የቱርክ ክስ እና የመብት ተሟጋቾች | ዓለም | DW | 19.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የቱርክ ክስ እና የመብት ተሟጋቾች

የቱርክ ፍርድ ቤት ክስ የተመሠረተባቸዉ ስድስት የመብት ተሟጋቾች በእስር እንዲቆዩ በትናንትናዉ ዕለት መወሰኑ ትችትን አስከትሏል።  የሀገሪቱ አቃቤ ሕግ በአሸባሪ ድርጅት ስም ወንጀል ፈጽመዋል ሲል ክስ ከመሠረተባቸዉ መካከል በቱርክ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ይገኙበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:55

ትችት ያስከተለዉ የመብት ተሟጋቾች እስራት፤

ቱርክ ሰባት የመብት ተሟጋቾች እና ሁለት የዉጭ ዜጎች የሆኑ አሠልጣኞችን ክስ ሳይመሠረትባቸዉ አስቀድማ ወደ ወህኒ የወረወረችዉ ባለፈዉ ሰኔ 28 ቀን 2009ዓ,ም ነዉ። ዘገባዎች እንደሚያስረዱት ሰዎቹ የተያዙት የዲጂታል ደህንነት እና የመረጃ አስተዳደር አዉደ ጥናት ሲያካሂዱ ከነበረባት ከኢስታንቡል በስተደቡብ ከምትገኝ ደሴት ነዉ። ትናንት የቱርክ ፍርድ ቤት ከዘጠኙ ታሳሪዎች ሦስቱን በሕጋዊ ግዴታ ገብተዉ እንዲለቁ ሲወስን ቀሪዎቹ ሥድስቱን ሽብርተኝነትን ደግፋችኋል ሲል በእስር እንዲቆዩ ወስኗል። የቱርክ አቃቢያነ ሕግ በቱርክ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ኢዲል ኤሰርን ጨምሮ እንዲታሠሩ የተወሰነባቸዉን አባል ሳይሆኑ ግን በአንድ ሽብርተኛ  ድርጅት ስም ወንጀል ፈጽመዋል ሲሉ ይከሳሉ። በእነሱ ላይ ትናንት በቱርክ ፍርድ ቤት የተላለፈዉ ዉሳኔ በፕሬዝደንት ራሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን በምትመራዉ ሀገር ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት እየኮሰመነ መሄዱን ያመላክታል በሚል ትችት አስከትሏል። መጀመሪያ ላይ ከታሠሩት 10 ሰዎች ስምንቱ የቱርክ ዜጎች እና የመብት ተሟጋቾች ሲሁኑ ሁለቱ ደግሞ አንዱ የጀርመን አንደኛዉ ደግሞ የስዊድን ዜጎች እና የአዉደ ጥናቱ አስተባባሪዎች ናቸዉ።

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የፔተር ሽቶይትነር የኑሮ አጋር ማግደሊና ፍሮደንሹስ ከታሠሩ ጀምሮ በጠበቆች አማካኝነት ብቻ መረጃ መለዋወጥ እንደቻሉ ነዉ የሚናገሩት።  ያካሂዱት የነበረዉ ሥልጠና ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መረጃን እንዴት ማከማቸት እንደሚችሉ የሚያመለክት የመረጃ አስተዳደርን እንደሚመለከት አክለዉ የገለፁት ማግደሊና ፍሮደንሹስ ሥልጠናዉ ኮምፕዩተር የሚጠቀም ሁሉ ዲጂታል በሚባለዉ በዘመናችን ሊያዉቀዉ የሚገባ እንደሆነ ነዉ የዘረዘሩት። እንዲያለዉ ሥልጠናም እንዴት ተለዉጦ ከሽብርተኝነት ጋር እንደተሳሰረ ሊገባቸዉ እንዳልቻለም ገልጸዋል። ሽብረተኛ ቡድንን መርዳት በሚል የቀረበባቸዉን ክስም ትርጉም የሌለዉ በማለት አጣጥለዋል።

«ፍፁም ትርጉም የላቸዉም። ፒተር የአሊጋራቢ ተባባሪ አሰልጣኝ ነዉ፤ እሱም ሆነ አብረዉን የሚያሰለጥኑትም ሆነ ስምንቱ የመብት ተሟጋች ቱርካዉያን ለሥራቸዉ የሚቆሙ እና፤ ከሥራቸዉ እና ከሰብዕናቸዉ ጋር የሚቃረን ነገር ነዉ ይሄ። ለሰብዓዊ መብት ነዉ የቆሙት።»

በዜጋዉ መታሠር ስጋት እንደገባዉ ያመለከተዉ የስዊድን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን እንደሚመረምር አስታዉቋል። የስዊድን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ ለሰብዓዊ መብቶች መሟጋት ቱርክ ዉስጥ ወንጀል መሆኑን እንደሚያመለክትም ተናግረዋል።

የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ባወጣዉ የጽሑፍ መግለጫ የዜጋዉ የፔተር ሽቶይትነር እና የሌሎቹ አምስት የመብት ተሟጋቾች መታሠር ተቀባይነት የለዉም ሲል አዉግዟል። እንደ ፔተር ሽቶይትነር ያለ የመብት እና የዴሞክራሲ ተከራካሪን ሽብርተኞችን ይደግፋል ማለትም የተሳሳተ ነዉ ሲል በመግለጫዉ ዘርዝሯል። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም በማንኛዉም ደረጃ ከጎኑ በመቆም ትብብራችንን እናሳያለን፤ እንሟገትለትማለን ብለዋል።

«እናም ይህ እስር ምክንያት የለሽ እንደሆነ በሚገባ ተረድተናል። እንደጀርመን መንግሥት እኛ እናወግዘዋለን። ከእሱ እና ከሌሎቹ ታሳሪዎች ጎን እንደሆንንም እንገልጻለን ። እሱን ለማስለቀቅም እንደጀርመን መንግሥት ማድረግ የሚገባንን ሁሉ እናደርጋለን። ይህ በእኛ ዕይታ ንፁሐን ሰዎች በሕግ ሥርዓቱ ሽክርክሪት እንደሚታሠሩ የሚያሳይ ሌላ አሳዛኝ ምሳሌ ነዉ።»

ዩናይትድ ስቴትስም የቱርክ ፍርድ ቤት በመብት ተሟጋቾቹ ላይ የወሰደዉን ርምጃ አዉግዛለች። የአሜሪካዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፤ ሄዘር ኖየርት «አነስተኛ መረጃ ወይም ግልጽነት የሌላቸዉ እንዲህ ያሉ ክሶች የቱርክን የሕግ የበላይነት እና የግለሰቦችን መብት የማክበር ግዴታዋን ዝቅ የሚያደርጉ ናቸዉ።» ማለታቸዉ ተጠቅሷል። ኑዮርት አክለዉም ታሳሪዎቹን ቱርክ ባስቸኳይ እንድለቅ ጠይቀዉ፤ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ክሱን እንዲያነሱም ተማፅነዋል።። ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል እስራቱን፤ «አስቂኝ በሆነ መልኩ ስልጣንን አላግባብ መጠቀም» ሲል ኮንኗል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች