የታዳጊው ዓለም የኤኮኖሚ ዕድገት | ኤኮኖሚ | DW | 12.04.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የታዳጊው ዓለም የኤኮኖሚ ዕድገት

በመልማት ላይ የሚገኙ ሃገራት የኤኮኖሚ ዕድገትን በተመለከተ ባለፈው ዓመት ታላቅ ዕርምጃ አድርገዋል። ይህን የሚያመለክተው የዓለም ባንክ ባለፈው አርብ ይፋ ያደረገው የልማት ዕርዳታ ዘገባ ነው።

ግን ይህ ከዓመታት ወዲህ ጎልቶ የታየ ዕድገት በወቅቱ እየናረ ከሚገኘው የነዳጅ ዘይት ዋጋና ከፍተኛ ወለድ አንጻር በዕርምጃው ሊቀጥል ይችላል ወይ? አጠቃላዩ የዓለም ኤኮኖሚ ባለፈው ዓመት በ 3.8 ከመቶ ሲያድግ የታዳጊ አገሮች ዕርምጃ በአንጻሩ 6.6 ከመቶ ከፍ ያለ ነበር። ዓመታዊ ዕድገታቸው በወቅቱ ሁለት በመቶ እንኳ መድረስ ያልቻለው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ይህን ሊያስቡት ቀርቶ ሊያልሙት እንኳ አይችሉም። በመልማት ላይ በሚገኘው ዓለም ባለፈው ዓመት የታየው የዕድገት መጠን ከሰባኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ወዲህ ከፍተኛው መሆኑ ነው።
ያኔ ከ 35 ዓመታት ገደማ በፊት መሆኑ ነው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት በያመቱ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው 0.7 በመቶ የምትሆነዋን ድርሻ ለልማት ዕርዳታ ለማቅረብ ግዴታ ይገባሉ። ሆኖም በዓለምአቀፍ ደረጃ ሲታይ ከዚህ ከተባለው ግብ እስከዛሬ አልተደረሰም። የስካንዲኔቪያን አገሮች የመሳሰሉት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው የገቡትን ቃል ገቢር አድርገው የሚገኙት። ጀርመን በወቅቱ የምታቀርበው የልማት ዕርዳታ በአንጻሩ 0.3 በመቶ ገደማ ቢጠጋ ነው።

ይሁንና በሌላ በኩል ከ 2000 ዓ.ም. ወዲህ በልማት ዕርዳታው ዘርፍ የመሻሻል ሂደት መታየቱ አልቀረም። በዓለም ባንክ ዘገባ መሠረት ባለፈው ዓመት በዓለምአቀፍ ደረጃ የቀረበው መንግሥታዊ የልማት ዕርዳታ 69 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የተጠጋ ነበር። ይህም ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር በ 11 ሚሊያርድ ከፍ ያለ መሆኑ ነው። ዘገባውን ያጠናቀሩት ጄፍሪይ ሉዊስ እንደሚሉት የወቅቱ ዕድገት ከተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ግብ ለመድረስ፤ በተለይም እስከ 2015 ድህነትን በከፊል ለመቀነስ ለተቀመጠው ዕቅድ እንደ አንድ ማበረታቻ ሆኖ ሊታይ ይገባዋል።

“በእኔ ዕምነት ለረጅም ጊዜ ኋላ ቀር ሆኖ ከቆየው የልማት ዕርዳታ አንጻር አሁን የበለጸጉት መንግሥታት ዕርዳታቸውን ማሳደጋቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ብቻ ነው በሚሌኒየሙ ዕቅድ መሠረት በድሆቹ አገሮች ፊት የገቡትን ግዴታ ሊያሟሉ የሚችሉት።”

እርግጥ የዓለም ባንኩ ባልደረባ የልማት ዕርዳታ አቅርቦቱ በዓለም ኤኮኖሚ መዳከም ሳቢያ መሰናክል ሊገጥመው እንደሚችል ሳይገልጹ አላለፉም። በአሜሪካ እያደገ መሄዱን የቀጠለው የበጀት ኪሣራና የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ለምሳሌ ዋነኞቹ አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው። ሆኖም የዓለም ባንኩ የልማት ጉዳይ ባለሙያ በታዳጊ አገሮች የሚታየውን አበረታች ሁኔታ ማጠናከሩን ነው የሚመርጡት። ይህ አበረታች ሁኔታ የሚታየው ደግሞ በእሢያ፣ በተለይም በቻይና፤ ወይም ብራዚልንና ሜክሢኮን በመሳሰሉት የላቲን አሜሪካ አገሮች ብቻ አይደለም። ዕርምጃው የአፍሪቃን ክፍለ-ዓለምም የሚጠቀልል ነው።

በነዚህ አካባቢዎች ባለፈው ዓመት የታየው የኤኮኖሚ ዕድገት በአማካይ 3.8 በመቶ የተጠጋ ነበር። ይህም እርግጥ ከአጠቃላዩ የታዳጊ አገሮች የ 6.6 በመቶ ዕድገት ሲበዛ ያቆለቆለ ነው። ይሁንና አዝማሚያው በአጠቃላይ አርኪ መሆኑን ነው የዓለም ባንኩ ባልደረባ ጄፍሪይ ሉዊስ የሚያስረዱት።

“ዋናው ጥሩ ዜና ታዳጊ አገሮች የዕድገት ጥረታቸውን በሰፊው ማሻሻላቸው ነው። ይህም ብዙ አገሮች ለተሻለ ፖሊሲ መጣር መያዛቸውን ያንጸባርቃል። ውዝግቦች ቀንሰዋል፣ አንዳንድ አገሮች በተሻለ የኤኮኖሚ ሁኔታ ላይ ናቸው። የወሰዷቸው የለውጥ ዕርምጃዎችም የመጀመሪያ ፍሬያቸውን እያሳዩ ነው። የብዙዎቹ አገሮች ዕድገት ከ 5 በመቶ ይበልጣል። እና አሁን ዋናው ነገር ገና ትልቅ ችግር እንደገጠማቸው ያሉትን አገሮች ዕድገት ከፍ ማድረጉ ነው።”

የገንዘብ ዕርዳታውን በተወሰኑ ቅድመ-ግዴታዎች ለምሳሌ ሙስናን በመታገሉና የሰብዓዊ መብት ይዞታን በመሻሻሉ ጉዳይ ላይ ጥገኛ ያደረገው የጀርመን መንግሥትም በተለይ በእሢያ የሚታየው የኤኮኖሚ ዕድገት ለስልታዊ ፖሊሲው ትክክለኛነት ማረጋገጫ እንደሆነ ያምናል። በበርሊኑ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት የዓለም ባንክ ዘርፍ ሃላፊ ዩርገን ሤትለር የድሃ ድሃ የሚባሉት አገሮች ይህንኑ የእሢያ የዕድገት አርአያ እንዲከተሉ ይመክራሉ።

“ይህ ዕርምጃ በአብዛኛው እነዚህ አገሮች ራሳቸው ዕድገትን ለማስፈን የሚከተሉት የኤኮኖሚ ፖሊሲ ውጤት ነው። አሁን ስልታዊ በሆነ መንገድ በተግባር ሊያውሉ የሚችሉትን የውጭ ሃብት በሰፊው ለማከማቸት በቅተዋል። ለዚህም ነው በዓለም የኤኮኖሚ መድረክ ላይ ወሣኝና ጠቃሚ ሃይል ሊሆኑ ችለው የሚገኙት።”

ዩርገን ሤትለር የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ተቋም መለስተኛ ብድር ሊቀርብ የሚችልበትን የልማት ፖሊሲ ለውጥ ማካሄዱም ጠቃሚ እንደሆነ ያስገነዝባሉ። የጀርመን መንግሥት በሚቀጥለው ዓመት የልማት ዕርዳታውን ከ 0.28 ወደ 0.33 በመቶ ከፍ ሊያደርግ ያቅዳል። ይህን ያስታወቁት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል ናቸው። እርግጥ ይህ ከሶሥት-አሠርተ-ዓመታት በፊት ቃል ከተገባው በግማሽ ያነሰ ቢሆንም ጥቂት ዕድገት ማሣየቱ ራሱ የሚጠቅምና የሚያበረታታ ነው።

የአውሮፓ ሕብረት ደግሞ በ 2000 ዓ.ም. ያሰፈነውን የልማት ፖሊሲ ከዚያን ወዲህ ከተለወጠው ዓለምአቀፍ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ለማሻሻል እንዲጥር ከያቅጣጫው የሚሰነዘርለት ጥሪ አይሏል። ያኔ የልማት ፖሊሲው በሰፈነበት ወቅት የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ ግምት ውስጥ አልገባም ነበር። ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ይህን የሕብረቱን ፖሊሲ “በአንድ ዕጅ ሰጥቶ በሌላ ዕጅ መልሶ መንጠቅ” ነው ይሉታል።

እዚህ ቦን ውስጥ በጉዳዩ ተሰብስበው የመከሩ የነዚሁ ድርጅቶች ተጠሪዎችና የጀርመን ተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል እንዳስረዱት የአውሮፓው ሕብረት ፖሊሲ የቆመበት መሠረት ከዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ አይጣጣምም። ስለዚህም የግድ መለወጥ ይኖርበታል። እርግጥ ብዙዎቹ የሕብረቱ የድህነት መታገያ፤ ያልተቋረጠ የኤኮኖሚ፣ የማሕበራዊና የተፈጥሮ ጥበቃ ፖሊሲ ነጥቦች ዛሬም ወቅታዊነት አላቸው። ሆኖም ቪቾሬክ-ሶይል እንደሚያስገነዝቡት በመስከረም 2001 ሽብርተኞች በአሜሪካ ጥቃት ካደረሱና የዓለም ኤኮኖሚ ትስስር “ግሎባላይዜሺን” መፋጠን ከያዘ ወዲህ ጸጥታና የነጻው ንግድ ይዞታዎች ታላቅ ክብደት አግኝተዋል።

“የአውሮፓውን ሕብረት ተግባራት በአዲስ መልክ በማቀናበሩ በኩል የልማት ፖሊሲው ጸጥታን በመሳሰሉ ሌሎች ዓቢይ ጉዳዮች ሥር ወድቆ ክብደቱን እንዳያጣ መጠንቀቅ ይኖርብናል።” ነው ያሉት ቪቾሬክ-ሶይል!

የልማት ተራድኦን በተመለከተ ራሳቸውን የቻሉ የሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች በጀርመንና በብሪታኒያ ብቻ የሚገኙ መሆናቸው ለዚህ ስጋት ጭብጥ ትርጉም የሚሰጥ ነው። በብዙዎች አገሮች ይህ የልማት ተግባር በሌሎች ዘርፎች ሥር የተጠቃለለ ነው። በመሆኑም የልማት ፖሊሲው ወደፊት በሕብረቱ ውስጥ የሚኖረው ሚና ዝቅተኛ እንዳይሆን ማሳሰቡ አልቀረም።

ገና ከአሁኑ አዲሱ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሢዮን ሥራውን ከጀመረ ወዲህ የልማት ዕርዳታው ሃላፊነት በከፊል በውጭ ጉዳይ ኮሜሣሯ በፌሬሮ ቫልድነር ሥር እንዲውል ተደርጎ ነው የሚገኘው። ይህ ደግሞ የጥቅም ውዝግብ እንዳያስከትል በጣሙን ያሰጋል። ጉዳዩ ከሕብረቱ ዓበይት መርሆች አንዱ ቢሆንም ብራስልስ ከተጣጣመ የልማት ፖሊሲ ገና ብዙ ርቃ ነው የምትገኘው።

በጥቂት ወራት ውስጥ ሊወጣ የታቀደው አዲስ መግለጫም ፖሊሲውን ማጠናከሩ ሲበዛ ያጠራጥራል። ለዚህም ምክንያቶች አይታጡም። አንዱን ለመጥቀስ ያህል ሕብረቱ ወደ ምሥራቅ ከተስፋፋ ወዲህ በራሱ የኤኮኖሚ ችግሮች ተወጥሮ ነው የሚገኝው። በተለይ አሥሩ አዳዲስ ዓባል ሃገራት ከራሳቸው ጥቅም አልፈው ከሕብረቱ ውጭ ለሚራመድ የልማት ፖሊሲ መዳበር ማሰባቸው አይጠበቅም። ከዚህ አንጻር በአንድ ዕጅ ሰጥቶ በሌላው መልሶ የመንጠቁ የአሠራር ዘይቤ ባለበት የሚቀጥል ነው የሚመስለው።