የቱርክ-ሶርያ ውዝግብና የኔቶ ውሳኔ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 19 2004
በሶርያ ወቀሳ አንጻር፣ "ኤፍ 4 ፋንቶም " የተባለው የቱርክ ተዋጊ አይሮፕላን ተመቶ በወደቀበት ጊዜ በሶርያ የበረራ ክልል ውስጥ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ክልል ውስጥ እንደነበረ ነው ቱርክ ያስታወቀችው። ቱርክ አባል የሆነችበት የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን ኔቶ የሶርያን ርምጃ ተቀባይነት የሌለው ሲል በጥብቅ አውግዞታል።
በቱርክ ጥሪ መሠረት ኔቶ ሶርያ የቱርክ ተዋጊ አይሮፕላንን መታ በጣለችለት ጉዳይ ላይ ዛሬ በልዩ ስብሰባ ከተወያየ በኋላ ድርጊቱን ማውገዙን የኪዳኑ ዋና ፀሐፊ ፎኽት አንደርስ ራስሙሰን አስታውቀዋል።
« ይህን ተግባር ተቀባይነት የሌላቸው አድርገን እናየዋለን። በመሆኑም በጥብቅ አውግዘነዋል። ይህ የሶርያ ባለሥልጣናት ዓለም አቀፍ ደንቦችን፡ ሰላምን እና ፀጥታን የሰው ሕይወት ደንታ እንደሌላቸው የሚያሳይ ተጨማሪ ምሳሌ ነው። »
ሀያ ስምንቱ አባል ሀገሮች የሚጠቃለሉበት ኔቶም ከቱርክ ጎን መቆሙን ራስሙሰን አክለው አረጋግጠዋል። ኔቶ በአንድ አባል ሀገር ጥሪ መሠረት ምክክር ለማድረግ ልዩ ስብሰባ ሲጠራ ይህ ሁለተኛው ጊዜ ነው። እአአ በ 2003 ዓም የኢራቅ ጦርነት ሊካሄድ ጥቂት ጊዜ ሲቀረው ቱርክ የድንበርዋን ጥበቃ ለማረጋገጥ የኔቶን ድጋፍ በጠየቀችበት ጊዜ ነበር ኔቶ የመጀመሪያውን ልዩ ስብሰባ የጠራው።
የአውሮጳ ህብረትም ሶርያ የአየር ክልሏን ጥሶ ገብቶዋል በሚል የቱርክ ተዋጊ አይሮፕላንን መታ በምሥራቃዊ ሜድትሬንያን ባህር የጣለችበትን ድርጊት አውግዞታል።
አይሮፕላኑ ተመቶ በወደቀበት ጊዜ የምሥራቃዊ ሜድትሬንያን ባህር የተተከሉ ራዳሮቹን በመፈተሽ የስልጠና በረራ ላይ ነበር።
የቱርክ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ቢውለንት አርኒች ሀገራቸው ጦርነት ፈላጊ አለመሆንዋን ቢገልጹም፡ የሶርያ ርምጃ ካለምላሽ እንደማይቀር ዝተዋል።
« ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት መደረግ ያለበት ሁሉ ይደረጋል። ግን ጦርነት የማወጅ ዓላማ የለንም። »
ይህ በዚህ እንዳለ፡ ሁለት በሶርያ ተመቶ የወደቀው አይሮፕላን አብራሪዎችዋን ፍለጋ ያሰማራችው ሌላ ሁለተኛ አይሮፕላንዋም እንደተመታባት ቢውለንት አርኒች አክለው አስታውቀዋል።
« የነፍስ አድን ቡድኖችን የያዘ አንድ " ካዛ" የተባለ አይሮፕላን፣ የጠፉትን ሁለት አብራሪዎች ፍለጋ በተሰማራበት ጊዜ ከመሬት በኩል ጥቃት ተሰንዝሮበታል። በዚሁ ጊዜ ከሶርያ መንግሥት ጋ ግንኙነት በማድረጋችን ጥቃቱ ሊቆም ችሎዋል። »
ፍለጋው ቢቀጥልም አብራሪዎቹ በሕይወት መገኘታቸው አጠራጣሪ መሆኑን የቱርክ መንግሥት አስታውቆዋል። ቀደም ሲል ቱርክ ለተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ የሶርያ ፀብ አጫሪ ርምጃ የቱርክን ብሄራዊ ፀጥታ ብቻ ሳይሆን ላካባቢው ሰላምና ፀጥታም አሳሳቢ ስጋት መሆኑን ገልጾዋል።
አርያም ተክሌ
ተክሌ የኋላ