚህ አዲስ ስልታዊ ዘገባቸው ያለሙት በታዳጊ አገሮች የፖለቲካ ለውጥ በማስፈለጉ ላይ ብቻ አይደለም። በዓለምአቀፍ ደረጃም የሰውልጅ የዕድል እኩልነት ይበልጥ ሊጠናከር ይገባዋል ባዮች ናቸው። ዘገባው በታዳጊ አገሮች የሚኖረው ድሃ የሕብረተሰብ ክፍል ፍትሃዊ የኑሮ ዕድል ሊያገኝ ይገባዋል የሚለውን ያህል በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ሃብታም መንግሥታትም ዕርዳታ ወይም ድጋፋቸውን ከፍ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ነው።

ይህ ደግሞ ከአሠርተ-ዓመታት በፊት ከተገባው ቃል ዛሬም አቆልቁሎ የሚገኘውን ዓለምአቀፍ የልማት ዕርዳታ ብቻ የሚመለከት አይደለም። የገበዮችን መከፈት፣ የዓለም ንግድንና የሥራ ገበያ ሥርዓቶችን ፍትሃዊ አወቃቀርም ይጠቀልላል። የዓለም ባንኩ የኤኮኖሚ ጠቢብ ፍራንሱዋስ ቡርጊኞን በብሄራዊ ደረጃ የዕድል እኩልነትን በማሳደጉና በአንድ አገር የኤኮኖሚ ሃይል መጠናከር መካከል ትስስር መኖሩን ያምናሉ። አንዱ ካለሌላው ሊታሰብ አይችልም።

የዓለም ባንክ ዘገባ ማዕከላዊ ያደረገው የዕድል እኩልነት የሚል መልዕክት፤ የኤኮኖሚ፣ የትምሕርት፣ የጤና ጥበቃ አገልግሎትና የሥራ ገበያ ጥቅም ተካፋይ መሆንን፤ በአካባቢና በብሄራዊ ደረጃ የፖለቲካ ድርሻ ማግኘትንም ጭምር ይጠቀልላል። ለምን ቢባል በሕብረተሰብ የዕድል እኩልነትና በኤኮኖሚ ዕድገት መካከል ጽኑ ትስስር በመኖሩ ነው።

በዚሁ የተነሣ በመላው ታዳጊ አገሮች የዜጎች እኩል ዕድል ማግኘት ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገው ስልታዊ ትግል አንድ አካል ይሆናል። እኩልነት መስፈን ያለበት ደግሞ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በማቅረቡ ደረጃ ብቻ አይደለም። የተለያየው የሕብረተሰብ ክፍል መሬት፣ ውሃና መዋዕለ-ነዋይ ሊያገኝ መቻል ይኖርበታል።

በዚህ ረገድ በተለይ የባለሥልጣናት የፖለቲካና የኤኮኖሚ ምዝበራ መገታቱ ግድ ነው። አለበለዚያ ይህን መሰሉ ፍትህ-ዓልባነት የሚያስከትለው ብዙ መዘዝ ይኖረዋል። የሕጻናት በአጭር ዕድማ መቀጨት፣ የትምሕርት ዕድል መጓደል፣ ዝቅተኛ ገቢና ሰፊ ሥራ-አጥነት እንደምሳሌ ሊጠቀሱ ይችላሉ። እነዚህ ጎጂ ችግሮች ታዲያ እርስበርሳቸው ሁኔታውን ይበልጥ የሚያባብሱ ናቸው።

በአጠቃላይ የዓለም ባንክ ባለሙያዎች ያለፈውን አሠርተ-ዓመት ዓለምአቀፍ ሂደት አበረታች አድርገው ነው የተመለከቱት። ሆኖም አማካዩ መሻሻል በመጀመሪያ ደረጃ ከእሢያ፤ በተለይም ከቻይናና ከሕንድ ዕድገት ጋር የተሳሰረ መሆኑን ሳያስገነዝቡ አላለፉም። በሌላ በኩል ግን በነዚህም አገሮች ድሃው የሕብረተሰብ ክፍል በዕርምጃው ያለው የተሳትፎ ድርሻ ዝቅተኛ መሆን ሌላው ሃቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተለይ ከሣሃራ በስተደቡብ ያለው የልማት ድቀት ሁኔታውን ሻል አያደርገውም።
ዛሬ ማሕበራዊው የእኩልነት እጦት ይበልጥ ጎልቶ የሚገኘውም በዚሁ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለምና በላቲን አሜሪካ አገሮች ነው። የባንኩን ዓመታዊ የልማት ዘገባ ካረቀቁት ጠበብት አንዱ ማይክ ዋትሰን ሁኔታውን ለመለወጥ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት አስተዋጽኦ የማድረግ ግዴታ አለባቸው ይላሉ።

በዋትሰን አባባል ሃብታም አገሮች የሚያቀርቡት የልማት ዕርዳታ ለእርሻ ዘርፋቸው ከሚሰጡት ድጎማ ሲነጻጸር ሲበዛ ዝቅተኛ ነው። ለምሳሌ አሜሪካ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ አንጻር የምትሰጠው የልማት ዕርዳታ 0.2 በመቶ ብቻ ነው። ይህም የተባበሩት መንግሥታት ዕርዳታውን 0,7 በመቶ ለማድረስ ከዓመታት በፊት ካስቀመጡት ግብ ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል። በአንጻሩ አሜሪካ ለእርሻ ድጎማዋ ከብሄራዊ ምርቷ 0,9 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ታወጣለች።

በዓለም ባንክ አመለካከት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት አገሮች የዓለም ንግድ ሥርዓት የሚለዝብበትን ለውጥ ማፋጠንም ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በታዳጊው ዓለም ምርቶች ላይ የጣሉትን የንግድ መሰናክል ማንሣት፣ መጤ ሠራተኞችን አገር ማስገባትና ድሆቹ አገሮች ኤይድስን፣ ሣምባ-ነቀርሣን፤ ኩፍኝና ሌሎች ተስቦ በሽታዎችን መቋቋም የሚያስችሉ የራሳቸውን ርካሽ መድሃኒቶች ለመሥራት እንዲበቁ መፍቀድም አለባቸው። ይህን ለማድረግ ደግሞ መጪው በፊታችን ታሕሣስ ወር ሆንግኮንግ ላይ የሚካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔ መልካም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል።