የቱኒዚያ ሕዝባዊ አመፅ እና አስተጋብኦቱ | ዓለም | DW | 24.01.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የቱኒዚያ ሕዝባዊ አመፅ እና አስተጋብኦቱ

ሙባረክ ተቃዋሚዎቻቸዉን አሸባሪ፥ እስላማዊ ነዉጠኛ እያሉ እያሳሰሩ፥ እያስገረፉ፥ እያስገደሉ ሰላሳ አመት መግዛታቸዉ አልበቃ ያለ-ይመስል ሥልጣናቸዉን ልክ እንደ ዙፋን ለልጃቸዉ ለማዉረስ እየተዘጋጁ ነዉ

default

ቱኒስ


የቱኒዚያ ሕዝባዊ አመፅ ዉጤትን አስታከን ባለፈዉ ሳምንት እኛም እንዳቅሚቲ-የብዙዎችን ጥያቄ-ጠይቀን ነበር።ማነሕ ባለተራ ብለን።ጥያቄዉ በርግጥ ዛሬም እቅጩን መልስ አላገኘም።ሰኞ ዞሮ እስኪገጥም ግን የቱኒዚያዉ ሕዝባዊ አመፅ አስተጋብኦት አልጄሪያን እየነዘረ፥ ግብፅን እየወዘወዘ፥ የመንን እያስነጠሰ፥ ዮርዳኖስን ጎንጦ፥ አልባንያን እየናጣት ነዉ።በየሐገሩ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ አመፅ-ቁጣ እንዴትነት፥ ምክንያት፥ ዉጤቱ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።

የሃያ-ዘጠኝ አመቱ ወጣት ታሪክ አል-ታይብ መሐመድ ኢብን ቡዛዚ-እንደ እሳት ራት እራሱን ከእሳት ሲማግድ ጭል ጭል ይል የነበረዉን ሕዝባዊ እሳት ያዉ እንደ እሳት ራትዋ ያጠፋዋል እንጂ ያንቀለቅለዋል ብለዉ የገመቱ የቅርብም የሩቅም ታዛቢዎች ጥቂቶች ነበሩ።ታሪክ ታሪክ ሠርቶ አለፈ-አረፈ።

Proteste in Algerien Flash-Galerie

አልጀርስ

ዓሊ ኤል ባዝ የተወለዱት ከሞሮኮ ቤተ-ሰብ ሞሮኮ ነዉ። አል-ጄሪያ አደጉ።ፓሪስ ይኖራሉ።ፈረንሳይ ዉስጥ የሚሠሩ የመግሪብ ሐገራት ተወላጆችን የሚያስተባብር-የሚያስቀጥር መስሪያ ቤት ሐላፊ ናቸዉ።ሞሮኮን እንደ ተወለዱባት፥ አልጄሪያን እንደ አዳደጉባት፥ቱኒዚያን በቅርብ እንደሚያዉቁ-እንደሚሰሩባት ሐገር የሚያዉቋት ኤል ባዝ እንደ ብዙ ብጤዎቻቸዉ እራሷን በእሳት ያጋየዉ ቱኒዚያዊ ወጣትን መልዕክት-አስተምሕሮት ለመገንዘብ ብዙ መጠበቅ ነበረባቸዉ።

«የቱኒዚያ የተቃዉሞ ሠልፍን ለብዙ አመታት ከሐምሳ የማይበልጡ ሰዎች ጩኸት አድርገን ነበር የምናየዉ።አመፁ ሲጠናከር የተሳታፊዉ ብዛት ጨመረ።ያኔ ነዉ ምን እየሆነ እንደሆነ ማስተዋል የጀመርኩት።ቢን ዓሊ በሥልጣን መቆየት አይችሉም የሚለዉ ጭምጭምታ ባለፉት ሳምንታት መሰማት ሲጀምር ደግሞ የተቃዋሚዉ ቁጥር እያየለ፥ ተቃዉሞዉ እየተጠናከረ መጣ።(ባለፈዉ ሳምንት) ቅዳሜ ቤን አሊ መሰደዳቸዉ እንደተሰማ ፈንጠዝያ ሆነ።»

ቱኒዚያዊዉ በርግጥ ፈነጠዘ።

ቱኒዚያ በጣሙን ርዕሠ-ከተማ ቱኒዝ ግን ለሕዝባዊ አመፅ ድል ጭዳ የሆኑ ዜጎችዋን በጅምላ አሰበች እንጂ፥የታሪክን ልዩ ታሪክ ለመመዝገብ፥ የሃያ ሰወስት አመት ፈላጭ ቆራጭ ገዢዋ የተባበረሩ፥ አምባገነን ሥርዓታቸዉ የተገረሰሰበትን ሳምንት ለመዘከር፥ ፅዳጅ፥ ክሳይዋን ለማፅዳት ዛሬም ፋታ አላገኘችም።የቱኒስ ነዋሪ የቀድሞ ገዢዉ ዘይን አል አቢዲን ቤን ዓሊ የተከሉት ፖለቲካዊ ነቀርሳ ከሥሩ እንዲነቀል ዛሬም እንደታገለ፥ ባደባባይ እንደተሰለፈ፥ እንደጮኸ ነዉ።

«ሐገሪቱን የሚያድን መንግሥት ነዉ-የምንፈልገዉ።የሕዝቡን ጥያቄና ፍላጎት የሚቀበል መንግሥት እንፈልጋለን።»ይላል-ከሰልፈኛዉ አንዱ።ቱኒዚያ በርግጥ ቅንቅኗን አላረገፈችም።የሕዝባዊ አመፅዋን ትልቅ ምርት ግን አፍሳለች።የቀድሞ ሥርዓቷ ተሽቀንጥሮላታል።የዚያን ሥርዓት ግፍ ፍራቻ የተሰደዱ ዜጎችዋም ይፈነጥዛሉ።የዚያኑ ያክል ይጠራጠራሉም።

Flash-Galerie Textilarbeiter Ägypten Protest 2008

ካይሮ

«አምባገነኑ በመወገዱ ደስተኞች ነን።ግን ሐገራችን ሁኔታ ያሳስበናል።»

ይላሉ ፈረንሳይ የሚኖሩት ቱኒዚያዊ።ሌለኛዋ ግን ኢል ባዝ እንዳሉት ይፈነድቃሉ።«ነፃ ነኝ።እስካሁን ሐገሬ መግባት አልችልም ነበር።ምክንያቱም የቤን አሊ ተቃዋሚ በመሆኔ ከተሰደድኩ ሃያ አምስት አመቴ።»

ቤን ዓሊ እንደ ብዙ ብጤዎቻቸዉ ሁሉ ሕዝባዊዉን አመፅ ለማዳፈን ያወሰዱት እርምጃ ያልሞከሩት ሥልት አልነበረም።የሕዝቡን ቁጣ የቀሰቀሰዉ የኑሮ በተለይም የምግብ ሸቀጥ ዋጋ ንረት ብቻ ነዉ ብለዉ ለማቅረብ ሞክረዉ ነበር።ይሕን እንደ ምክንያት ማቅረቡ ጥሩ ማምለጫ ነበረዉ።የአለም ምጣኔ ሐብት ቀዉስ፥ እና የአለም የምግብ ሰብል እጥረት-የሚል ሰበብ መፍጠር ቀላል ነበርና።

የአለም ምግብ ድርጅት ባልደረባ ራልፍ ዙድሆፍ እንደሚሉት የምግብ ሠብል በተለይ አብዛኛዉ አለም የሚመገበዉ የስንዴ ሰብል እጥረት የለም።

«በቂ የስንዴ ክምች አለ።የስንዴ ዋጋ የሚንርበት ምንም አይነት ምክንያት የለም።አንዳድ ነጋዴዎች ዋጋዉ ይጨምራል በሚል እምነት ክምችታቸዉን ለገበያ አያቀርቡ ይሆናል።ይሕ ደግሞ ደሐዉ ብዙ በጣም ብዙ እንዲያወጣ ያስገድደዋል።»

ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን፥ የምግብ ሸቀጥ ዋጋ ንረት ቤን-ዓሊን ላስወገደዉ ሕዝባዊ አመፅ ግመት አንዱ ምክንያት መሆኑ አያጠራጥርም።ሁሉም ግን አይደለም።ዋናዉ ሊሆንም አይችልም።ሥራ አጥነት መበራከቱ፥ ፖለቲካዊ ነፃነት መገደቡ፥ ነፃ መገናኛ ዘዴዎችን መታፈኑ፥ዋልጌነት፥ ሙስና መስፈኑ፥ የአንድ ሰዉ፥የአንድ ጎሳ ወይም ዘር አገዛዝ መስፈኑ ከብዙዎቹ ምክንያቶች ዋንኞቹ ናቸዉ።
ታሪክ አል-ጠይብ መሐመድ ቢን ቡዛዚ እራሱን በእሳት ያጋየዉ ሥራ-አጥቶ አትክልት ፍራፍሬ በመቸርቸሩ ብቻ አልነበረም።ገበያ ሥልጣ ብቻ አልነበረም።ጉቦ የጠየቁት ፖሊሶች ሸቀጡን ሥለወረሱበት፥ ሥለደደቡ-ሥላንገላቱት ብቻ አልነረም።በደሉን የሚያሰማበት-መስሪያ ቤት፥ የሚሰማለት ባለሥልጣን በማጣቱ ጭምር እንጂ።ፍትሕ።

አልጀሪያም-መሐመድ ቡዛዝን ብጤዎች አላጣችም።አል-ጄሪያዎች እንደ ቱኒዚያዎች ሁሉ ብልጭ ድርግም የሚል የአደባባይ ሠልፍ ተቃዉሟቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።ርዕሠ-ከተማ አልጀርስን የሚነዝረዉ የአደባባይ ሠልፍ-ተቃዉሞ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በሰልፈኛዉና በፀጥታ አስከባሪዎች መካካል በተረገ ግጭት አርባ-ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።

አልጄሪያ ዳግማዊት ቱኒዚያ መሆን-አመሆኗ አሁንም አለየም።አመፅ-ግጭቱ ግን እንደቀጠለ ነዉ።አል-ጄሪያን ለበርካታ አመታት ያበጠዉን የርስ በርስ ግጭት፥ ቁርቁስ ያስወገዱ፥ የኢትዮ-ኤርትራን ጨምሮ አፍሪቃ ሐገራትን ጠብ ፥ዉዝግብ ለማግረብ የጣሩ እየተባሉ ሲደነቁ፥ በምዕራቦች ሲንቆለጳጰሱ የነበሩት ፕሬዝዳት ቡተፈሊቃን ሕባቸዉ ትናንት አደባባይ የወጣዉን ተቃዋሚ ካስተባበሩት አንዱ እንዳሉት በቁን በቃንዎት እያላቸዉ ነዉ።

«ዛሬ አልጀርስ አደባባይ የወጣነዉ፥ በሙስና የተዘፈቀዉ፥ በተጭበረበረ ምርጫ ሥልጣን የያዘዉ፥ ጨቋኙ የአልጄሪያ ገዢ ሥርዓት የሚከተለዉን መርሕ በመቃወም፥ የተለየ መርሕ ለመንደፍ ነዉ።»

ግብፅ አሰልሳለች።ፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክ ለምዕራባዉያን በጣሙን ለዩናይትድ ስቴትስ ከአረብ ሐገራት መሪዎች ሁሉ የቅርብ ወዳጅ፥ ጠንካራ-ታማኝ መሪም ናቸዉ።ለወዳጅ ታማኝነታቸዉ ዉለታ በየአመቱ እስከ ሁለት ቢሊን ዶላር የሚደርስ ድጋፍ ርዳታ ይንቆረቆርላቸዋልም።በሰላሳ አመታት የአጋዛዝ ዘመናቸዉ የዋሽንግተን ብራስልስ ድጋፍ-እገዛ አድናቆት እንዳልተለያቸዉ ሁሉ ከሕዝባቸዉ ቅሬታ-ተቃዉሞ አምለጠዉ አያዉቅምም።

የምዕራቦቹን ድጋፍ ጠንከራ መከታ፥ የአሸባሪዎችን ጥቃት ጥሩ ሰበብ፥ ማብቂያ የለሹን የፍልስጤም እስራኤሎችን ግጭት ዉዝግብ ደሕና ማሳበቢያ ያደረጉት ሙባረክ በየጊዜዉ የሚነሳዉን ተቃዉሞ ለመደፍለቅ ብዙም ተጨንቀዉ አያዉቁም።ከቤን አሊ በሕዋላ ግን የሙባረክ የአገዛዝ ሥልት ብልሐት የተጋለጠ ይመስላል።ሕዝባቸዉ የሚከፍለዉን ከፍሎ መብት-ነፃነቱን ለማስመለስ እየፈራም ቢሆን አንድ-ሁለት እያለ ነዉ።እንደ መሐመድ ቡዛዚ እራሱን ያቃጠለም አለ።

እሱ ደግሞ እንዴት አርፈን እንቀመጥ ይላል።«በሰሚያ አመት አዛዉንት የሚገዛዉ ሕዝብ ከጫንካዉ የተሸከመዉ ከብዶታል።እንዴት አርፎ ይቀመጣል።ዝም ብለን ልንቀመጥ አንችልም።ሌላዉ ሐገር የሆነዉ እዚሕም መሆን አለበት።»

ሙባረክ ተቃዋሚዎቻቸዉን አሸባሪ፥ እስላማዊ ነዉጠኛ እያሉ እያሳሰሩ፥ እያስገረፉ፥ እያስገደሉ ሰላሳ አመት መግዛታቸዉ አልበቃ ያለ-ይመስል ሥልጣናቸዉን ልክ እንደ ዙፋን ለልጃቸዉ ለማዉረስ እየተዘጋጁ ነዉ።ከዚያ በፊት ግን ከሕዝብ አመፅ ጋር መጋፈጥ አለባቸዉ።በተጭበረበረ ምርጫ ሲንደላቀቁበት የኖሩትን የካይሮ ቤተ-መንግሥትን ለመቆጣጠር ከልጃቸዉ ወይም ከተቃዋሚዎቻቸዉ የሚቀድመዉን ላሁኑ በግልፅ የሚያዉቅ የለም።እና ጊዜ ነዉ በያኙ።

ዮርዳኖስም እንዲያ ናት።ቱኒዚያ የተቀጣጠለዉ አመፅ በአልጀርስ ዞሮ ካይሮ ደርሶ አማን ሲገባ ደከም-ረገብ ያለ መምሰሉ አልቀረም።የዮርዳኖስ ሕዝብ አመፅም ከሐገሪቱ ዘዉዳዊ አገዛዝ ይልቅ በጠቅላይ ሚንስትሩ በሚመራዉ መንግሥት ላይ ያነጣጠረ ነዉ።ንጉስ አብደላሕ የሕዝቡን ብሶት ቁጣ «አዳምጬያለሁ» ለማለት፥ ጠቅላይ ሚንስትር መንግሥታቸዉ ተቃዉሞዉን ለማቀዝቀዝ የመሠረታዊ ሸቆጦች ዋጋን ለማስቀነስ ቃል ገብዘዋል።

Flash-Galerie Albanien Tirana Unruhe Januar 2011

አልባንያ

ከተቃዉሞ ሠልፈኛዉ አስተባባሪዎች አንዱ እንደሚሉት ግን ብዙ ሕዝብ የመሪዎቹን ቃል የሚያምን አይነት አልሆነም።«መንግሥት የሸቀጥ ዋጋ ለመቀነስ የገባዉን ቃል ገቢር ያደርገዋል ብለን አናምንም።ይሕ የሕዝቡን ተቃዉሞ ለማቀዝቀዝና የተቃዉሞ ሠልፉን ለማስቆም የተገባ ቃል ነዉ።»
የዮርዳኖስም ጉዞ ወዴትነት አለየም።

የመንም በሕዝባዊ አመፅ እየተርገበገበች ነዉ።አመፁ እዚሕ አዉሮጳ ተሻግሮ አልባንያንም አርገፍግፏታል።የከሰሐረ-በስተደቡቡ አፍሪቃዊ የሰሜን ጎረቤቶችን እቅድ-እርምጃ ይሰማል።ግን ዝም-ብሏል።ዝም።ቱኒዚያን ቀጣይ አሰላሽ መኖር-አለመኖሩ፥ ካለም ማንነቱም ዛሬም-እንደ መሰንበቻዉ ሁሉ ጥያቄ ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ

ተዛማጅ ዘገባዎች