የታዳሽ የኃይል ምንጮች ተስፋ | ጤና እና አካባቢ | DW | 11.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የታዳሽ የኃይል ምንጮች ተስፋ

ከባቢ አየርን የዓለም የሙቀት መጠንን ከፍ ከሚያደርጉ ሙቀት አማቂ ጋዞች በተለይም ከካርቦን የፀዳ ለማድረግ ታዳሽ የኃይል ምንጭን መጠቀም የሚለዉ ሚዛን የሚደፋ መሆኑ ይታመናል። ሆኖም የሚያስፈልገዉ ወጪና የቴክኒዎሎጂዉ እንደልብ አለመስፋፋት መላዉ ዓለምን የጽዱ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚ ማድረግ የሚለዉን እቅድ አነጋጋሪ አድርጎታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:48

ሙሉ በሙሉ ታዳሽ ኃይል መጠቀም

እቅዱ ኃይል ለማመንጨት በከሰል፤ በነዳጅ ዘይት እና ጋዝ መጠቀም ቀርቶ ሙሉ በሙሉ መላዉ ዓለም ታዳሽ የኃይል ምንጮችን እንዲጠቀም ነዉ የታለመዉ። ይህ ደግሞ እዉን ይሆናል ተብሎ የሚገመተዉ እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር 2050ዓ,ም ድረስ ነዉ። መቀመጫዉን ፓሪስ ላይ ያደረገዉ በግርድፍ ትርጉሙ፤ የ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የታዳሽ ኃይል መርህ ትስስር በአህፅርኦት REN 21 የተገሰኘዉ ተቋም ይህ እቅድ ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል በሚል ከመላዉ የዓለም ክፍል የ114 የኃይል ምንጭ ምሁራንን ትንታኔና አስተያየት በመጠየቅ አሰባስቦ አንድ ዘገባ ባለፈዉ ሳምንት ኒዉዮርክ ላይ አቅርቧል። የተጠየቁት ከ70 በመቶ የሚበልጡት ምሁራን ወደፊት የዛሬ 33ዓመት ላይ የዓለም ኅብረተሰብ ሙሉ በሙሉ ታዳሽ እና ከካርቦን ከፀዳ ምንጭ በተገኘ ኃይል ሊጠቀም ይችላል የሚለዉ እቅድ እዉን መሆን ይችላል ባይ ናቸዉ። በተለይም አዉሮጳ እና አዉስትራሊያ የሚገኙት የዘርፉ ምሁራን የዚህ ሃሳብ ጠንካራ ደጋፊዎች ሆነዉ ነዉ የተገኙት። ሁሉንም የሚያግባባ አንድ ነጥብ ደግሞ፤ በመጪዎቹ ዓመታት ታዳሽ ኃይል የማግኘትም ሆነ የመጠቀም ዝንባሌዉ ከፍ እያለ ይሄዳል የሚለዉ ነዉ። ለዚህም በማሳየትነት ያቀረቡት ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች፤ የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች የመጠቀም ወይም ደግሞ ያንን ራሳቸዉ ገንዘባቸዉን አፍስሰዉ የማምረት ዝንባሌያቸዉ እየጨመረ የመሄዱን አዝማሚያ ነዉ። በሃገራት ደረጃ ይህ የታሰበዉ እዉን ሊሆን የሚችለዉ ግን የፖለቲካ ፈቃደኝነቱ ሲሆን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። የፖለቲካ ፈቃደኝነቱ ሲኖር ተፈላጊነቱ ስለሚጨምርም ታዳሽ የኃይል ምንጭ ለማመንጨት የሚረዳዉ ግብዓት ዋጋዉ በ10 ዓመታት ዉስጥ እየቀነሰ ይሄዳል የሚል ግምታቸዉንም ሰንዝረዋል።

በተቃራኒዉ 17 በመቶ የሚሆኑት የዘርፉ ምሁራን ይህን እዉን ለማድረግ እንደሚያዳግት በመግለጽ የራሳቸዉን መከራከሪያ አቅርበዋል። ። በተለይ ለጃፓን እና ዩናይትድ ስቴትስ ምሁራን ይህ የሚዋጥ እንዳልሆነ ነዉ በጥናቱ የታየዉ። በአቶሚክ የኃይል ምንጭ የምትንቀሳቀሰዉ ጃፓን ስለታዳሽ የኃይል ምንጮች የሚሰማ ጆሮ ያላት አትመስልም። በዩናይትድ ስቴትስም ቢሆን እስከጎርጎሪዮሳዊ 2050ዓ,ም ድረስ የመጓጓዣ ዘርፉን ብቻ ብንመለከት ከጋዝና ነዳጅ ዘይት ተጠቃሚነት የማላቀቁ ጉዳይ አስተማማኝ እንዳልሆነ ነዉ የሚነገረዉ። በሀገሪቱም ቢሆን የተለመደዉ የኃይል ምንጭ ማለትም ከድንጋይ ከሰል እና ከነዳጅ ዘይት የሚገኘዉ ማለት ነዉ፤ ሥርከመስደዱ በተጨማሪ በቅርቡ ስልጣን ላይ የወጡት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቀደመዉ የባራክ ኦባማ አስተዳደር የተወሰኑ መሰል መርሃግብሮችን የማጣጣልና የታገዱትን የመፍቀድ ርምጃ፤ ታይቶ የነበረዉን ጥቂት የተስፋ ጭላንጭል ማደብዘዙ እሙን ነዉ። ጃፓን እና ዩናይትድ ስቴትስ ብቻም አይደሉም ይህ እንዴት እዉን ሊሆን ይቻል በሚል የሚጠይቁት። አፍሪቃና ላቲን አሜሪካዉያን ምሁራንም በ2050 ሙሉ ለሙሉ ታዳሽ ኃይል ዓለም ትጠቀማለች የሚለዉ እቅድ ተግባራዊ ይሆናል የሚለዉ ብዙም እንዳልተዋጠላቸዉ ይፋ አድርገዋል። እነሱ ደግሞ፤ በዉሳኔ ሰጪዎች በኩል የእዉቀት እና የግንዛቤ ጉድለት መኖሩን፤ በዚህም ምክንያት የሚቃረን የኃይል ፖሊሲ መኖሩን፤ በዚያም ላይ ታዳሽ የኃይል ማመንጫዎችን ለመጠቀም፤ ሲበላሹም ለመጠገን የሚያስችል የቴክኒክ ብቃቱ አለመኖሩንም በዝርዝር አንስተዉ ይሞግታሉ።

መገን ፓወር የተሰኘ ስለታዳሽ ኃይል የምክር አገልግሎት የሚሰጠዉ ኢትዮጵያዊ ኩባንያ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ አቶ መልሰዉ ሻንቆ፤ የመንግሥታት የፖለቲካ ፈቃደኝነት እና ቁጥርጠኝነቱ ካለ ተግባራዊ ማድረጉ እንደማይከብድ ነዉ ያስረዱት።

አቶ መልሰዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1985ዓ,ም አንስተዉ በኃይል ምንጭ በተለይም በታዳሽ የኃይል ምንጭ ዘርፍ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ኋላም የራሳቸዉን ኩባንያ አቋቁመዉ ረዥም ዓመታት ሠርተዋል፤ አሁንም እየሠሩ ነዉ። ኢትዮጵያ 90 በመቶ የሚሆነዉ የምትጠቀምበት ኃይል ምንጩ ታዳሽ መሆኑን የሚናገሩት አቶ መልሰዉ ራሳቸዉም የታዳሽ የኃይል ምንጭ አድናቂም ደጋፊም መሆናቸዉን ይናገራሉ። ይህን እዉን ለማድረግ ሃገራት መልማት የሚፈልጉትበትን አቅጣጫ ቆርጠዉ መወሰን ይኖርባቸዋል ነዉ የሚሉት።

በርካታ ሃገራትም ከባቢ አየር ላይ ስለሚደርሰዉ ጉዳት የሚቀርቡ ጥናቶችን በስጋት የሚመለከቷቸዉ ከጀመሩት የልማት እንቅስቃሴ ያጓትተናል ከሚል ስጋት መሆኑ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል። ታዳሽ የኃይል ምንጭ ላይ ማተኮሩ እንደሚበጅ የሚናገሩት ባለሙያዉ አቶ መልሰዉ መንግሥታት ለሚያከናዉኗቸዉ ተግባራት የሚኖራቸዉ ቅደም ተከተል ከራሳቸዉ አልፎ የትዉልድን ህይወት ያገናዘበ ቢሆን እንደበጅ አፅንኦት ይሰጣሉ።

እንደአቶ መልሰዉ ሻንቆ ሁሉ የቻይና እና ሕንድ ምሁራን እቅዱ እዉን ይሆናል የሚል አዎንታዊ አመለካከት ነዉ ያላቸዉ።

ለጥናቱ ሲባል የተጠየቁት የዘርፉ ምሁራን በመላዉ ዓለም በቂ ታዳሽ የኃይል ምንጭ አለ ባዮች ናቸዉ። በተለይ ደግሞ አፍሪቃ ዉስጥ ያለዉ የታዳሽ የኃይል ምንጭ ሥራ ላይ ከሚዉለዉ 200 እጅ ጊዜ እጥፍ እንደሚበልጥ፤ በመካከለኛዉ ምሥራቅ ደግሞ አዉስትራሊያ እና ላቲን አሜሪካ ካለዉ ከ30 እስከ 60 በመቶ ከፍ እንደሚል ነዉ የሚገመተዉ። በሩሲያ፣ ቻይና፣ አዉሮጳ እና ዩናይትድ ስቴትስም ቢሆን ለየአካባቢዉ የሚበቃ የታዳሽ የኃይል ምንጭ መኖሩን ምሁራኑ ይናገራሉ።

ጀርመን በአሁኑ ወቅት 34 በመቶዉ የሚሆነዉን ኃይሏን ከታዳሽ ምንጮች ነዉ የምታገኘዉ። በቴክኒዎሎጂዉ ዘርፍም ቀዳሚ ሀገር መሆኗ ይነገርላታል። ይህም ሆኖ ግን ዛሬም የድንጋይ ከሰል ሰፊዉ የኃይል ምንጩዋ ነዉ። ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥላ ግንባር ቀደሟ ከባቢ አየር በካይ ቻይና በ2014 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በተመዘገበዉ መሠረት 23 በመቶ ደርሳለች። ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ 13 በመቶ ላይ ትገኛለች። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic