የታዳጊው ዓለም የኤኮኖሚ ዕድገት | ኤኮኖሚ | DW | 25.08.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የታዳጊው ዓለም የኤኮኖሚ ዕድገት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከጥቂት ሣምንታት በፊት በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ይዞታና የወደፊት ዕጣ ላይ አውጥቶት በነበረው ዘገባ የወቅቱን ሁኔታ እንግዳ ወይም ያልተለመደ ነገር የሚያደርገው ዕድገቱ በመልማት ላይ በሚገኙ አገሮች መስፋፋቱ መሆኑን አመልክቷል። በመልማት ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ቀጣይ ባሕርይ ይዞ የሚገኘው የምጣኔ-ሐብት ዕድገት በተለያዩ ዓለምአቀፍ ጉባዔዎች ከጸደቁት የልማት ግቦች ለመድረስ በር ከፋች ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጉባዔ በ 2000 ዓ.ም. የተጣለውን የሚሌኒየም ዕቅድም እንደሚጠቀልል የድርጅቱን የግማሽ ዓመት ዘገባ ያረቀቁት የኤኮኖሚ ጠበብት ግምት ነው።
ዕቅዱ በዓለም ላይ የሰፈነውን ድሕነትና ረሃብ በግማሽ መቀነስን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርትን ለሁሉም ማዳረስን፣ የሚሞቱ ሕጻናትን ቁጥር በሶሥት-አራተኛ መጠን መቀነስን፣ የጾታ እኩልነትን ለማስፈን መጣርን፤ እንዲሁም ከዚሁ ባሻገር የኤይድስን፣ የወባንና መሰል ደዌዎችን አዙሪት መግታትን ጭምር ይጠቀልላል። እነዚህ ግቦች ሁሉ ደግሞ እስከ 2015፤ ማለትም በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ዕውን መሆን ይጠበቅባቸዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የታየውን የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት የተለየ የሚያደርገው ካለፉት ዓመታት አንጻር ጠንካራው መሆኑ ብቻ አይደለም። በመልማት ላይ በሚገኙና በሽግግር ላይ ባሉ አገሮች ባልተለመደ ሁኔታ መስፋፋቱ ጭምር ነው። ዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞት ሳለ እንኳ በመልማት ላይ የሚገኙት አገሮች በዚህና በመጪው ዓመት ስድሥት በመቶና ከዚያም የበለጠ ዕድገት እንደሚያሳዩ ነው የሚገመተው።

የተባበሩት መንግሥታት ጠበብት ሰባት በመቶ የዕድገት ነጥብ በማስመዝገብ ከምሥራቅ እሢያ የተስተካከለው የደቡብ እሢያ አካባቢ የያዝነውን ዓመትም በዚሁ መጠን እንደሚዘጋ ይተነብያሉ። ከሣሃራ በስተደቡብ ያለው የአፍሪቃ አካባቢም በተመሳሳስ ጊዜ ከአምሥት በመቶ የበለጠ ዕድገት እንደሚያሣይ ነው የሚጠበቀው። የቀድሞዎቹ ሶቪየት ሬፑብሊኮች ደግሞ በዚህ ዓመት ስድሥት በመቶ፤ በሚቀጥለው ዓመትም ከሰባት በመቶ የበለጠ ዕድገት እንደሚያደርጉ ግምት አለ።

ከሆነ በእርግጥ የወደፊቱን የልማት ተሥፋ የሚያዳብር ነው። ከፍተኛው የምጣኔ-ሐብት ዕድገት በብዙዎች በመልማት ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ የራስን የኤኮኖሚ ፖሊሲዎች ለማሻሻልም እንደሚረዳ ታላቅ ተሥፋ ተጥሎበታል። በወቅቱ ዓለምአቀፉ ንግድ እየተስፋፋ ባለበት ሰዓት አጠቃላዩ ሁኔታ ለታዳጊ አገሮች ያመቸ ሆኖ ነው የሚገኘው።

የኤኮኖሚው ጠበብት እንደሚናገሩት በመልማት ላይ በሚገኙ አገሮች ከፍተኛ ዕድገት እንዲደረግ ለመቻሉ አንዳንድ ውስጣዊ ምክንያቶችም አሉ። ለምሳሌ በቻይናና በሕንድ የተፋጠነውን የኤኮኖሚ ዕርምጃ ተከትሎ የመጣው የገቢ ዕድገትና የድሕነት መቀነስ ከውጭ ንግድ ባሻገር የአገር ገበዮች ፍላጎት እንዲስፋፋ በማድረር ላይ ይገኛል። ይህ በታዳጊ አገሮች መካከል እየጨመረ የመጣውን ንግድ የሚጠቀልል ሂደት አንድ የሁኔታው አዲስ ገጽታ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን በወቅቱ የታዳጊ አገሮች የኤኮኖሚ ይዞታ የሚገኝበትን አበረታች ሁኔታ አድንቀዋል። ቢሆንም የዕድገቱ ሂደት ዕርምጃውን ሊገታ ከሚችል፤ እንበል ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ዋጋና ከወቅቱ ያልተመጣጠነ የዓለም ንግድ ሁኔታ ጋር ከተሳሰረ አደጋ ነጻ አለመሆኑንም ነው አያይዘው የሚናገሩት። ለምሳሌ ያህል ሰባት መቶ ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀውን የአሜሪካ የበጀት ኪሣራ የመሳሰሉ የውጭ ዝቤቶች መስፋት አደገኛ ሆኖ ነው የሚቀጥለው።

ይህ የኤኮኖሚና የምንዛሪ ውጣ-ውረድ ካልተስተካከለ ሁኔታው ዓለምአቀፍ መለዋወጫ በሆነው የአሜሪካ ዶላር ላይ አመኔታን የሚያሳጣ እንደሚሆንም የምጣኔ-ሐብት ጠበብቱ ያስጠነቅቃሉ። አንዳንዶቹ እንዲያውም ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ይህን የበጀት አለመመጣጠን ሁኔታ ለማረቅ ግንባር ቀደም ሚና እንዲኖረው ነው የሚያሳስቡት።

በነዚሁ አስተሳሰብ ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ዕድገቱን ሊገታ የሚችለው አደጋ በመልማት ላይ ከሚገኙት አገሮች ወደ በለጸጉት አገሮች የሚሸጋሸግበትን መንገድ መንደፍ ይኖርበታል። የኤኮኖሚ ጠቢብ ጆዜፍ ስቲግሊትስ እንደሚሉት ታዳጊ አገሮች በበለጸጉት አገሮች የምንዛሪና የወለድ ተመን መዋዠቅ የተነሣ የችግሩ ተሸካሚ መሆን የለባቸውም።

ስቲግሊትስ የጠበብቱ የግማሽ ዓመት ዘገባ በቀረበበት የተባበሩት መንግሥታት የምጣኔ-ሐብትና የማሕበራዊ ጉዳይ ኮሚቴ ስብስባ ላይ ባሰሙት ንግግር በዓለም ኤኮኖሚ ላይ እየጨመረ ለመጣው አለመረጋጋት ተቀዳሚው መፍትሄ የአሜሪካን ፖሊሲ ማረሙ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በእርግጥም የወቅቱ የኤኮኖሚ የዕድገት አዝማሚያ ድህነትን ለመታገል ዓቢይ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ከተፈለገ የሰከኑ ፖሊሲዎች፣ የበለጠ ገንዘብና የጠበቀ ትብብር መስፈኑ ግድ ነው የሚሆነው። አለበለዚያ የዓለም ኤኮኖሚ ትስስር፤ ግሎባላይዜሽን የሚሰጣቸው ጥቅሞች መላውን ሕዝብ፤ በተለይ ደግሞ እጅግ የሚያስፈልገውን ድሃውን ወገን ማዳረሳቸው ዘበት ነው።

አጠቃላዩ በመልማት ላይ የሚገኙ አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት ተሥፋ-ሰጭ አዝማሚያ ይዞ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ዕቅድ በጊዜው ማሟላት መቻሉ አጠያያቂ የሆነው ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል ብቻ ነው። የምግብ ይዞታው እየከፋ መጥቷል፤ የውሃ እጥረትም የተፈጥሮው ጸጋ ሳይጠፋ በወቅቱ ብርቱ የኤኮኖሚ ችግርና የሕልውና ፈተና እየሆነ መሄዱንም ጠበብት እያስገነዘቡ ነው።

የአፍሪቃ አገሮች የሚሌኒየሙን ዕቅድ ጊዜውን ተከትለው ዕውን ማድረግ አለመቻላቸው በመሠረቱ ማንንም ሊያስደንቅ አይገባውም፤ ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆነው ዓለምአቀፍ የምግብ ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት በቅርቡ አውጥቶት በነበረው 60 ገጾችን ያቀፈ ዘገባው እንዳመለከተው። ከሣሃራ በሰደቡብ በምግብ እጥረት የሚሰቃየው ሕዝብ ድርሻ እርግጥ ባለፉት ሰላሣ ዓመታት እምብዛም አልተለወጠም። ከ 30 እስከ 35 በመቶ ድርሻ ይዞ ነው የሚገኘው።

ይሁን እንጂ በሌላ በኩል በሕዝብ ብዛት መናር ሳቢያ የችግረኛው ቁጥር ከ 88 ወደ 200 ሚሊዮን ማደጉ የመከራው መባባስ ዕውነተኛ ገጽታ ነው። አፍሪቃ በተመሳሳይ ጊዜ የምግብ እጥረትን በተሣካ ሁኔታ ለመታገል የቻሉትን የደቡብና ምሥራቅ እሢያ ታዳጊ አገሮች ተከትላ ልትራመድ አልቻለችም።

ለአፍሪቃ ችግሮች መንስዔ የሆኑት ምክንያቶች መሠረታዊ ምንጮች የተዛባ የኤኮኖሚ ፖሊሲና ፍትህ-አልባ የአስተዳደር ዘይቤ፣ ደካማ የእርሻና የውሃ ልማት ይዞታ፣ እንዲሁም ምርምሮችና ልማት ተገቢውን ትኩረት አለማግኘታቸው ናቸው። እርግጥ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጡ በኩል የአየር ሁኔታ፣ ደካማ የሃብት አጠቃቀም፣ ድርቅ፣ ድሕነት፣ በሽታና ሌሎች ማሕበራዊ እክሎችም ፈታኝ ሆነው ነው የሚገኙት።
በአፍሪቃ ከዚሁ ከውስጣዊው ማሕበራዊ ፍትሕና በጎ-አስተዳደር ከጎደለው አገዛዝ ባሻገር ልማትን አንቆ የያዘው ችግር የዕዳው ክምር እየጨመረ መሄድ ነው። ይህ ደግሞ ረሃብና ድሕነትን መታገሉን ሲበዛ ያከብደዋል። ጠቅላላው በአፍሪቃ ላይ ተጭኖ የሚገኘው የውጭ ዕዳ ከአንድ ትሪሊየን ዶላር በላይ እንደሚሆን ነው የሚገመተው።
ከዚህ አንጻር በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ባለፈው የስኮትላንድ ጉባዔያቸው ያደረጉት የአርባ ሚሊያርድ ዶላር የዕዳ ምሕረት እዚህ ግባ ሊባል የሚችል አይሆንም። የመንግሥታቱ ዕርምጃ በተለይ ላተኮረባቸው ከባድ የዕዳ ጭነት ለተከመረባቸው 18 አገሮች ምሕረቱ ጥቂትም ቢሆን ማስታገሻ መሆኑ አያጠያይቅም። እርግጥ ለዕርሻ ልማትና ለምግብ ዋስትና አግባብ ባለው መንገድ በሥራ ላይ ከዋለ!

ግን አጠቃላዩን የአፍሪቃን ችግር ለመፍታት ከዚህ በላይ ሰፊ የሆነ ዕርምጃን ይጠይቃል። በመሆኑም ጉዳዩን የሚከታተሉ ጠበብት በፊታችን መሥከረም ወር የሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የመሪዎች ጉባዔ የአፍሪቃን የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት አዳዲስ የተግባር ዕርምጃዎች እንዲወስዱ ነው የሚያሳስቡት።

በመጀመሪያ ደረጃ የአፍሪቃ አምራቾች በዓለም ገበዮች ላይ ተገቢ ድርሻ እንዲኖራቸው ዓለምአቀፉ የንግድና የታሪፍ ደምቦች መጠገን ይኖርባቸዋል። የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድሮች በዚህ በኩል ተገቢውን ውሣኔ ማስከተላቸው ግድ ነው፤ የበለጸጉት መንግሥታትም የአፍሪቃን ገበሬ የጎዳውን የእርሻ ድጎማቸውን ማቆምና የገበያ መሰናክሎችንም ማንሣት ይጠበቅባቸዋል።

ከዚሁ ሌላ ችግሩን ለመወጣት ከአፍሪቃ መንግሥታት የሚጠበቁ ብዙ የፖሊሲ ለውጦችም አሉ። የመሬት፣ የሰብልና የውሃ ሃብት ይዞታ መሻሻል አንዱ ነው። በአፍሪቃ የምግብ ዋስትና አስተማማኝ ሆኖ እንዲሰፍን ከተፈለገ የእርሻ ልማትን በማስፋፋቱና ምርምርን በማዳበሩ በኩልም ተጨማሪ መዋዕለ-ነዋይ በሥራ ላይ መዋል ይኖርበታል።
ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኙት የአፍሪቃ አገሮች ለምግብ ዋስትና ዓቢይ ድርሻ ያላቸው የሴቶች ማሕበራዊ ይዞታም ትልቅ መሻሻልን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። በመሠረቱ ይህ ሁሉ እስካሁን ያልታወቀ አዲስ ነገር አይደለም። በየጊዜው ተነግሯል-ተዘርዝሯል። ግን ችግሩ በተግባር በመተርጎሙ በኩል የረባ ጭብጥ ዕርምጃ አለመታየቱ ነው።