የታህሳስ ወር ሃገራዊ እና ባህላዊ ትርጓሜ | ባህል | DW | 18.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የታህሳስ ወር ሃገራዊ እና ባህላዊ ትርጓሜ

«አርሶ አደሩ እያጉረመረመ ሲለዉ ከረመ፤ አርሶ በሌዉ መጣ ጠላ ሊጠጣ፤ አርሶ በሌዉ ካለ ምን ችግር አለ፤ አርሶ በሌዉ ጎፈር ማረስ መቆፈር፤ ላለዉ መንገዱን አለስልሶ ከርሞ ይመጣል ያልሞተ ሰዉ፤ እመቤቴ ያደረችበቱ እጣን ይሸታል መሬቱ» እያለ ሆ ይላል ያዜማል ፤ የኢትዮጵያ ገበሬ የዘራዉን ሰብል በታህሳስ ሲሰበስብ።


ታህሳስ ወር በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ክንዋኔዎች መካሄዳቸዉንም የለቱ የባህል መድረክ እንግዶቻችን አጫዉተዉናል። መምህር ካሳይ ገብረ ግዚአብሄር ይባላሉ አንዱ የዝግጅታችን ታዳሚ ፤ ካሳይ ገብረ እግዚአብሄር የተለያዩ መጻሕፍትን ለአንባብያን ያቀረቡና በተለይ ሕብረ- ብዕር በተሰኘዉ ተከታታይ መጻህፍቶቻቸዉ ታዋቂነትን አትርፈዋል።

ታህሳስ ወር በሃገራችን በተለይ በደጋዉ አካባቢ የምርት መሰብሰብያ የዉቅያና የጥጋብ ወር መሆኑ ይታወቅለታል፤ ይህን ተከትሎ ደግሞ ታህሳስ የመተጫጫ ፍቅረኛ የማፈላለግያ ወርም ነዉ። በለቱ ዝግጅታችን የታህሳስ ወር ሃገራዊ እና ባህላዊ ትርጓሜዉን የሚያጫዉቱን እንግዶችን ይዘናል።
ታህሳስ ወር በተለምዶ አጠራሩ «ትሳስ» የሚለዉ ቃል የተወሰደዉ ከግዕዝ ሲሆን፤ ሃሰሰ፤ ፈለገ፤ ሻተ፤ መረመረ፤ የሚል ግስ ሲሆን ፍችዉ፤ የፍላጎት የመሻት፤ወይም ደግሞ የመመርመር ወር እንደማለት እንደሆን በዕለቱ ያነጋገርናቸዉ ምሁራን ገልፀዉልናል። ይህ ማለት አዝመራ የሚሰበሰብበት ምርት የሚፈለግበት ወር እንደማለት እንደሆን በግዕዝ መዝገበ ቃላት መጽሐፋቸዉ የሚታወቁት እና የዛሬዉ የባህል መድረክ ሁለተኛ እንግዳ ሊቀ-ኽሩያን በላይ መኮንን ገልፀዉልናል።
በሃገራችን ሰማንያ ከመቶ የሚሆነዉ የሕብረተሰባችን ክፍል የሚተዳደረዉ በግብርና መሆኑን እና ግብርና የሃገራችን ትልቁ የኤኮኖሚ ዋልታ መሆኑን የሚናገሩት ሊቀ ኽሩያን በላይ መኮንን፤ በግብርና ተሰማርቶ የሚኖረዉ የሕብረተሰብ ክፍል ታህሳስ ወርን እንደ አንድ ትልቅ ፀጋ እንደሚቆጥር ገልፀዋል። ስለ ታህሳስ የተነገረ ቃል ግጥም አንዱ ከአባይ ወንዝ ጋር የተያያዘዉ መሆኑን የሚገልጹት ሊቀ ኽሩያን በላይ « አባይ ጉደል ብለዉ አለኝ በትሳስ፤ የማን ልብ ይችላል እስከዝያ ድረስ» የሚለዉ የክረምቱ ወራት፤ ማዕበሉ ዉርጩ ሁሉ አልፎ ታህሳስ ወር ወንዞች በሙሉ ትክክለኛዉን ፍሰታቸዉን የሚይዙበት፤ የወንዝ ዉኃ ጠርቶ የሚገኝበት ወራት በመሆኑና፤ የክረምት ወራት አልፎ ዘመነ መፀዉም እየተገባደደ ያለበት መሆኑን የሚያሳይ ነዉ ሲሉ ገልፀዉልናል።


ታህሳስ ወር በኢትዮጵያ የጥጋብ ወር በመሆኑ ይታወቃል። ገበሪዉ ሰብሉን ሲሰበስብ በታህሳስ ምን አይነት ለየት ያለ ዝግጅት ይኖረዉ ይሆን? በሃገራችን በኢትዮጵያ ታህሳስ ወር የአጨዳ የዉቅያ ወር በመሆኑ ታህሳስ የጥጋብ ወር ነዉ፤ ያሉት መምህር ካሳይ ገብረ ግዚአብሄር፤ በታህሳስ ወር ገበሪዉ እህሉን በበሬ የሚያስኬድበት ወቅት፤ ፈጣሪዉን የሚያመሰግንበት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል። ገበሬዉ በዚህ ወር ሰብሉን ሲወቃ ድግስ ደግሶ ጠላ ተጠምቆ እንዲሁም በአዉድማዉ ዙርያ ጎጆ ወይም ዳስ ብጤ ተጥሎ ነዉ። ይህ ድግስ «አድማስ» ይባላል ሲሉ መምህር ካሳይ ገብረ ግዚአብሄር፤ ገልፀዉልናል። በዉቅያዉ ግዜ በመንገድ የሚያልፈዉ ሰዉ ሁሉ የድግሱ ተካፋይ እንዲሆን ይጋበዛል፤ ተጋባዡ ደግሞ መብላት ግዴታዉ ነዉ ሲሉ ያጫወቱን መምህር ካሳይ ገብረ ግዚአብሄር፤ አለበለዝያ ግን ባለ ድግሱ አድማሴን ይዘህብኝ አትሂድ ሲል ከድግሱ እንዲቋደስ ገበሬዉ ይማፀናል። ይህ ማለቱ ደግሞ በረከቴን አትዉሰድብኝ ለማለት ነዉ ሲሉ አጫዉተዉናል። ተጋባዡ እንግዳ በልቶ ጠጥጦ በረከት ያዉርድ ብሎ መርቆ ይሄዳል። በዉቅያ ግዜም ገበሬዉ ዘንድ ከታህሳስ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሥነ-ቃሎች ይደመጣሉ፤ «በሬ ሆይ፤ በሬ ሆይ፤ አንተ ጌታ ብዙ አትዉረድ ከወንዙ፤ አልቅት ያገኙሃል የሚጎዘጉዙ» « ኧረ በሬ ዓለሙ ይልሃል አዳሙ፤ የተሰራህበት ምንድን ነዉ ቀለሙ፤ ኧረ በሬ ሆይ የጣርከዉ የጋርከዉ የክረምቱ አዝመራዉ እነሆ» « ከድንጋይ ከእንጨት እንድያ ሲንገላታ፤ ካራ ሁኖ ቀረ የበሬ ዉለታ»

Landverpachtung an ausländische Investoren in Äthiopien


ታህሳስን የሚያወድስዉ ምርት አፋሹ ገበሪ ብቻ ሳይሆን፤ የቆሎ ተማሪዉ እረኛዉ ሁሉ መሆኑን መምህር ካሳይ ገብረ ግዚአብሄር ሳይገልፁ አላለፉም። እናም ከመስከረም ይጀምራሉ። በመስከረም አየሁ የለመለም፤ በጥቅምት ተቀናቀንኩት፤ በኅዳር ነሐሴ ወጣች ከዳር፤ በታህሳስ,,,»

የሃገራችን ገበሪዎች አዘማራቸዉን የሚሰበስቡት በተናጠል ሳይሆን በሕብረት ነዉ ያሉት ሊቀ-ኽሩያን በላይ መኮንን በበኩላቸዉ፤ በአጨዳ ወቅት የሚባለዉን ሥነ-ግጥም በጥቂቱ ገልፀዉልናል።« በሬ በሬ ብለዉ ጠምደዉ ካረሱ፤ ይሸታል ጨገዳዉ ስብ እንደጠበሱ፤«ጨገዳ ማለት በመጀመርያ የምትደርስ የበኩር እሸት»፤ እንጀራ አለብለዉ አይነግሩም ለድኃ፤ ተሻግሮ ይሄዳል አርባራትን ዉኃ፤ የበሬዉ እናት የአያዬ እናት ፤ ያዉለዋል ከቤት ያጠጣዋል ሻሚት»
ገበሬዉ በጋዉን አርሶ አለስልሶ በግንቦት በሰኔ ዝናብን ጠብቆ ከወፍ አዕላፍ አብላኝ ብሎ በተስፋ ይዘራል በተስፋ የዘራዉን ከትል ከበረድ ከወፍ ጠብቅልኝ እያለ ፈጣሬዉን እየተማፀነ እየለመነ ቡቃያዉን ይኮተኩታል፤ ያርማል ሲሉ ያጫወቱንን እንግዶች በሚቀጥለዉ ሳምንት በሁለተኛ ክፍል ዝግጅት፤ ገበሬዉ በታህሳስ ወር በአጨዳና በዉቅያ ወቅት የሚያዜማቸዉን ሥነ-ቃሎች በሰፊዉ ይዘዉልን ይቀርባሉ።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic