1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱርክ ፓርላማ፤ የተ መ ድ -IS እና ኢራቅ

ሐሙስ፣ መስከረም 22 2007

የቱርክ ፓርላማ ፤ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ከድንበር ማዶ ወደ ኢራቅና ሶሪያ በመግባት የ IS ታጣቂዎችን እንዲወጋ በተካሄደ የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት መደገፉ ተነገረ። ከ3/4ኛ በላይ የሕዝብ እንደራሴዎች ያጸደቁት ውሳኔ በተጨማሪ የውጭ ሃገራት

https://p.dw.com/p/1DPBd
ምስል Reuters

ወታደሮች ቱርክ ውስጥ በመሥፍር ለተጠቀሰው ዓላማ በቱርክ የጦር ሠፈሮች እንዲገለገሉም ይፈቅዳል።

በኢራቅ ካለፈው ዓመት ጥር ወር አንስቶ በአሸባሪው ድርጅት IS እጅ ከ 9,300 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የቆሰሉትም ወደ 17,400 እንደሚጠጋ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከጀኔቭ አስታወቀ። ይሁንና ቁጥራቸው ከተጠቀሰው እጅግ ሊበልጥ እንደሚችል መገመቱንም ጠቁሟል። በዛ ያሉ የኢራቅ ተወላጆች በረሃብና በጥም እንዲሁም በህክምና እጦት መሞታቸውን ኮሚሽኑ አያይዞ ገልጿል። IS አሸባሪ ቡድን በሲቭሉ ሕዝብ ላይ አረመኔአዊ ተግባር መፈጸሙን በጅምላ መረሸኑን፤ ሴቶችንና ልጃገረዶችን ለወሲባዊ ባርነት ማጋዙን ፤ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን አስገድዶ ለውትድርና መመልመሉን የተ መ ድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አጋልጧል። አክራሪው ንቅናቄ ፤ ክርስቲያኖችን ጀሲድን ሺዓ ሙስሊሞችን ፣ ሻባኮችን ፣ የቱርክሜንስታን ዝርዮችንና ሳባውያንን መጨፍጨፉንም በመጥቀስ ተጠያቂ ነው ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የ IS ታጣቂዎች በአየር ኃይል ድብደባ ቢደርስባቸውም ፣ አሁንም ወደ ሰሜናዊቷ የሶሪያ ከተማ ኮባኔ በመገስገስ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ተክሌ የኋላ