የቱርክ የጥቃት ዘመቻ በሰሜን ሶርያ | ዓለም | DW | 31.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የቱርክ የጥቃት ዘመቻ በሰሜን ሶርያ

ቱርክ በሰሜን ሶርያ የከፈተችውን የጥቃት ዘመቻ ቀጠለችበት። ጥቃቱ በተለይ በእስላማዊው መንግሥት ላይ፣ በተለይ ግን በአካባቢው በሚንቀሳቀሱት የኩርዳውያን ቡድኖች ላይ ያነጣጠረ ነው። ቡድኖቹ ሶርያን ከቱርክ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ግዙፍ አካባቢ ተቆጣጥረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:49

የሶርያ ጦርነት


ቱርክ ኩርዳውያኑ ፣ በቱርክ ያሉትም ጭምር እንዳይጠናከሩ እና የሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር ጥረታቸውን ለማዳከም ትፈልጋለች። ባለፈው የሳምንት መጨረሻ በሰሜን ሶርያ በቱርክ ጦር እና በኩርዳውያን ቡድኖች መካከል ከባድ ውጊያ ተካሂዶዋል፣ ቱርክም በአየር ኃይሏ ጥቃቷን ያጠናከረች ሲሆን፣ ፕሬዚደንት ጠይብ ሬቼፕ ኤርዶኻን የሀገራቸውን ትግል ለማጠናከር ዝግጁ መሆናቸውንr ገልጸዋል።
« ሶርያ እና ኢራቅ ውስጥ በሚንቀሳቀሰው «አይ ኤስ» አንፃር የሚደረግ ማንኛውንም ትግል እንደግፋለን። ለዚህ ነው እዚህ ያለነው። ተገንጣዮቹን የኩርዳውያኑን ቡድን አሸባሪዎችን መታገልንም በተመለከተ እንዲሁ ቆርጠን ተነስተናል። እስከሚደመሰሱ ድረስ ትግላችንን እንቀጥላለን። »

የመብት ተሟጋቾች በጥቃቱ ሲቭሎች መገደላቸውን ቢያስታውቁም፣ የቱርክ ጦር የሲቭልን ህይወት ለመታደግ ጥንቃቄ እንዳደረገ እና ኩርዳውያን ተዋጊዎች፣ እንዲሁም፣ አንድ የቱርክ ወታደር ብቻ እንደሞቱ ነው ያመለከተው። የቱርክ ትግል የኩርዳውያኑ ሚሊሺያ ቡድን « YPG» የሚመራው እና በ«አይ ኤስ» አንፃር የሚዋጋው በዩኤስ አሜሪካ የሚረዳው የሶርያ ዴሞክራሲያዊ ኃይላት ጥምረት ላይ ጭምር ያነጣጠረ መሆኑን ጦሩ አመልክቶዋል።
ይህ አንዱ ሌላውን የሚዋጋበት የሶርያ ጦርነት ምን ያህል የተወሳሰበ መሆኑን ለታዛቢዎች በግልጽ ያሳየ ሌላ ምሳሌ ነው። ዩኤስ አሜሪካ በቱርክ አንፃር የሚዋጉ ቡድኖችን ጭምር መደገፍ ይዛለች። በሰሜን ሶርያ በተካሄደው ውጊያ በሕግ የተከለከለው «ፒ ኬ ኬ» የጃባኪርን አየር ማረፊያ በሮኬት ደብድቦ አስር ሰዎች ሞተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሶርያ መንግሥት ከመዲናይቱ ደማስቆ በስተደቡብ የምትገኘዋን የዳሪያን ከተማ መልሶ ተቆጣጥሮዋል። የከተማይቱ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ፋዲ መሀመድ እንዳሉት፣ የመንግሥቱ ጦር ከተማይቱን ለብዙ ጊዜ ከቧት በመቆየቱ ከውጭው ዓለም ጋር ግንኙነት ያልነበራቸው እና የምግብ እና መድሀኒት አቅርቦት ችግር ያጋጠማቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች እፎይታ ተሰምቷቸዋል።


« ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ተከበን ነበር የቆየነው። ወደመጨረሻው ላይ በከተማይቱ የነበረው የመስክ ሆስፒታል በናፓልም ቦምብ በመደብደቡ አስፈላጊው የመድሀኒት አቅርቦት እንኳን አልነበረንም። ለብዙ ጊዜ ተከበን ስለቆየን ሳይራቡ መደበኛ ኑሮ የኖሩ ሰዎች ምን እንደሚመስሉ እንኳን ከሞላ ጎደል ረስተናል ።»
የሶርያ ጦር እና ዓማፅያኑ ለብዙ ቀናት ከተደራደሩ በኋላ ባለፈው የሳምንት መጨረሻ በደረሱት ስምምነት መሰረት፣ የዳርያ ነዋሪዎችን ከከተማይቱ በማስወጣት ወደ አንድ መጠለያ ጣቢያ ተወስደዋል፣ ዓማፅያኑም ከነመሳሪያቸው ከተማይቱን በነፃ እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ፣ የሶርያ ጦር ከተማ በአንድ የጦር አየር መረፊያ አቅራቢያ የምትገኘው ስልታዊ ከተማ ተቆጣጥሮዋል። ይህ በዚህ እንዳለ በሌሎች የሶርያ ከተሞች ውጊያው እና የሲቭሉ ስቃ እና ሞት ተጠናክሮ ቀጥሎዋል።

አና ኦሲዩስ/አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic