የቲምቡክቱ ቅርስ ውድመት ተጠያቂዎች | አፍሪቃ | DW | 27.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የቲምቡክቱ ቅርስ ውድመት ተጠያቂዎች

በቲምቡክቱ ከተማ የሚኖሩት የማሊ ተወላጆች የከተማይቱ ባህላዊ ቅርሶች ለወደሙበት ወንጀል ተጠያቂ ናቸው በሚል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸውን የአህመድ አል ፋቂ አል ማህዲ ዘ ሄግ ፣ ኔዘርላንድስ የሚገኘው የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት፣ «አይ ሲ ሲ» ለፍርድ በማቅረቡ ደስታ ተሰምቷቸዋል። አንዳንዶች ግን ይህን ርምጃ በቂ ሆኖ አላገኙትም።

«አላህ ወአኩባር» እያሉ ነበር በአህመድ አል ፋቂ አል ማህዲ የተመሩት የአንሳር ዲን ቡድን አባላት በተመድ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት፣ ዩኔስኮ በታሪካዊ ቅርስነት ከተመዘገቡት የማሊ 16 ጥንታዊ መካነ መቃብሮች መካከል 14ቱን እና አንድ መስጊድ በመዶሻ እና በመጥረቢያ ቅርሶቹን ያፈራረሱት። በዚሁ ድርጊታቸው ከወደሙት መካከል የታወቀው የሲዲ ያሂያ መስጊድ ይገኝበታል።
ለዚህም የሰጡት ምክንያት እነዚህ ግንባታዎች ግለሰቦችን ለማምለኪያ የታሰቡ በመሆናቸው በእስልምና እምነት ቦታ የላቸውም የሚል ነበር።
የ333 ሙስሊም ምሁራን መካነ መቃብሮች የሚገኙባት በአምስተኛው እና በ12 ኛው ምዕተ ዓመት በቱዋሬግ ጎሳ የተቆረቆረችው ጥንታዊቷ የቲምቡክቱ ከተማ ከብዙ ምዕተ ዓመታት አንስታ የእስልምና ትምህርት ማዕከል በመሆን ነው የምትታወቀው። እና የጽንፈኞቹ እኩይ ተግባር በከተማይቱ ላይ የተወው መዘዝ አስከፊ መሆኑን የከተማይቱ ከንቲባ ሀለ ኡስማን ያስታውሳሉ።
« ቲምቡክቱ በዚያን ወቅት በጠቅላላ ተመሰቃቅላ ነበር። ከላሺንኮቭ የታጠቁ የ15 ዓመት ልጆች ነበሩ በከተማይቱ መንገዶች የሚታዩት። »
አንሳር ዲን ተቆጣጥሯት የነበረችው ከመዲናይቱ ባማኮ በስትሰሜን ምሥራቅ ወደ 965 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ የምትገኘው ቲምቡክቱ ጽንፈኞቹ ይህን ወንጀል ከፈጸሙ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በፈረንሳይ፣ ማሊ እና ሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት ጦር በመሰረቱት ጥምር ጓድ ነፃ ሆናለች።

ሄግ ኔዘርላንድስ በሚገኘው የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት፣ «አይ ሲ ሲ» ለቲምቡክቱ ቅርስ ውድመት ተጠያቂ ናቸው ባላቸው የአንሳር ዲን መሪ አህመድ አል ፋቂ ማህዲ ላይ ባስተላለፈው የእስር ማዘዣ አል ማህዲ ካለፈው መስከረም ፣ 2015 ዓም ወዲህ በእስር ይገኛሉ። «አይ ሲ ሲ» ክስ የተመሰረተባቸው የ40 ዓመቱ አል ማህዲ ባለፈው ሰኞ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ጊዜ ወዲያው ነበር ጥፋተኛ መሆናቸውን ያመኑት።

« ክቡራት እና ክቡራን፣ ጥፋተኛ መሆኔን በጥልቅ ጸጸት እና ሀዘን እገልጽላችኋላሁ። በኔ ላይ የተመሰረቱት ክሶች በጠቅላላም ትክልል እና ልክ ናቸው። በጣም አዝናለh። ጸጸትም ይሰማኛል። በቲምቡክቱ ህብረተሰብ፣ በቤተሰቤ እና በሀገሬ ላይ ባደረስኩት ጥፋት በጣም አዝኛለሁ። »
ችሎቱን የተከታተሉት የቲምቡክቱ ከንቲባ ሀለ ኡስማን አል ማህዲ ጥፋተኛነታቸውን ካመኑ በኋላ በሰጡት አስተያየት ችሎቱ ማንም ከሕግ በላይ አለመሆኑን አሳይቶዋል ነበር ያሉት።
« በእውነቱ፣ ፍትሕ እውን ሆኖዋል። አምላክን እና አጋሮቻችንን በጠቅላላ እናመሰግናለን። አል ማህዲ ተይዘው እንዲታሰሩ እና ለፍርድ እንዲቀርቡ የረዱንን ሁሉ እናመሰግናለን። ማንም ከሕግ በላይ አለመሆኑን ሁሉም ሰው ሊያውቀው ይገባል። »
እጎአ በ1998 ዓም የተቋቋመው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት፣ «አይ ሲ ሲ» በቅርስ ውድመት ተጠርጣሪን ከሶ ለፍርድ ማቅረቡ እና አል ማህዲም ጥፋተኝነታቸውን ወዲያውኑ ማመናቸው በፍርድ ቤቱ ታሪክ የመጀመሪያ ጊዜ ናቸው። ማህዲ ለዚሁ ጥፋታቸው የብዙ ዓመት እስራት ይጠብቃቸዋል። የ«አይ ሲ ሲ» ዓቃብያነ ሕግ እስከ 11 ዓመት እስራት እንዲበየንባቸው ነው የጠየቁት። ዋና ዓቃቤ ሕግ ፋጡ ቤንሱዳ በችሎቱ መክፈቻ ላይ አፅንዖት ሰጥተው እንዳመለከቱት፣ ቅርስ ማውደም ከባድ ቅጣት የሚያሰጥ ትልቅ ወንጀል ነው። ወንጀሎቹን የፈፀሙት ጽንፈኞች መሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው በኃላፊነት በመጠየቃቸው እና ከብዙ ጊዜ አንስተው ሲጠብቁት የነበረው ችሎት እውን በመሆኑ የቲምቡክቱ ነዋሪዎች መደሰታቸውን አንድ የከተማይቱ ተወላጅ አስታውቋል።
« ይህ ዓይነት ወንጀል እንደገና እንዳይፈፀም ፍትህ እንዲሰጥ እንፈልጋለን። »
በጀርመን የ«ዩኔስኮ» ኮሚሽን ፕሬዚደንት ቬሬና ሜትሰ ማንጎልድ ችሎቱ ወሳኝ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን ገልጸዋል።
« በንዲህ ዓይነት ህንፃዎች ላይ የሚፈፀም የሽብር ጥቃት በድንጋይ ወይም በባህላዊ ቅርሶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ቅርሶቹ በያዙት ትርጓሜም ላይ የተቃጣ ነው። በቲምቡክቱ ደግሞ ሕዝቡ ከነዚህ ቅርሶች ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው ነው። ከተማይቱ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራው ቡድን ሙስሊም ጽንፈኞች ተይዛ በነበረችበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ለሕይወታቸው አስጊ ቢሆንም፣ ሌሊት ተነስተው ወደ መካነ መቃብሮቹ ይሄዱ ነበር። »
ለሌሎች ጽንፈኞች ባህላዊ ቅርሶችን ቢያወድሙ ከሕግ ሊያመልጡ እንደማይችሉ ግልጽ መልዕክት የሚያስተላልፍ በመሆኑ የመብት ተሟጋቾችም ታሪካዊ የተባለውን ችሎት በቅርብ ተከታተለውታል። የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ፌዴሬሽን ባልደረባ አላሳ ዋንጋራ ስለ ችሎቱ ሲናገሩ፣
« የቲምቡክቱ ነዋሪዎች ይህንን ችሎት ሲጠብቁ ብዙ ጊዜአቸው ነው። ምክንያቱም እነዚህ ጽንፈኞች በሕዝቡ ላይ ብዙ በደል ፈፀመዋል። ጽንፈኞቹ በቲምቡክቱ ሕዝብ ምን ያህል ጉዳት ማድረሳቸውን እንዲያውቁት ችሎቱ መቀጠል አለበት። »
የባህል ቅርሶች በብዙ ሀገራትም ውስጥ በተለይ ከአሸባሪዎች ትልቅ ስጋት እንደተደቀነባቸው በጀርመን የ«ዩኔስኮ» ኮሚሽን ፕሬዚደንት ቬሬና ሜትሰ ማንጎልድ አስጠንቅቀዋል።
« የሚያሳዝነው ይህን ስጋት የሚደቅኑት ወገኖች ቁጥር ከፍ ማለቱ ነው። እስላማዊው መንግሥት አመላካከታቸውን በሰለጠነው ዓለም ላይ ለመጫን ከሚፈልጉ ሌሎች 30 አሸባሪ ድርጅቶች ጋር ጥምረት ፈጥሮዋል። የነዚህ ቡድኖች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ በብዙ ሀገራት፣ በተለይም፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪቃ ሀገራት ውስጥ ቅርስ የሚወድምበትን ስጋት መጠን ይበልጡን ከፍ አድርጎታል። »

ከማሊ ጎን በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ እና ናይጀሪያ የሚገኙ ቅርሶች በተቀናቃኝ ወገኖች መካከል በቀጠሉት ውዝግቦች ከፍተኛ ስጋት ተደቅኖባቸዋል። ለምሳሌ ፣ በሰሜናዊ ናይጀሪያ የሚገኘው እan እጎአ በ1999 ዓም በ«ዩኔስኮ» ቅርስ ጥበቃ ዝርዝር የተመዘገበው የሱኩር አካባቢ ከአሸባሪው ቡድን ቦኮ ሀራም ትልቅ ስጋት ተደቅኖበታል። የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በዚሁ በባህል እና ታሪካዊ ቅርሶች ላይ የሚፈፀመውን የማውደም ወንጀልን አስመልክቶ ባለፈው ዓመት ጠንካራ ርምጃ መውሰዱን የጀርመን «ዩኔስኮ» ኮሚሽን ኃላፊ ቬሬና ሜትስሰ ማንጎልድ አስታውሰዋል።

« የዚህ በ«አይ ሲ ሲ» የተጀመረውን ችሎት ትርጓሜ አጋኖ መመልከት አይቻልም። የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት እጎአ በ2015 ዓም ባሳለፈው ውሳኔ አንቀጽ 2199 ባህላዊ ቅርሶችን የሚወድሙበትን ወንጀል አውግዞ ፣ ድርጊቱን በጦር ወንጀል ስር አስቀምጦዋል። ፓለም በዚህ ውሳኔ ላይ ዓለም ሁሉ ተስማምቶበታል። »
በዘ ሄግ ችሎቱ መጀመሩ መልካም ቢሆንም፣ ትኩረቱን የባህል ቅርስ በወደመበት ወንጀል ላይ ማድረጉ ወቀሳ አስነስቶበታል። ጽንፈኞቹ የአንሳር ዲን አባላት በቲምቡክቱ ከተማ ከዚሁ ጎን የፈፀሙዋቸውን ዝርፊያ፣ ክብረ ንጽሕና መድፈርን የመሳሰሉትን ከባድ ወንጀሎችንም ሊመለከት በተገባው እንደነበር ነው የማሊ ተወላጁ የመብት ተሟጋች ጠበቃ ባካሪ ካማራ የገለጹት።
« የጦር ወንጀል ተመልካቹ ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ ሌሎቹንም ወንጀሎች፣ ማለትም፣ ወሲባዊ ጥቃትን፣ የግዳጅ ጋብቻን ወይም ክብረ ንፅሕናን መድፈርን ፣ ቁም ስቅል ማሳየትን፣ ባጠቃላይ በሰሜን ናይጀሪያ በሚኖሩት ሴቶች ላይ የተፈፀሙትን ወንጀሎች እንዲመረምሩ እንፈልጋለን። »
በቲምቡክቱ ቅርስ ውድመት ፍርድ ቤት ክስ በተመሰረተባቸው አል ማህዲ ላይ «አይ ሲ ሲ» የፊታችን እጎአ መስከረም 27 ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። የተከሳሽ ጠበቃ እና ዓቃቤ ሕግ አል ማህዲ ከዘጠኝ እስከ 11 ዓመት እስራት ከተበየነባቸው ይግባኝ እንዳይሉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
አርያም ተክሌ
እሸቴ በቀለ