የቱርክ ጦር ዘመቻና እንድምታዉ | ዓለም | DW | 29.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የቱርክ ጦር ዘመቻና እንድምታዉ

በሶሪያ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሮበርት ፎርድ በቅርቡ እንደነገሩት የኦቦማ መስተዳድር በዉጪ መርሑ ከሚወቀስባቸዉ ችግሮቹ የሶሪያ ቀዳሚዉ ነዉ።ፎርድ ይሕን ባሉበት ሰሞን የዩናይትድ ስቴትሱ ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከቱርክ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዉ ነበር።በጉብኝት ዉይይታቸዉ የሶሪያን ጦርነት ማንስታቸዉን መገመት አይገድም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:38

የቱርክ ጦር ዘመቻና እድምታዉ

መሳሪያዉ ጄት፤ ታንክ፤መድፍ ጠመንጃ ሊሆን ይችላል።አብዛኛዉ ግን አንድ ሐገር የተመረተ፤ ባንድ መንግሥት የተሰጠ ወይም የተሸጠ ነዉ።በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ።ተኳሾቹ ብዙ ናቸዉ።ሁለቱ ግን የአንድ ሐገር መንግሥት ጦር-የቱርክ፤ የሌላ ሐገር አማፂ ሐይል-የሶሪያ ኩርድ(PYD) ሸማቂዎች ናቸዉ።ሁለቱም በዩናይድ ስቴትስ ይደገፋሉ።ሁለቱም የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት የተሰኘዉን አማፂ ቡድን ይወጋሉ።ሁለቱም የሶሪያ መንግሥትን ይቃወማሉ።ደግሞ በተቃራኒዉ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ይወጋሉ።ሁለቱ የነሱንም ያስታጣቂ፤ ረዳት፤ የበላዮቻቸዉንም ጠላቶች ወጉም፤ እርስ በርስ ተዋጉም ሜዳቸዉ ሶሪያ፤ በአብዛኛዉ የሚያልቀዉ ሕዝብም ሶሪያዊ ነዉ።የሰሞኑ ብሷል።የዉስብስቡ ጦርነት ጥፋት፤የመወሳሰቡ ምክንያት ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።

የጥንታዊ ስልጣኔ ማዕከል፤የሰዉ ልጅ የረጅም ዘመን መኖሪያ ምድር፤ የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ መዘዉር፤ ለሐይማኖት ያልወገነ ሥርዓት አብነት ነበረች።ዛሬ የሸማቂ ቡድናት መፈልፈያ፤የሐያላን መንግሥታት ቦምብ-ሚሳዬል መፈተሻ፤ የሐብታም አረብ-ፋርሶች ገንዘብ መርጪያ የእልቂት፤ ፍጅት፤ የጥፋት፤ ስደት እንግልት ማዕከል ሆናለች።ሶሪያ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዝደንታዊ እጩነታቸዉ ባለፈዉ ሐምሌ በፀደቀበት ወቅት ዓለምን ከሚያብጠዉ ችግር የአብዛኛዉ፤ በተለይ የስደተኛና የፅንፈኞች ምንጭ ነበር ያሏት።ሶሪያን።ሶሪያ፤ ትራምፕ፤ በተደጋጋሚ እንዳሉት የዘመናችን ዓለም ችግሮች አብዛኛ ምንጭ እንደሆነች ሁሉ የሶሪያ አብዛኛ ችግሮች ምንጭ ደግሞ የትራምፕ ዋና ተቀናቃኝ ሒላሪ ክሊንተን እና ባጠቃላይ የኦባማ መስተዳድር ናቸዉ።

የትራምፕ ዓላማ፤ መልዕክት፤የወቀሳ-ትችታቸዉ መሠረት በርግጥ እንድየሰሚዉ እዉነት-ሐሰት ይሆን ይሆናል።የሶሪያ ግን በርግጥ ወድማለች።ሩብ ሚሊዮን የሚገመት ሕዝቧ አልቋል።12 ሚሊዮኑ አንድም ተሰድዷል-አለያም

ተፈናቅሏል።የሶሪያ ጥፋት፤ የሕዝቧ እልቂት ፍጅት ስደት ዓለም ችግር ከሆነ ዓለምን የምትመራዉ ልዕለ-ሐያል ሐገር ከብዙዎቹ ተጠያቂዎች አንዷ መሆንዋ አያነጋግርም።

በሶሪያ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሮበርት ፎርድ በቅርቡ ለአሜሪካዉ ዜና አገልግሎት (ኤፒ) እንደነገሩት የኦቦማ መስተዳድር በዉጪ መርሑ ከሚወቀስባቸዉ ሁለት ወይም ሰዎስት ዋና ዋና ችግሮቹ የሶሪያ ቀዳሚዉ ነዉ።ፎርድ ይሕን ባሉበት ሰሞን የዩናይትድ ስቴትሱ ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አንካራ-ቱርክ ዉስጥ ከቱርክ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዉ ነበር።በጉብኝት ዉይይታቸዉ የሶሪያን ጦርነት ማንስታቸዉን መገመት አይገድም።

ዋና ትኩረታቸዉ ግን ቱርክ እራሱን የሶሪያና የኢራቅ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) የሚለዉን አማፂ ቡድንን ለመደምሰስ በሚደረገዉ ዉጊያ በመካፈሏ ማወደስና ማድነቅ እንጂ አካባቢዉን ላመነቃቀረዉ ጦርነት ሁነኛ መፍትሔ መፈለግ አልነበረም።

የቱርክ ጦር ጥቃት ግን በISIS ላይ ብቻ ያነጣጠረ አልነበረም።መንታ እንጂ።ነዉም።ISISም የኩርድ ሸማቂዎችም።ኩርድ ተብሎ የሚጠራዉ ነገድ፤ ከ950 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ የኦስማን ቱርክ እስከፈረጠመበት እስከ 1290ዎቹ ድረስ ከዛሬዋ አዘርበጃን እስከ ሰሜን አፍሪቃ፤ ከደቡብ አረቢያ እስከ ኢራን የሚገኘዉን ሰፊ ግዛት የገዛ ሐያል ነገድ ነበር።ከ1290ዎቹ ማብቂያ በኋላ የሻዳዳዲስ፤ የሐሰንዋይሒድስ፤ የአዩቢድስ እና ሌሎችም የኩርድ ጠንካራ ሥርወ-መንግሥታት እየተፈረካከሱ ግዛቶቻቸዉን ለቱርኮች ወይም በቱርክ ለሚታዘዙ ሱልጣናት ለማስረከብ ተገደዱ።

በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ማብቂያ የኦስማን ቱርክ ሥርወ መንግሥት ተፈረካክሶ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ የሚመሯቸዉ የአዉሮጳ ሐያልን አብዛኞቹን የቱርክ ቅኝ ግዛቶች ሲገዙ፤ ወይም ቅኝ ተገዢዎቹ ነፃ ሲወጡ ኩርዶችም በአዳዲሶቹ ሐገራት ግዛቶች ተከፋፈሉ። ዛሬ ደቡብ ምሥራቅ ቱርክ፤ ምዕራባዊ ኢራን፤ ሰሜን ኢራቅ እና ሰሜን ሶሪያ ዉስጥ ወደ ሰላሳ ሚሊዮን የሚገመቱ የኩርድ ነገድ አባላት አሉ።

በአራቱም ሐገራት የሚኖሩ ትርኮች ሲጠነክር የነፃነት፤ ሲቀዘቅዝ የራስ ገዝ መብት ጥያቄ እያነሱ በየጊዜዉ ከሚቀየየረዉ፤የዓለም ሐያላን እና የአካባቢዉ መንግስታት ፍላጎትና ጥቅምና ግጭት ጋራ ግራ ቀኝ ይላጋሉ።ኢራንና ኢራቅ ሲጣሉ የባግዳድ ገዢዎች

የኢራንን፤ የቴሕራን ገዢዎች የኢራቅ ኩርዶችን ያስታጥቃሉ፤ ያደራጃሉ፤ ከለላ ይሰጣሉም።ባግዳድ ከአንካራ፤አንካራ ከደማስቆ፤ አንካራ ከቴሕራን፤ ወይም ቴሕራን ከደማስቆ ከተጋጩም እንዲሁ።

«የጠላቴ-ጠላት ወዳጄነዉ» በሚለዉ ነባር ፖለቲካዊ ሻጥር ለኩርዶች የሚደረገዉ ድጋፍ-ተቃዉሞ በተቀያየረ ቁጥር በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራዉ የአዉሮጳና የአረብ ዓለም ባንድ በኩል፤ ድሮ በሞስኮ ይመሩ የነበሩት የምሥራቅና የዓረብ ዓለም በተቃራኒዉ ቆመዉ ግጭት፤ጦርነት፤ሻጥሩን ያላቀጣጠሉበት ጊዜ የለም።

ፕሬዝደንት ሰዳም ሁሴን የዋሽግተን-ለንደኖች ወዳጅ፤ የቴሕራን ጠላት በነበሩበት ዘመን የኢራቅ ኩርዶች ደጋፊ፤ አስታጣቂ፤ መጠለያ ሰጪም ቴሕራን ነበረች።ሳዳም ሁሴን የምዕራቦችና የተከታዮቻቸዉ ጠላት ሆነዉ ከተዘመተባቸዉ ጊዜ ጀምሮ ግን የኢራቅ ኩርዶች የምዕራብ ወዳጆች የኢራን ጠላቶች ናቸዉ።

የኢራቅ ኩርዶች በዩናይትድ ስቴትስ እና በብሪታንያ የጦር ጄቶች ድጋፍ ኤርቢል (ሰሜን ኢራቅ) የመንግሥት አከል መዋቅር የዘረጋ፤ የራሱን ባንዲራ የሰቀለ፤ምክር ቤት፤ ፕሬዝደንት፤ ጠንካራ ጦር ያለዉ የመንግሥት ዉስጥ መንግሥት ከመሠረቱ አስራ-ሰወስት ዓመት አለፋቸዉ።ጀላል ጠላባኒ ከኢራቅ ኩርድ አማፂያን መሪዎች አንዱ ነበሩ።ከ2005 እስከ 2014 ድረስ የኢራቅ ፕሬዝደንት ነበሩ።

ኢራቅን ኩርዳዊ ፕሬዝደንት እየመራት የኢራቅ ኩርዶችን ሌላዉ የቀድሞዉ የኩርድ አማፂ መሪ መስዑድ ባርዛኒ በፕሬዝደንት ማዕረግ ከኤርቢል ቤተ-መንግሥት ይመራሉ።ቱርክ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ነች።ከምዕራባዉያን ጋር የነበረና ያላት ግንኙነት እንቅፋት ባያጣዉም ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ «ወዳጅ» እንጂ «ጠላት» ተብላ ግን አታዉቅም።

የቱርክ ኩርዶች በ1980ዎቹ የነፍጥ ትግል ሲጀምሩ የሐፊዝ አል አሰድዋን ሶሪያ ሙጥኝ ማለት፤ በሞስኮ የሚመራዉን ሶሻሊስታዊ ዓለምን ድጋፍ ለማግኘት ኮሚንስት ሆኖ ወይም መስሎ መቅረብ ጥሩ ፖለቲካዊ ስልት ነበር።አብዱላሕ ኦጄላን የሚመሩትን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን PKK-አሉት።የኩርዲስታ ሰራተኛ ፓርቲ እንደማለት ነዉ።

ሶሻሊስታዊ ቡድን ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በፊት ከኢራን ኋላ ከምዕራባዉያን ዙሪያ መለስ ድጋፍ ከሚደረግላቸዉ ከኢራቅ ኩርድ ሸማቂዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለዉ።የኢራቅ ኩርዶች የመንግሥት ዉስጥ መንግሥት በመመስረታቸዉ የልብ ልብ የተሰማቸዉ የሶሪያ ኩርዶች በ2003 የዲሞክራቲክ አንድነት ፓርቲ (PYD) ያሉትን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሲመሠርቱም ከPKK ጋር ጥብቅ ግንኙነት መሥርቷል።

PKK ለቱርክም ለምዕራባዉያንም አሸባሪ ድርጅት ነዉ።PKKን የሚደግፉት የኢራቅም፤የሶሪያም ኩርዶች ለቱርክ አሸባሪዎች ናቸዉ።ግን ፔሽ መርጋ የተሰኘዉን የኢራቅ

ኩርድ ጦርንም፤ የሶሪያዉን PYDንም የሚያስታጥቁት የቱርክ የጦር ተሻራኪዎች ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ናቸዉ።

የአሜሪካዉ ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ባለፈዉ ሳምንት አንካራን በጎበኙበት ወቅት ISISን ለማጥፋት ሥለሚደረገዉ ዘመቻ ነበር የተናገሩት።የቱርኩ ፕሬዝደንት ሬቼብ ጠይብ ኤርዶኻን ግን ISISም PYDም ልዩነት የላቸዉም አሉ።ጥቃትም አወጁ።

«ዛሬ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ጀምሮ ጦራችን እና የፀጥታ አስከባሪ ሐይሎቻችን ሰሜናዊ ሶሪያ ዉስጥ ሐገራችንን በተደጋጋሚ በሚያሰጉ ደዓሽና PYD በመሰሉ አሸባሪዎች ላይ ዘመቻ ከፍተዋል።»

ግራ-አጋቢዉ የሐይል አሰላለፍ ሶሪያ ዉስጥ ተጨማሪ ሐይወት፤ሐብትና ንብረት እያጠፋ ነዉ።የቱርክ ጦር ሰሜናዊ ሶሪያ በሸመቁ የISIS እና የኩርድ ታጣቂዎች ላይ የምድርና የአየር ጥቃት ከጀመረ ካለፈዉ ሮብ እስከ ትናንት ድረስ በትንሽ ግምት ሰላሳ-አምስት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

ዘመቻዉ፤ ታዛቢዎች፤ እንደሚሉት ለአንካራ መሪዎች ድርብ-መልዕክት አለዉ። ቱርክ ላይ የሚደርሰዉን ጥቃት መቀነስ-ቀዳሚዉ ነዉ። የፕሬዝደንት ኤርዶኻን መንግሥት በቅርቡ በተቃጣበት መፈንቅለ መንግሥት ሰበብ አለመዳከሙን ማሳያም ነዉ። በመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ የሚጠረጠሩትን ፈቱላሕ ጉላንን ዩናይትድ ስቴትስ ለቱርክ አሳልፋ ባለመስጠትዋ የዋሽግን ፍላጎትን እንደእስካሁኑ እንደማያስታምሙ ማመልከትም ይፈልጋሉ።

በመፈንቅለ መንግሥት በሚጠረጠሩ ወገኖች ላይ በሚወሰደዉ እርምጃ ሰበብ የአንካራ መሪዎችን የሚወቅሱ ወገኖችን የትኩረት አቅጣጫ ማስቀየሪያም ነዉ።

እና ይቀጥላል አሉ-ኤርዶኻን።«ሶሪያ እና ኢራቅ ዉስጥ በአይ ሲ ስ ላይ የሚደረገዉን ወታደራዊ ዘመቻ ሙሉ በሙሉ እንደግፋለን።ለዚሕ ነዉ በዘመቻዉ የምንካፈለዉም።በኩርድ ቡድናት ላይ ተመሳሳይ አቋም ይዘናል።እነዚሕ ተገንጣይ አሸባሪዎች እስኪደመሰሱ ድረስ (ጥቃቱን) እንቀጥላለን።»

የቱርክ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እንዳሉት ጦራቸዉ በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፈዉን የሶሪያ ኩርድ ይዞታን መደብደብ የጀመረዉ በአሜሪካኖች ፍቃድና ይሁንታ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት በኩርዶች ላይ የተከፈተዉን ዘመቻ ሥለመደገፍ-አለመደገፋቸዉ እስካሁን በግልፅ ያሉት ነገር የለም።ዉጊያዉ ግን ቀጥሏል።እና ለዛሬ ይብቃን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic