የታህሳስ ወር ሃገራዊና ባህላዊ ትርጓሜ ክፍል ሁለት | ባህል | DW | 25.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የታህሳስ ወር ሃገራዊና ባህላዊ ትርጓሜ ክፍል ሁለት

መፀዉ ወይም መኽር ወር፤ ከመስከረም ሃያ ስድስት እስከ ታህሳስ ሃያ አምስት ይዘልቃል፤ ከታህሳስ ሃያ ስድስት ደግሞ በጋ ይጀምርና እስከ መጋቢት ሃያ አምስት ይዘልቃል። በዚህም ኢትዮጵያዉያን የገና በዓልን የሚያከብሩት ታህሳስ መጨረሻ በበጋ ወርራት ዉስጥ ነዉ።

የታህሳስ ወር ሃገራዊ እና ባህላዊ ትርጓሜ በሚል ርዕስ በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በገበሬዉ ዘንድ ስለሚከናወኑ ተግባራትና ስለሚነገሩ ስነ- ቃሎች ባለፈዉ ሳምንት ባቀረብነዉ የመጀመርያ ክፍል ዝግጅት መምህር ካሳይ ገብረ እግዚአብሄርና፤ ሊቀ-ኽሩያን በላይ መኮንን፤ ሰፊ ማብራርያ እንደሰጡን ይታወሳል። በዕለቱ ዝግጅታችን በመፀዉ ወይም መኸር ወቅት በተለይም በኢትዮጵያ ሰብል በሚሰበሰበት በታህሳስ ወር በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የገበሬዉን ህይወት የሚያስቃኙንን ሥነ-ቃሎችና ወጎች እናያለን።

Landverpachtung an ausländische Investoren in Äthiopienቅዱስ ያሬድ ባወጣዉ የጊዜ አቆጣጠር ሰሌዳ መሰረት መፀዉ ወይም መኽር ወር፤ ከመስከረም ሃያ ስድስት እስከ ታህሳስ ሃያ አምስት ይዘልቃል፤ ከታህሳስ ሃያ ስድስት ደግሞ በጋ ይጀምርና እስከ መጋቢት ሃያ አምስት ይዘልቃል፣ በመቀጠል ከመጋቢት ሃያ ስድስት እስከ ሰኔ ሃያ አምስት ፀደይ ይሆናል። የክረምት ወራት ደግሞ ከሰኔ ሃያ ስድስት እስከ መስከረም ሃያ አምስት ይዘልቃል፤ በዚህም ኢትዮጵያዉያን የገና በዓልን የሚያከብሩት ታህሳስ ወር በጋ ዉስጥ ነዉ ያሉን መምህር ካሳይ ገብረ ግዚአብሄር፤ ታህሳስ ወር ለኢትዮጵያዉያን ታሪካዊ ክንዉኖች የተካሄዱበት የተከበረ ወርም ነዉ ሲሉ ገልፀዋል። ለምሳሌ ይላሉ መምህር ካሳይ በመቀጠል፤ ታህሳስ ሶስት እመቤታችን ቤተ- መቅደስ የገባችበት ዕለት ማለትም ባህታ የምንለዉ ይከበራል። ሌላዉ ታህሳስ ሶስት አፄ ምኒሊክ ያረፉበት ቀን ነዉ። ታህሳስ አምስት የታህሳስ ግርግር ብለን የምንጠራዉ መንግሥቱ ንዋይና ግርማሜ ንዋይ በአፄ ኃይለስላሴ ላይ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ያደረጉበት ዕለትም ነዉ። ሌላዉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ- ክርስትያን ታላቅ መምህር የነበሩት መምህር ክፍሌ የጣልያንን አገዛዝ በመቃወማቸዉ ጣልያን እንደገባ ታህሳስ ሰባት 1928 ዓ,ም ረሽንዋቸዋል፤ ይህ ቀን በኢትዮጳያ ታሪካዊ ቀን ተብሎ ይዘከራል፤ ይታወሳል። በ 1943 ዓ,ም ታህሳስ አስር ቀን የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ 71 ተማሪዎችን ይዞ የማስተማር መማር ሂደት የጀመረበት ዕለትም ነዉ፤ ግን ይህን ቀን ዩንቨርስቲዉ ለምን አስቦት እንደማይወል በዉል ባይታወቅም ቀኑ በታሪክነት ተመዝግቦአል ሲሉ መምህር ካሳይ በታህሳስ ወር ባሉት እያንዳንዱ ቀናት የተመዘገቡትን ታሪኮች እስከ ታህሳስ ሰላሳ ንጉስ ሄሮድስ 144 ሺህ ህጻናት የፈጀበት ቀን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቀኑን የምትዘክርበት መሆኑን በዝርዝር አጫዉተዉናል።

"ታህሳስ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፣ እጠብቅሀለሁ አንተ ልጅ ቶሎ ና፡፡

ይወዘውዘኛል አልጠላኝም ገና፣ ፍቅር ሞገደኛው እየነሳኝ ጤና፡፡

ምግብ አያስበላ አያስለብስ ልብስ፣ ሞገደኛው ፍቅሩ ይዞኝ በታህሳስ፡፡በማለዳ ጀንበር በገና ጨረቃ፣ እኔን እኔን ብላ መጣች ተደብቃ፡፡"

በግዕዝ አማርኛ ተከታታይ መዝገበ ቃላታቸዉ የሚታወቁት ሊቀ-ኽሩያን በላይ መኮንን በበኩላቸዉ በታህሳስ ጎበዙ ገበሬ ይገጠምለታል፤ ሰነፉ ገበሬም ይገጠምበታል ሲሉ ይገልፃሉ። «የወይፈኑ ቄስ የበሬዉ መምህር፤ አቆላለፈዉ ክምር በክምር» ሲባል ገበሬዉ ይወደሳል። በዚሁ አንፃር ለገበሬዉ የሚቀርቡ ቃል ግጥሞች አሉ፤ « ተላላዉ ገበሬ ይዉላል ከጥላ ዉርጭ የመሰለ ብር ከመሬት ሲፈላ» «ወገቡ ከረረ ወደ ኋላ ቀረ ማጭዱን ንጠቁት ሚስቱ ትጨድበት፤ አንድ ግዜ ሳቁበት» እየተባለ ሰነፉን ገበሬ ለማትጋት ይህንን አይነቱን ሥነ- ቃል ይገጠቀሙበታል ሲሉ ሊቀ-ኽሩያን በላይ መኮንን አጫዉተዉናል።

በታህሳስ የቆሎ ተማሪና ጉንዳን ስንቅ የሚሰበስቡበት ወርም ነዉ ይባል የሚሉን መምህር ካሳይ ገብረ ግዚአብሄር በበኩላቸዉ ስለ ጉንዳን በታህሳስ ወር ቃርሞ አጫዉተዉናል።

ሊቀ-ኽሩያን በላይ መኮንን በገበሬዉ ዘንድ የሚነገሩ ሥነ - ቃሎች መካከል አሉ በመቀጠል ፤ የጠንካራዉን ገበሬ ምርት የጠንካራዉን ገበሬ ነዶ የሚጎትት ሰነፍ ገበሬም አለ። ታድያ እሱን ለመገሰፅ ሰነፉ ገበሬ እንዲህ ይገጠምበታል፤ « ማምረት ነዉ እንጂ ወገብን ታጥቆ ማጨድ ነዉ እንጂ ወገብን ታጥቆ፤ ዉሻ ይመስል ምንድነዉ ሰርቆ» « እንጨድ ጎበዝ ሳያልፍ መኸሩ፤ ጥሬ አይገኝም መንደር ቢዞሩ» « በማጨዴ ስለት በሚስቴ ትጋት አጨዳዬን በወቅቱ ጨረስኳት» ሲል ገበሬዉ ሚስቱንም ያመሰግናል፤ ምክንያቱም ሚስት በአጨዳ ግዜ ጥሩ ጠላ ጠምቃ፤ ጥሩ ንፍሮ ቀቅላ በማቅረብ በአጨዳ ግዜ የደቦ ስራ ላይ እያበላች እያጠጣች አጨዳዉ በጥሩና በፍጥነት እንዲካሄድ ትረዳለች ሲሉ ገልፀዋል ። « ሄደ ነጎደ ሄደ ነደደ፤ ማጭዱ እንደሳት እየነደደ፤ የቆመዉን እንጨት እየጎመደ» ሲል ገበሬዉ እያዜመ አጨዳዉን በጥንካሪ ይተገብራል። « ተዋጋ ብሎ ቢሰጠዉ ጋሻ ለሚስቱ ሰጣት ኩበት ማፈሻ» በአገራችን ማሕበረሰብ በተለይ በአርሶ አደሩ ዘንድ ለስራ መቀስቀሻ ማነቃቅያ «ሰንጎ መገን» የግጥም አይነት ዝቅም ላይ ይዉላል ሲሉ ሊቀ-ኽሩያን በላይ መኮንን በዝርዝር አስረድተዋል።የሰዉ ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቱን ካሟላ በኋላ እንደሚሆነዉ ሁሉ፤ ገበሬዉም ሰብሉን ሰብስቦ ጎተራዉን ከሞላና ጥጋብ ከሆነ በኋላ ትዳር ያልያዘዉ ጎልማሳዉ ገበሬ ጎኑ የምትሆን የምትረዳዉ የሚያፈቅራት ሚስትም የሚፈልገዉ የሚጨዉ በታህሳስ ወር ነዉ። ገበሬዉ ትዳር እንዲይዝ የሚያሳስበዉ ደግሞ አዝመራዉ ታጭዶ ተሰብስቦ ተወቅቶ ጎተራ በመግባቱ፤ ለድግስም የሚሆን በኢ እህልም ስላለዉ ነዉ። ታድያ በልደት« በገና» በጥምቀት ቆንጆዋ ተኳኩላ አምራ፤ ሳዱላዋን አሳምራ፤ ጋሜዋን አበጥራ፤ ወደ ክብረ በዓሉ ስትወጣ ጎረምሳዉም እዚሁ በዓል ላይ ያገኛታል ይተቻጫሉም ሲሉ የገጠሩን በተለይ ደግሞ የአርሶ አደሩን ህይወት አመላክተዋል።

Landschaft in Äthiopien Flash-Galerieበሰብል ስብሰባ ወቅት ገበሬዉ ብቻ ሳይሆን በሬዉም በሥነ-ቃል ዉዳሴ ይቀርብለታል፤ ያሉ ሊቀ-ኽሩያን በላይ መኮንን በመቀጠል፤« በርዬ ሽሩሩ በሬ ወዳጅ ማሩ የበሬ ቀላሽ የወንድም ታናሽ እንኳን በሰላሳ አይገኝም በሽ» «በርዬ ሽሩሩ ላብላህ ከዳርዳሩ ላጠጣህ ከባህሩ በአንተ ላይ ነዉና የሚገኘዉ ሁሉ» እየተባለ በሬዉ ይወደሳል። « በሬና ገበሬ ቢጣሉም አይበጅ እንደዉ ሰተት ብሎ ይጠመዳል እንጂ»

ሊቀ-ኽሩያን በላይ መኮንን በመጨረሻ፤ ሰብል በመኽር ተሰበሰበም ታረሰም ተጎለጎለ በገጠሩ ህይወት በግብርና ህይወት እጅግ ትልቁን የሥራ ድርሻ የሚያከናዉኑት ሴቶች ናቸዉ ሲሉ በዝርዝር ተርከዉልናል ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic