የታክሲ ላይ እንጀራ | ባህል | DW | 30.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የታክሲ ላይ እንጀራ

በአዲስ አበባ 11 ሰዎች መጫን የሚችሉ ከ10,000 በላይ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡና በተለምዶ ‘ሚኒ-ባስ’ ተብለው የሚጠሩ መኪናዎች መኖራቸውን በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ይጠቁማሉ።

ሰለሞን ይባላል። አዲስ አበባ ውስጥ ከሜክሲኮ -መካኒሳ በታክሲ ረዳትነት ይሰራል። ዛሬ አብዝቶ የሚማረርበትን ስራ የጀመረው የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኃላ ታክሲ ተራ በሚያዘወትርበት ወቅት ነበር። «ጠዋት ወጥተህ ማታ ነው የምትገባው።የማታ እንኳን ልማር ብትል አትችልም።» የሚለው ሰለሞን ድንገት በጀመረው ስራ የሚያገኘው ገቢ ትምህርቱን ችላ እንዲለው አድርጎታል።

በአዲስ አበባ 11 ሰዎች መጫን የሚችሉ ከ10,000 በላይ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡና በተለምዶ ሚኒ-ባስተብለው የሚጠሩ መኪናዎች መኖራቸውን በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ይጠቁማሉ።የአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት ከ50,000 በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች በተለይ ወጣቶች የስራ እድል ፈጥሯል። ይህ ሾፌሮችን፤ረዳትና የታክሲ ተራ አስከባሪዎችን ይጨምራል። አብዛኞቹ ዝቅተኛ ገቢ ካለው የከተማዋ ነዋሪ የሚመደቡ ናቸው።

አሸናፊ በታክሲ ረዳትነት ለአምስት አመታት ሰርቷል። ከቆሬ ሜክሲኮ ለመጀመሪያ ጊዜ በረዳትነት የሰራው አሸናፊ ከዚህ ውጪ ሌላ የስራ እድል እንዳልነበረው ተናግሯል።

Äthiopien - Taxifahrer in Addis Ababa

ያሬድ ይህን ስራ የጀመረው ከትምህርቱ ጎን ለጎን ነበር።«ውጤት ሳይመጣልኝ ሲቀር የደሃ ልጅ ስለሆንኩ በቀጥታ የረዳትነት ስራ ጀመርኩ» የሚለው ያሬድ ለስድስት አመታት በሰመያዊ እና ነጭ ቀለማቸው ተለይተው በሚታወቁት የአዲስ አበባ ታክሲዎች ላይ አገልግሏል።

የአዲስ አበባ ታክሲ አገልግሎት የከተማዋ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የደም ስር ነው። የአዲስ አበባ ታክሲዎች የማይገቡበት የከተማዋ ጓዳ ጎድጓዳ የለም። የታክሲዎቹ ሾፌሮችና ረዳቶች ከተሳፋሪዎቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት የገንዘብ መልስ አይሰጡም፤የስነ-ምግባር ችግር አለባቸው፤መንገድ እነሱ በሚመቻቸዉ መንገድ ያቆራርጣሉ የሚሉ ወቀሳዎች ይቀርቡባቸዋል። ሰለሞን «ሰው ላንተ ክብር አይሰጥህም። ሃቀኛ እንኳ ብትሆን ለእነሱ አጭበርባሪ ነህ።እቃና ብር አግኝተው የሚመልሱ ስንት የዋሆች አሉ መሰለህ» ሲል ይሞግታል።

የታክሲ ረዳትነት ከፍተኛ ትዕግስት የሚጠይቅ አስቸጋሪ ስራ ነው የሚለው ያሬድ «ተሳፋሪ ሽሮ በርበሬ ሲያልቅበት መጥቶ እሪ የሚለው አንተ ጋ ነው። መብቱንም ተግባራዊ የሚያደርገው ረዳት ላይ ነው።» በማለት የትራንስፖርት ተጠቃሚውን ይተቻል። አሸናፊ በበኩሉ የታክሲ ረዳቶች በስራቸው ከብዙ ሰው ጋር ስለሚገናኙ እና የስራው አሰልቺ በመሆኑ ቶሎ ሊናደዱ እንደሚችሉ ይናገራል።

በዕለት ከዕለት ስራቸው ከነዳጅ ወጪ እና ከታክሲ ባለቤቱ ቋሚ እለታዊ ገቢ የተረፈውን የታክሲ ሾፌር እና ረዳት ይከፋፈላሉ። አሸናፊ እንደሚሰራበት መስመር እና አብሮት እንደሚሰራው ሾፌር ከ80-200 ብር አገኛለሁ ይላል። ይሁንና «ሳምንት ሰርተህ ሶስት ቀን አራት ቀን ስለምታርፍ መልሰህ ወጪ ታደርገዋለህ።» በማለት ገንዘቡ እንደማይበረክት ይናገራል። ሰለሞንም «ሰው እየረገመ ስለሚሰጥህ ነው መሰለኝ ብሩ አይበረክትም»ሲል ገንዘቡ የታክሲ ረዳቶች እጅ ላይ ቆይቶ ለውጥ እንደማያመጣ ይስማማል።

Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU

ለስድስት አመታት በረዳትነት የሰራው ያሬድ ዛሬ ሾፌር ሆኗል። «የእኔ ሾፌር በጣም ጥሩ ሰው ነበር።የሰፈር ልጅ ነበር። እናም ለእኔ ጥሩ አመለካከት ነበረው። ብር ያስቀምጥልኝ ነበር። ከዛ በኃላ መንጃ ፈቃድ አስመዘገበኝና አወጣሁ።» ሲል ያለፈበትን መንገድ ይናገራል።

ያሬድ በአንድ ወቅት በሾፌርነት ሙያው ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች ሄዶ የመስራት ሃሳብ ነበረው። አሁን ትዳር ለመመስረት ዝግጅት ላይ ነው። ከታክሲ ስራው ጎን ለጎን የከባድ መኪና ሾፌር መሆን ይፈልጋል። ስራውን ለመቀየር ዋና ምክንያቱ የሚያገኘው ገቢ በቂ ባለመሆኑ ነው። ያሬድ በታክሲ ረዳትነት ስራ ውስጥ ከገጠሙት ችግሮች አንዱ ሱስ ነበር። «እኔ አሁን ጫት የተወሰነ ጊዜ ሞክሬ አውቃለሁ። ጓደኞችህን ስታይ እንደ ቀልድ ነው የምትገባበት። ጫት እና ሲጋራ በሰፊው የተለመደ ነው። መስበሪያ ይባልና መጠጥ ይጠጣል። 80 በመቶው ቃሚ ነው።»

አሸናፊ የደረቅ ጭነት መኪና ማሽከርከሪያ ፈቃድ ቢኖረውም አሁንም በታክሲ ረዳትነት በመስራት ላይ ይገኛል።በነገራችን ላይ አሸናፊ የቆዳ ልብሶች መስራት የሚያስችለውን ትምህርት አጠናል። ቢሆንም ስራውን ለመጀመር የሚያስችል የገንዘብ አቅም ስለሌለው በሙያው እየሰራ አይደለም። ሰለሞን ዛሬ በሚማረርበት የረዳትነት ስራ ህይወቱን ይግፋ እንጂ የመንጃ ፈቃድ አውጥቶ ሾፌር ለመሆን ዝግጅት ላይ ነው።

ያሬድ «ታክሲና ህጻን ልጅ ሳያጠፋ አይኖርም» የሚለው አባባል አለው። የታክሲ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ ጥፋት ሲፈጽም በቅጣት አሊያም በጉቦ ማለፍ የተለመደ መሆኑን ያሬድ ይናገራል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic